>
5:13 pm - Tuesday April 19, 1881

"እርቅ… ……ቅብጥርጥስ" (ጌታቸው ሺፈራው)

 ገዥዎቹ ሲጨንቃቸው ሰሞን ከራሳቸው ሰፈር የማይርቁትን፣ ሕዝብ ሲበደል ዝም ብለው የከረሙትን “ሽማግሌ፣ የሀይማኖት አባት እያሉ ሲቀልዱ ኖረዋል! እየቀለዱ ነው!
ብሔራዊ እርቅ ያስፈልጋል” የሚባለውን ሀሳብ ከሚቀበሉት መካከል ነበርኩ። በዚህ የአፓርታይድ ዘመን ከገዥዎቹ ጋር “መጎናበስን” መቀበል በእውነት ትልቅ ትግስት ይጠይቃል።  ገዥዎች እየገደሉ፣ እየዘረፉ፣ ሀገር እያቆረቆዙ፣… …”እርቅ ያስፈልጋል” እያሉ፣ ከእርቅ ይልቅ ማረቅን ስራዬ ብለው በመያዛቸው ተስፋ የቆረጠ ካለ አልፈርድበትም፣ እኔንም እንዳትፈርዱብኝ!
~ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በደማቁ ቀለም ደንግጎ ሀገሩ መልካም የምትሆንበትን ሀሳብ የፃፈና የተናገረ ሲታሰር፣ የሕዝብ ድምፅ የነበሩ የሚዲያ ተቋማት ታፍነው  ለራሳቸው ስልጣን ሲባል የሀገርን ስልጣኔ እጅግ ወደኋላ የጎተቱ፣
~ የመደራጀት መብትን ደንግገው በሕጉ መሰረት የተደራጀውን በሕገወጥ  አዋጅ በትነው መደራጀት  ለሀገር ይሰጥ የነበረውን መልካም እድል መና ያስቀሩ፣
~ሲቪክ ማህበራት ሕዝብን ማንቃት ሲጀምሩ፣ ማህበራቱን ዘግተው ሕዝብን አደንቁረው የገዡ፣
~ነፃ ገበያ በሕግ ተፈቅዷል ብለው፣ ነፃ ገበያን ለራሳቸው አድርገው፣ ሌላውን ከልክለው የሀገርን ንብረት በነፃ የራሳቸው ያደረጉ፣ ሕዝብን ያደኸዩ፣ የሐገር ሀብትን በዘመድ አዝማድ የመዘበሩ፣
~ምርጫ ብቸኛው መንገዳችን ነው ብለው፣ ሕዝብን ምርጫ ያሳጡ፣ ምርጫን ያረከሱ፣ ምርጫን ቅርጫ ያደረጉ፣  ለምርጫ ቀለም የተቀባ ጣቱን እንቆርጣለን ያሉ፣ ጣቱን ብቻ ሳይሆን አንገቱን የቆረጡ፣
~በሰላማዊ መንገድ መታገል ተፈቅዷል ብለው፣ በሰላማዊ መንገድ የጠየቁትን፣ የተጠየቀለትን ሕዝብ ሰላም የነሱ፣
~መብት ጠይቁ ብለው የመብት ጠያቂውን ወጣት ብልት ላይ ውሃ ያንጠለጠሉ፣ ብልቱን ያኮላሹ፣ ጥፍር የነቀሉ፣
~የውሃ ማማዋን ሀገር ሕዝብ የውሃ አገልግሎት እናቀርባለን ብለው፣ መብራት  እናደርሳለን ብለው 26 አመት ሙሉ የተበጀተውን የውሃ ሽታ ያደረጉ፣
~ታግለው በጣሉት ስርዓት ስኳር በግድ ውሰድ ሲባል የነበረን ሕዝብ “ስኳር እናቀርብልሀለን” ብለው 77ቢሊዮን  በጀቱን ቀርጥፈው፣ ሕይወቱን መራራ ያደረጉ፣
~ነርሲንግ፣ ኢንጅነሪንግ፣ አካውንቲንግ……የሚባል የትምህርት ክፍል መድበው፣ የሀገር ገንዘብ አፍስሰው ተማር ካሉ በኋላ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው አንድ ቀን ያልተማረውን ድንጋይ ፍለጥ፣ እንቁላል አስፈጥፍጥ ብለው የትውልዱን ተስፋ የፈጠፈጡ፣
~ የእምነት ነፃነት እናከብራለን፣ እናስከብራለን እንዳላሉ ቄስና ሸክን ለሕዝብ የመረጡ፣ ቤተክሕነትንና መስጊድን የረገጡ፣ መነኮሳትን ምንኩስና አውልቁ ያለ፣ ሸኮችን ያዋረዱ፣
~ሕዝብን በሚናገረው ቋንቋ “አሸባሪ” ብለው የፈረጁ፣ የዘር ጥቃት የፈፀሙ፣ በኖረበት ቀየ ቤት ንብረቱን ቀምተው ባይተዋር ያደረጉ፣
~ለሀገር ደሕንነትና ኢኮኖሚ እጅግ ጠቃሚ የሆነውን የባህር፣ ዳር ድንበር አሳልፈው የሰጡ፣ ድንግል መሬቷን በሲጋራ ዋና ሸጠው ለግላቸውና ለስልጣን መክረሚያ ያደረጉ፣
~ሕገ መንግስት አፅድቀናል ብለው፣ በ”ሕገ አራዊት”፣ በአዋጅ፣… …የገዙ፣ የሕግ የበላይነት እናሰፍናለን ብለው፣ ህግን መግዢያ ያደረጉ፣
~ታሪክን፣ ባህልን፣ እምነትን፣ ብልፅግናን፣ ተስፋን ነገን፣… ………የገደሉ እንደምን ይቅር ይባላሉ? እንዴት ከእነሱ ጋር መስማማት ይኖራል?
