>

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማችንን -  ግብጾቹ ሊነጥቁን አሰፍስፈዋል (ዘመድኩን በቀለ  

ጉዳዩን እንደ ቀለል የሚታይ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። የኢትዮጵያ የ3 ሺ ዘመን ታሪክ ያለው ኢየሩሳሌም መሆኑን እንድታውቁ ይሁን ። 
~ በእኔ በኩል ግብጻውያን ኦርቶዶክሳውያን አባቶቼና ወንድሞቼ ናቸው ብሎ ለመቀበል መቸገሬን ስገልጽ ያለመሳቀቅ ነው ። እንዲህ አይነት የሌብነት ክርስትና ጥንቅር ብሎ በአፍንጫዬ ይውጣ ።  አከተመ ።
~ ” ባለቤቱን ካልናቁ ፤ አጥሩን አይነቀንቁ ። አለ የሀገሬ ሰው ” ደግሞም ” አያያዙን አይተው ጭቡጦውን ቀሙትም”  ይላል ይኸው የሀገሬ ሰው ። የግብጾቹ ሁናቴ እንደዚያ ይመስላልሸ።
~ በትናንትናው ዕለትም በጳጳስ የሚመራ ወረራ ፈጽመው በኢየሩሳሌም በሚገኘው ገዳማችን ላይ ጥፋት ፈጽመው መመለሳቸውም ተነግሯል።
 ~ እስራኤል ~ ኢየሩሳሌም ~ ኢትዮጵያ ~ ግብጽ ~ ኤርትራ ~ ተሃድሶ ~ አግአዚያን ። አራት ነጥብ።
~ በትናንትናው ዕለት በኢየሩሳሌም ጎልጎታ የሚገኘውን ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይዞታ በሆነው ዴር ሱልጣን ገዳማችን ” ወንድሞቻችን ” ብለን በምንጠራቸው ግብጻውያን የኮፕት ቤተክርስቲያን መሪዎች የታገዘ ወረራ መፈጸሙን ከስፍራው ከደረሱኝ ተንቀሳቃሽ የድምፅና ምስል እንዲሁም የፎቶ መረጃዎች ለመረዳት ችያለሁ ።
~ የግብጻውያን ትንኮሳ የቆየና የኖረ ነው ። ኢትዮጵያ መንግሥቷ የደከመ ሲመስላቸው አጋጣሚውን እየተጠቀሙ  የግል ንብረቶቻችንና ይዞታዎቻችንን በሙሉ ሲነጥቁን የኖሩ መሆናቸው ይታወቃል ። ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ መልኩ ዘርፈውናል ፣ ነጥቀውናል ፣ አባቶቻችንን ደብድበዋል ፣ አንገላተዋል ፣ የአስከሬን መውጪያ እንኳን አሳጥተው እጅግ የከፋ አረመኔያዊ ድርጊት ሲፈጽሙብን ኖረዋል ።
~ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በተለየ ቅድስና የሚታዩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሳይቀር የኢትዮጵያን ገዳማት ” ለመንጠቅ ” ቅሽሽ ሳይላቸው አልፈዋል ። ግብጻውያን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ የሚፈጽሙትን ግፍ ለሚያይ ሰው የግብጻውያን ክርስትና በአፍንጫዬ ይውጣ ነው የሚያስብለው ። አህዛብ እንኳ የማይሠሩትን ግፍ ነው ” እህታችን ” የምንላት እና የምናንቆለጳጵሳት የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በእኛ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት  በተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ የሚፈጽሙት ። የመጨረሻ አረመኔ ፣ ፓጋኖች ነው የሚመስሉኝ ። ክፉዎች ናቸው።
~ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በግብጽ መንግሥት የዲፕሎማሲ እርዳታ ጭምር የሚደገፍ ነው ። በመካከለኛው ምስራቅ ላለው ፖለቲካ እስራኤል የአረቡን ዓለም ተጽእኖ ለመቋቋም ይረዳት ዘንድ በአረቦች ዘንድ ተደማጭ ናት የምትባለዋን ግብፅን በእጅጉ ትፈልጋታለች። ግብፅም ለእስራኤል ድጋፏን በሰጠች ቁጥር አሜሪካ ለግብጽ የፖለቲካና የገንዘብ ድጋፍ በማድርገ ፍላጎቷን ታሟላላታለች። በዚህም ምክንያት እስራኤልና ግብጽ አንዱ ለአንዱ የሚያስፈልጉ ሀገራት ሆነው የሚመጋገቡ ሀገራት መሆናቸው ይነገራል ።
