>
5:13 pm - Saturday April 18, 2076

የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ታላቅነት (ጋሻው መርሻ)

መምህር፤ተመራማሪ፤ደራሲ፤ሀያሲ፤ፖለቲከኛ፤የሰብአዊ መብት ተሟጋች፤ጂኦግራፈር፤አምደኛ፤የሀገር ሽማግሌ እያሉ ህልቆ መሳፈርት ችሎታቸውን ከባህሩ እየቀዱ መዘርዘር ይቻላል፡፡ መስፍን ወልደ ማርያም የሰብአዊነት ከፍታን የተቆናጠጡ፤የዘረኝነት በሽታን የተሻገሩ፤የእውቀት ባህር ላይ የዋኙ፤አፍቅሮተ ንዋይ የማያውቃቸው፤መታበይ ያልነካቸው የኢትዮጵያውያን ሁሉ ኩራት ናቸው፡፡ ከስልሳ አመት በላይ ስለ ሰብአዊነት፤ስለ ፍትህ፤ስለ እኩልነት ያስተማሩ፤የጻፉ፤የተከራከሩ፤ብሎም በተግባር የኖሩ ታላቅ ሰው፤ የአፍሪካ ብሎም የአለም ኩራት ናቸው፡፡ አፍሪካ ካሏት ጥቂት በራሳቸው ሚዛን ላይ የሚቆሙ ምሁራን ጋር ትክሻ ለትክሻ የሚጋፉ ባለብሩህ አዕምሮ ፈላስፋ ናቸው ታላቁ ሰው መስፍን ወልደማርያም፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ግን በስራ እንጅ በግድ ‹‹የአፍሪካ ኩራት ነኝ›› በሚል የፕሮፖጋዳ ጎርፍ አይደለም፡፡
መስፍን ወልደማርያም ለኢትዮጵያ አምባገነኖች በሸንቋጭ ብዕራቸው ከመቀመጫቸው የሚያቁነጠንጡ የሽማግሌ ጎረምሳ ናቸው፡፡ በሳል በሆነው ትችታቸው ራቁትን የሚያስቀሩ ነገር አዋቂ ምሁር ናቸው፡፡ በዚህ ችሎታቸውም ሶስት አምባገነን ስርዓቶችን በፊት ለፊት የታገሉ አዛውንት ኢትዮጵያዊ ያደርጋቸዋል፡፡ ለገንዘብ ደንታ የሌላቸው፤ስልጣን የማያጓጓቸው፤ማወቅ እንጅ መታዎቅ የማይደላቸው ራሳቸውን ሆነው የኖሩ ጉምቱ ምሁር ናቸው፡፡ የሰዎች ክፉ የሚያስከፋቸው ሩህሩህ አንጀት የታደሉ በክፍለ ዘመን አንዴ የሚፈጠሩ አይነት ሰው ናቸው ትልቁ ሰው መስፍን፡፡
የትግራይና የወሎ ወገኖቻችን በርሃብ ሲቆሉ የንጉሱ ደንገጡሮች ለመሸፋፈን ይጣጣሩ እንደ ነበር ይታዎቃል፡፡ ይህን የተመለከቱትና ለሰብአዊነት ቅዲሚያውን የሚሰጡት መስፍን ወልደማርያም ስፍራው ድረስ ተጉዘው ርሃቡን የአይን ምስክር በመሆን ለንጉሱ የተማጽኖ ደብዳቤ በመጻፍ እንዲያውቁት አድርገዋል፡፡ በዚህ ብቻ ያላበቁት መስፍን ስለ ርሃቡና ችግሩ አንድ ጥራዝ በመጻፍ አለም እንዲያውቀው ያደረጉ ሲሆን እሱን ተከትሎ የአለም ህዝብ ወደ ርሃብተኞቹ አይኑን እንዲያዞር አድርገዋል፡፡ የአለም በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች ገቢ እንዲያሰባስቡና የሚዲያ ባለሙያዎች በአካል ተገኝተው ዶክመነተሪ እስከመስራት የደረሱት የመስፍንን ጽሁፍ እንደ መነሻ በመውሰድ ነበር፡፡ ፕሮፍ ስፍራው በደረሱ ጊዜ የተሰማቸውን እያለቀሱ ሲገልጹት ‹‹ሰው መሆኔ አስጠላኝ›› ይሉታል፡፡ ከተራበው ጋር አብረው ተርበው፤ ከተጠማው ጋር አብረው ተጠምተው ያዩትን ለንጉሱ በደብባቤ ሲገልጹ ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ ሰውን የተማጸንኩበት›› ኩነት ነው ይላሉ ኩሩው ሰው መስፍን፡፡