~ በቀደም “እርቅ” ብለው የተጎነበሰላቸውን አንገት አንቀው ማጎሪያ ያስገቡ “ሰዎች” ጋር እርቅ፣ ሽምግልና፣………እንዴትስ ይቻላል? እንዴትስ ይታሰባል?
~ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ ገዥዎቹ ፈፅመዋቸዋል።  ይህን ሁሉ ካደረጉት ገዥዎች ጋር እርቅ ያስፈልጋል የሚሉት አብዛኛዎቹ አካላት ሀገር ከዚህ የባሰ ችግር እንዳይገጥማት በማሰብ እንደሆነ ይገልፃሉ። ነገር ግን ባለፉት 26 አመታት “እርቅ” ያለ ሁሉ ወደታች ታርቋል፣ ተደፍቋል! ገዥዎችም በነጋታው ሀገርን ወደ ገደል አፋፍ ከመግፋት የተሻለ ተግባር አልፈፀሙም! “እርቅ ይውረድ” ስለተባሉ “እርቀ ሰላም” እንዲሆን አልሰሩም፣ ይባስ ብለው ጥላቻ፣ ይባስ ብለው መከራና ስቃይ አብዝተዋል!
~ አሁን እንደገባኝ “እርቅ ይሁን” የሚባለው በራሱ የተሳሳተ ሀሳብ ነው፣ የተጣላ እንጅ የተጠላ ይቅር በለኝ ብሎ በዳዩ እግር ለምን ይደፋል? የገደለ፣ የዘረፈ፣… …እንጅ የሟች ወገን ለምን እርቅን አጥብቆ ይለምናል?  “እንታረቅ” ብሎ ደም ሳይደርቅ የሚገድል ጋር እርቅ ምን ያደርጋል?
~ “ኧረ እርቅ!” የሚሉት ተበዳዮች ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ፣ እንዳትቆረቁዥ፣ እንዳትደኸኝ በማሰብ እንደሆነ ይገልፃሉ! ግን ሀገር ከዚህ በላይ ምኑ ይፈርሳል? ከዚህ በላይ እንዴት ይደከያል? እንዴት ትጎሳቆል?
~ አሁንም እስከገባኝ፣ ገዥዎቹ እርቅ ያስፈልጋል ስለተባሉ እርቀ ሰላም አልፈለጉም፣ ሀገርም ከማረቅ አልተመለሱም። ሰላም ያለውን “ፀረ ሰላም” ከማለት አልተመለሱም!  እርቅ፣ ፍቅር፣ ሰላም… …የሚባለው አልዳኛቸውም! ስለሆነም በሕግና በሕግ ብቻ ነው መዳኘት ያለባቸው! እየተበደለ “እርቅ” ከሚባሉ ይልቅ ለሰሩት ክፉ ሁሉ ክፉ እንደሚጠብቃቸው ቢያውቁ  ቆም ብለው የሚያስቡበት ይመስለኛል!
~”አትግደል፣ በቃ ከአሁን በኋላ አትግደል” እየተባሉ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፣ ግን እየገደሉ ነው! “የእስካሁኑ ሆኗል ከአሁን በኋላ አትመዝብር” ተብለው እየመዘበሩ ነው። “ወደኋላ መመለሳችን ይብቃ” ቢባሉም የኋሊቱን ጉዞ ቀጥለዋል! አልተማሩም! እኛም አልተማርንም! ላደረጉት ሁሉ መጠየቅ ነበረብን! መጠየቅ አለብን! ላደረጉት ሁሉ መጠየቅ አለባቸው! ለገደሉት ሁሉ መጠየቅ አለባቸው፣ ለዘረፉት ስባሪ ሳንቲም ሁሉ መጠየቅ አለባቸው! ይቅር ማለት መቅረት አለበት! “እርቅ” ከስህተቱ ለሚማር እንጅ ተበድሎ ይቅር በሚያደርግ ለሚቀልድ አይገባውም!  እርቅ መልካም ለሚያስብ እንጅ መልካም ያሰበን ለሚጠላ፣ ለሚያጠፋ አይገባም! ክፉዎች እርቅ ጊዜ መገዢያቸው ነው! እርቅ መቀለጃቸው ነው! እርቅን፣ ሰላምን… …ያረክሱታል፣ አርክሰውታል! “እርቅ… ……ቅብጥርጥስ” ቢሉ  አሁንም እየገደሉ፣ እየዘረፉ፣ እየዘለፉ……ለመሰንበት ነው!
Filed in: Amharic