ሕወሓት ማን እንደሆነ ከ27 ዓመት በኋላም ያለተገለጸላቸው ወይንም ሕወሃትን መቃወም መደበሪያ እና የገቢ ምንጭ ያደረጉ አሊያም ሁሉንም እየተረዱ እነለማ ገዝፈው ከለሉን፣ከመስመራችንም አስወጡን የሚሉ የውዥንብሩን ቫይረስ ተሸክመው እያሰራጩት፣ ጥቃትም እየሰነዘሩ ይገኛሉ። በቅንነት ቅን አስተያየት የሚሰነዝሩ ሃሳባቸውን በግሌ እያከበርኩ በአጭሩ የምጨምረው ነገር ቢኖር አንቸኩል፣እንመርምር የሚል ነው።
ፋሲል የኔዓለም በዚህ ዙሪያ በማህበራዊ ገጹ ያሰፈረውም ይበልጥ ግዛቤ ይፈጥራል እና ይመልከቱት
– በህወሃት ቁጥጥር ስር የሚገኘው የደህንነት ተቋም፣ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚን ስብሰባ በተመለከተ አንዳንድ መረጃዎችን “እያሾለከ” እያወጣ ነው። የሚለቀቁት መረጃዎች ደግሞ በለማና አብይ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። ሁለቱም ሰዎች በስብሰባው ላይ የተለዬ ተቃውሞ እንዳላሰሙ የሚያሳይ ጽሁፍ አንብቤአለሁ። ። ሽፈራው ሽጉጤም ስብሰባው ያለችግር እየተካሄደ ነው የሚል መግለጫ ሰጥቷል። በጎን ደግሞ የህወሃት ድረገጾች በእነ አብይ ላይ ያሚያደርጉትን ዘመቻ አጠናክረዋል። ህወሃት ህዝብ የሚወደውን ሰው ለማስመታት ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አንዱ፣ ሰውዬው የእሱ ደጋፊ ሳይሆን ልክ የእሱ ደጋፊ እንደሆነ አድርጎ አሉባልታ በመንዛት ነው። የህወሃትን ሴራ ሳይገነዘቡ በህወሃት አሉባልታ የሚወናበዱ ሰዎች፣ “ እሱማ ከህወሃት ጋር ይሰራል” ብለው የሚወዱትን ሰው መደገፍ ሲያቆሙና ህወሃትም የሰውዬው ህዝባዊ ድጋፍ መቀነሱን ሲያይ፣ በሰውዬው ላይ የመውጊያ ጩቤውን ይመዛል። በህወሃት አሉባልታ ህዝባዊ ድጋፉ መሸርሸሩን የተረዳው ሰው፣ ህልውናውን ለማቀዬት ሲል የህወሃት ታዛዥ ሆኖ ያገለግላል፤ አልያም ዋጋ ይከፍላል።
በእነ አብይ ላይ የሚለቀቀው የፕሮፓጋንዳ አላማም ከዚህ ተለይቶ መታዬት ያለበት አይመስለኝም ፤ ሰዎቹ ከህወሃት ጋር እንደተሰለፉ አስመስሎ በማስወራት ህዝባዊ ድጋፋቸውን ለመሸርሸርና በሂደት ለመምታት ታስቦ የሚለቀቅ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ይሰማኛል። ከሚሰጡት መግለጫዎችና ጽሁፎች ተነስቼ የህወሃት የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ በጥሩ መልኩ እየሄደ እንዳልሆነ መገመት እችላለሁ። እነ ለማ የትግል ስልት ለውጥ ያደረጉም ይመስለኛል ፤ በአደባባይ ብዙ ባለማውራት “ሙያ በልብ ነው” የሚለውን አገራዊ ብሂል ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ይሰማኛል። በስራ አስፈጻሚው ስብሰባ ላይም ጠንካራ አቋም ይዘው እንደቀረቡ እገምታለሁ ። ያ ባይሆን ኖሮ “አብይ እንዲህ አለ ፣ ለማ እንዲያ ተናገረ” እየተባለ አሉባልታ መንዛት ባለስፈለገ ነበር። ህወሃቶች በራስ መተማመን ቢኖራቸውና ምንም እንዳልተፈጠረ ቢያምኑ ኖሮ የስብሰባውን ሙሉ ውይይት ቀርጸው ያቀርቡልን ነበር። አሁን “ በውስጥ አዋቂ” ስም የሚወጣው ቁንጽል መረጃ ሆን ተብሎ ከህወሃት የመረጃ ማቀነባበሪያ ቢሮ የሚወጣ ማደናገሪያና እነ አብይን ከህዝብ ነጥሎ ለመምታት የሚደረግ ሙከራ ነው ብዬ አምናለሁ።
ለማንኛውም “የበይዎች አለመስማማት ለተበይ ይጠቅመዋል” እንዲሉ፣ እነሱ ሽኩቻቸውን ሲቀጥሉ፣ የነጻነት ሃይሉም የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል አለበት። እውነተኛ ለውጥ በእኛ ትግል እንጅ በእነሱ መልካም ፈቃድ አይመጣም።