በተለምዶ ‹‹ያ ትውልድ›› የሚባለው እና ተቧድኖ በመገዳደል የሚታወቀው ክፉ ዘመን ነፋሱ ያላንገዳገዳቸው የጸና መሰረት ላይ ያረፉ ብርቱ ሰው ናቸው፡፡ የደርግን ስርዓት ፊት ለፊት የተሟገቱ፤ በጽሁፎቻቸው የሸነቆጡ፤ በመጨረሻም ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን መንግስቱን ሀ/ማርያምን ‹‹ስልጣንህን ልቀቅ›› ብለው የጻፉ አንጋፋ የመብት ተከራካሪ ናቸው ጠንካራው ሰውዬ መስፍን፡፡
‹‹ሰመጉን›› በገንዘባቸው የመሰረቱ እና ለህልውናው ሁሉ ነገራቸውን የሰጡ ታላቅነት የሚያንሳቸው ሰው መስፍን ወልደማርያም፡፡ ሰመጉን መሰርተው ወያኔ  በሰብዓዊነት ላይ ያደርስ የነበረውን ግፍና ሰቆቃ ያለምንም ፍርሃት ለኢንተርናሽናል ኮሚኒቲውና ለሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቶች ያጋልጡ የነበሩት ብርቱው ሰው መስፍን ናቸው፡፡ ከሰመጉ ጋር ተያይዞ በጣም ልብ የሚነካ ታሪክ አላቸው ጋሽ መስፍን፡፡ የኖርዌይ ዲፕሎማት ለሰመጉ ስራ ማስኬጃ አበድሯቸው የነበረውን ብር ምክንያት በማድረግ እጅ ለመጠምዘዝ ይፈልጋል፡፡ ይህ ያላስደሰታቸው እና ያስከፋቸው ኩሩው ሰው መስፍን ወልደማርያም ኮምጨጭ ባለ አነጋገር ‹‹እኛ ድሃ ነን!! ድህነታችን ግን ማንም እንደፈለገ እንዲያዘን አያደርገንም፤ከፈለግክ ገንዘብህ ይመለስልሃል በህልውናችን ላይ አንዳች አስተዋጽኦ ሊኖርህ ግን አይችልም›› ብለው መኪናቸውን ሽጠው ገንዘቡን ለመመለስ ያላመነቱ የሀገር ባለውለታ ናቸው መስፍን ወልደማርያም፡፡
                   መስፍን እንደ መምህር
አዲስ አበባ ዩንቨርስቲን በመምህርነት የተቀላቀሉት መስፍን የጂኦግራፊ ዲፓርትመንትን በማቋቋም፤ የመማሪያ ጹሁፎችን በማዘጋጀት፤አጋዥ ማቴሪያሎችን በማሰባሰብ ለትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከዳር እስከዳር በበቅሎ፤ በፈረስና በእግር በመዞር ያጠኑ ሲሆን ብሎም ከጥናታቸው በመነሳት የኢትዮጵያን ካርታ የሰሩ ‹‹ታላቅ›› የሚለው ቃል ሊገልጻቸው የሚያዳግተው የሀገር ባውለታ መስፍን ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጂኦግራፊ ዲፓርትመንት ውስጥ የእርሳቸው አሻራ ያላረፈበት ነገር ማግኘት ከባድ ነው፡፡ እንዲሁም በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ ጊዜ ቦታው ድረስ ሄደው በማጥናት እስካሁን ድረስ መረጃው ያላቸው ብቸኛው ሰው ናቸው ታላቁ ሰውዬ መስፍን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያየ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከ20 በላይ መጽሀፍት ሲያሳትሙ ያልታተሙትን መቁጠር ከባድ ብቻ ሳይሆን አንባቢንም ማሰልቸት ነው፡፡
ኤርትራውያን ሰብአዊነት በጎደለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ሲባረሩ ለምን ብለው የተቃወሙ፤ ዘረኝነትን የበጣጠሱ፤ የሰብአዊነት ሰገነት ላይ የተፈናጠጡ የታላቆች ሁሉ ታላቅ ሰው መስፍን ወልደ ማርያም፡፡
