ይበልጡኑ ነዳጅ አመላላሽ ቦቴ መኪኖችን እና ባለንብረቶችን የሚመለከተው ይኸው ጥሪ፣ ወደ ተግባር ተለውጦ በአገዛዙ ላይ ጫና እንዲያሳድር የሚመለከታቸው ሁሉ ሚናቸውን እንዲወጡም መልዕክት ተላልፏል፡፡ እንደ መረጃዎች ገለጻ፣ የነዳጅ ምርቶችን እንቅስቃሴ የማስተጓጎል ዘመቻው በትላንትናው ዕለት ማክሰኞ በይፋ ከተራዘመ በኋላ፤ ኦሮሚያን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ህዝባዊ ጥሪውን ተላልፈው ለመንቀሳቀስ የሞከሩ አንዳንድ ተሽከርካሪዎች ከህብረተሰቡ በደረሰባቸው ተግሳጽ እና ተቃውሞ ከድርጊታቸው መታቀባቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ አድማው በሰፊው እየተተገበረ የሚገኘው በኦሮሚያ ቢሆንም፤ ከሱዳን ነዳጅ ጭነው በመተማ በኩል ወደ አማራ ክልል የሚመጡ ቦቴ መኪኖች እንቅስቃሴያቸው በመገታቱ፤ አድማው በአማራ ክልል እየተተገበረ ስለመሆኑ አመላካች ነው ይላሉ የመረጃ ምንጮች፡፡
ለአንድ ሳምንት በተራዘመው በዚሁ የነዳጅ አቅርቦት የማስተጓጎል አድማ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍ ጥሪ ሲተላለፍ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በጥሪው መሰረትም በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በስልጣን ላይ የሚገኘውን አገዛዝ የማዳከም አንዱ አካል በሆነው በዚህ አድማ እየተሳተፉ ሲሆን፤ አድማው በትብብር መካሄዱ ደግሞ በአገዛዙ ላይ የሚደርሰውን ጫና ይበልጥ እንደሚያንረው ተገልጿል፡፡ ይኸው አድማ ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2010 ሲጀመር ዓላማው አድርጎ የተነሳው፣ ለንጹኃን ዜጎች እልቂት ምክንያት እየሆነ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተብዬ መቃወም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኮማንድ ፖስት የተባለው ቡድን አዋጁን ተገን በማድረግ በንጹኃን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ግድያ እና እስራትም የነዳጅ ማስተጓጎል አድማው በጽኑ ይቃወማል፡፡