የሰመጉ ሊቀመንበርነታቸውን እንደጨረሱ ‹‹ቀስተ-ደመና›› የተባለውን የፖለቲካ ድርጅት በማቋቋም በድንዛዜ ተውጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ነፍስ የዘሩበት የፖለቲካ መሃንዲስ ናቸው፡፡ ምን አልባትም ቀስተደመና የተባለው ፓርቲ ህዝብ ወደ ማደራጀቱ ባይገባም የተበታተኑትን ድርጅቶች ወደ አንድ እንዲመጡ ትልቅ ስራ ሰርቷል፡፡ የኢዲሊው ታምራት ነገራ ‹‹የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ባቡር›› ሲል በጻፈው መጣጥፍ የነበራቸውን አስተዋጽኦ ፍንትው አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ጽሁፉን ማንበብ ተጨማሪ መረጃ ይሰጣል፡፡
                    መስፍን በአሁኑ ሰዓት
መሰልቸትን የማያውቁት ፕሮፍ በሚቀጥለው ሚያዚያ 16 2007 ዓ.ም 85ኛ አመት ልደታቸውን ያከብራሉ፡፡ በዚህ እድሜያቸው ፌስቡክ ላይ የሚጽፉ፤ ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ አምደኛ፤ መጽሃፍትን ራሱ ተይቦ የሚያሳትም፤ የፓናል ውይይት ተሳታፊና አስተማሪ የሆነ ሰው ከእርሳቸው ሌላ ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡
            ነብይ በሀገሩ አይከበርም
እንዳለመታደል ሆኖ ሀገራችን ዳቦ ለጠዬቃት ድንጋይ የምትሰጥ የወላድ መካን ናት፡፡ ስንት የለፉላትን ወደ ጠርዝ በመግፋት ያጠፏትን የምትሸልም የእንጀራ እናት፡፡ ቤት ንብረት ሳያፈሩ ከ60 አመት በላይ ለሀገራቸው መልካሙን ሁሉ ያደረጉት አዛውንቱ መስፍን በኪራይ ቤቶች ውስጥ በመጽሃፎቻቸው ተከበው ይኖራሉ፡፡ ምን አልባት የሌላ ሀገር ዜጋ ሆነው ቢሆን ኖሮ እንደ ታላቅ ቅርስ በጥበቃ በኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ሀገሩ ነብይ የማይከበርበት ኢትዮጵያ ነው፡፡ ዘራፊና ጩልሌ የሚነግስባት እውነተኛ ልጇቿ የሚሸማቀቁባት ኢትዮጵያ!!!
          ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፤
          የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!!!
ሰሞኑን በዚህ እድሜያቸው ማስፈራራትና ዛቻ እንደደረሳቸው ጽፈው አነበብኩ፡፡ እኔም የበውቀቱ ስዩምን ግጥም ተውሸ እንዲህ አልኩ፡፡
ትናንት ነብይ በሀገሩ አይከበርም፤
ዛሬ ነብይ በሀገሩ አይኖርም፤
ነገ ነብይ በሀገሩ አይፈጠርም፡፡
ክብር እውነት መርሃቸው ለሆነው ለጋሽ መስፍን፡፡ እውነት ማለት መስፍን መስፍን ማለት እውነት ናቸው፡፡
 ኦ አምላክ ሆይ ለእኝህ ጉምቱ ምሁር ብትችል ከማያልቀው የዘመን ትሩፋትህ ካልቻልክ ደግሞ ከእኔ እድሜም ቢሆን ቀንሰህ ስጥልኝ!!
         ክብር ለጋሽ መስፍን!!
         ረቢ ሆይ እናመሰግናለን!!! አንተ ትክክለኛ መምህር ነህ!!!
Filed in: Amharic