~ የግብጽ መንግሥት እስላማዊ መንግሥት ቢሆንም ፣ የግብጽ ኦርቶዶዶክስ ቤተክርስቲያን በኢየሩሳሌም ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ በየጊዜው ለምታደርገው አይን ያወጣ ዘረፋ ይረዳት ያግዛትም ዘንድ በፓርላማ ደረጃ ተዋቅሮ የተቋቋመ የዲፕሎማሲና የፋይናንስና እገዛ ጭምር የሚደረግለት ግብረ ኃይል አቋቁሞ ሌት ተቀን ይረዳቸዋል ። ስለዚህ ግብጾች በሰው ሰውኛው ይበልጡናል ማለት ነው ። ያውም አሳምረው ነዋ የሚበልጡን ። የግብጽ እስላም በሀገሩ ላይ ግብጻዊ ክርስቲያኖችን ይረድ ይግደል እንጂ የግብጽ ኦርቶዶክስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ መነኮሳትን ለመደብደብ ፣ ቅርስና ይዞታዎቿን ለመዝረፍ ለምታደርገው ግፍና ኃጢአት በጀት መድቦ ነው ሽንጡን ገትሮ የሚሟገትላት ።
~ በኢትዮጵያ በኩል ያየን እንደሆነ ምንም አይነት ዝባዝንኬና ትንተና ሳያስፈልገን ከዚህ በታች በምዘረዝራቸው ምክንያቶች ለጊዜው ተሸናፊዎች ነን ። ይኽ የግል ምልከታዬ ነው ።
፩ኛ ፦ በዋናነት ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ገዢ አካል ዋነኛ ግቡ ” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን” ለማጥፋት የተፈጠረ በመሆኑ ፣ ይኽንንም አሁን እየገዛን ያለውን የመንግሥታችንን ከልጅነቱ ጀምረው እስከ ጉልምስናው ለእጁ ቦንብና ክላሽ እየሰጡ ፣ እየረዱ ያሳደጉት ግብጻውያኑ በመሆናቸው ግብጻውያኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምንም አይነት ተቃውሞ እንደማይመጣባቸው አሳምረው ያውቃሉ ። እናም እንደፈለጉ ለመሆን ከህወሓት መራሹ መንግሥት ምንም የሚያሰጋቸው ነገር የለም ።
፪ኛ፦ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያን ገዳማት ለማስተዳደር ተሹመው በአሁን ሰዓት በዚያ የሚገኙት አካላት ከአንድ ብሔር የተውጣጡና ለፓርቲያቸው የሚሠሩ ፣ መስቀል የጨበጡና ቆብ ቀሚስ ያጠለቁ ካድሬዎች ናቸው የሚሏቸው እጅግ ብዙዎች ናቸው ። እነዚህ የመነኩሴ ካድሬዎች ደግሞ መቀጫውን በዚያው በእስራኤል ያደረገና የአሁኗን ኤርትራና የትግራይን መሬቶች አዋሕዶ ” ምድሪ አግአዚያን ” የተባለ አዲስ ሀገር ለመመሥረት መቋቋሙን በመናገር ላይ የሚገኘው እስከአሁንም በሀሳብ ደረጃ በፌስቡክ ላይ ውርውር የሚለው ፣ ወደፊት መሬት ረግጦ በተግባር ለመንቀሳቀስ እየጣረ ከሚገኝ አካል ጋር በጥምረት እየሠሩ መሆናቸውም ይነገራል ።
~ በተለይ አባ ፍሰሀ የሚባሉት መነኩሴ በዋናነት ከኤርትራውያኑ የተሃድሶ አባላት ጋር እየተገናኙ ይመክራሉ ፣ ያስተምራሉ ፣ ይቀሰቅሳሉ ፣ አብረውም ይቀድሳሉም ይባላል። ከዚህ በመነሳት በእስራኤል ዩኒቨርሲቲ የሚማር አንድ ኤርትራዊ ተማሪ የመመረቂያ ጽሑፉን ” በኢየሩሳሌም የሚገኙት የኢትዮጵያ ገዳማት የኤርትራ ሀብቶች ናቸው ። ” የሚል ድፍረት የተሞላበት የመመረቂያ ጽሑፍ እስከማዘጋጀት መደረሱም ይነገራል ። ይኽን ጉዳይ በእስራኤል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተከታትለው የመመረቂያ ጽሑፉን ውድቅ ቢያደርጉትም ተማሪው ግን መረጃውን ያገኘሁት ከአባ ፍስሀ ነው በማለት እንደገና በጉዳዩ ላይ እንደቀጠለ ጋዜጠኛ ዮሴፍ ይጥና በፌስቡክ ገጹ ሲመሰክር አይተናል።
~ ፓትሪያርካችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም ከኤርትራውያኑ የተሃድሶ ክንፍ አባላት ጋር በተደጋጋሚ በዝግ እየተሰባሰቡ እንደሚወያዩ እኔ በግሌ በደንብ አሳምሬ አውቃለሁ ። ከእነ በጋሻው ደሳለኝ ጋር በጥምረት የተሃድሶ እንቅስቃሴን ያራምዱ የነበሩ በእስራኤል የኤርትራን ቤተክርስቲያን እናድሳለን ባዮች ከፍተኛ ድጋፍ ከአቡነ ማትያስ እንደሚደረግላቸውም ይነገራል ።
~ አባ ፍስሀም ከፓትሪያርኩ በተቀበሉት መመሪያ መሰረት ከኤርትራ የተሃድሶ አካላት ጋር በድብቅ ሳይሆን በሃላል እየተገናኙ አብረው ይቀድሳሉ ፣ ይመካከራሉ ፣ ይወያያሉ ፣ ምን እንደወሰኑ ግን መድኃኔዓለም ባለቤቱ ይወቅ ።
~ ኢትዮጵያን ለመምራት አሁን እንደመስፈርት የተያዘው የገዢዎቹ ሃይማኖት ጉዳይ ነው ። አሁን እንደሚታየው ኢትዮጵያን መግዛትና መምራት የሚችለው ፣ የሚፈቀድለትም እንደ አቶ መለስ ዜናዊ ” ሃይማኖት አልባ ” እንደ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፕሮቴስታንት ፣ እንደ ዶር ዐብይ አህመድ ፕሮቴስታንት ፣ እንደ ሽፈራው ሽጉጤ ፕሮቴስታንትና ፣ እንደ አቶ ደመቀ መኮንን እስላም መሆን እንዳለባቸው ባልተጻፈ ህግ መደንገጉ ይነገራል ። እሱስ ባልከፋ የሚያሳዝነው ነገር ግን የሚሾመው ሁሉ ” ተዋሕዶ ” ላይ የጭቃ ጅራፉን የሚያሳርፍ መሆኑ ነው ።
~ እናም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአሁን ጊዜ በሰው ሰውኛው ከቤተ ክህነቱም ፣ ከቤተ መንግሥቱም በተባበረ ክንድ እየተደቆሰች ስለሆነ አቅመ ቢስ ደካማ ሆና ትታየኛለች ። ይኽ ግን በሰው ዘንድ ያለ ኃሳብ ነው ። እግዚአብሔር ግን እንደሰው ስላልሆነ በሰከንዶች ውስጥ ነገሮችን ግልብጥብጣቸውን በማውጣት ተአምራቱን ሊያሳየን ይችላል ። ይቻለዋልም ።
~ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ የህወሓት አገዛዝ የእስራኤል መንግሥት ” ቂም ” ቋጥሮ ለብቀላ የሚነሳበትን ዕድል ፈጥሮለት በግብጾች እንድንቀጠቀጥ በር ከፍቶላቸዋል ። በአሜሪካው ፕሬዝዳንት አማካኝነት ለተባበሩት መንግሥታት የቀረበውና የኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማነት ሀገራት እንዲያጸድቁ ያቀረቡትን የድጋፍ ድምጽ ” ኢትዮጵያ ” በተቃውሞ በመቆሟ በአሜሪካም ፣ በእስራኤልም ጥርስ ውስጥ ገብታለች ። የእስራኤሉ አምባሳደር በኢትዮጵያ በጣም አዝነናል ። ሌላው መደገፉ እንኳን ቢቀር ድምፀ ተአቅቦ ማድረግ ትችል ነበር በማለት በአደባባይ ቅሬታቸውን እስኪናገሩ ድረስ ማኩረፋቸው ታይቷል ። የአገዛዙ ዋነኛ ሥራ ኢትዮጵያን በሁሉ ዘንድ በቂም በቀል እንድትያዝ ማድረግ ስለሆነ ይኸው ተሳክቶለታል ።
~ በዚህ መሠረት ግብጻውያን ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ በትናንትናው ዕለት በኢየሩሳሌም ቀራንዮ በሚገኘው የኢትዮጵያ ገዳማችን ላይ ወረራ ፈጽመው ” ምን አባታችሁ ታመጣላችሁ ” እያሉ ሲዘባበቱብን ውለዋል ። ግብጻውያኑ ለጊዜው እውነት አላቸው ። ኢትዮጵያ መንግሥት ስለሌላት እንደፈለጉ የመሆን መብት ያላቸው ይመስላል ። እናም እንዳሻቸው ቢሆኑም አይፈረድባቸውም ።
~ በግብጽ እስላሞቹና ኦርቶዶክሳውያኑ በመንግሥት ድጋፍ አግኝተው የኢትዮጵያን ገዳማትና ይዞታ ለመውረስ በአንድነት ሲሠሩ ዕድለቢሷ ኢትዮጵያ ግን ፣ የወላድ መካኗ ኢትዮጵያ ግን ፣ አባቶቻችን ባዶእግራቸውን ፣ ከአንበሳ ፣ ከዘንዶ ፣ ከእባብና ጊንጥ ፣ ከወባና ከሽፍታ ፣ ከውኃም ሙለት ታግለው ከኢትዮጵያ እስራኤል ድረስም በእግራቸውን ሔደው በቅድስቲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም የያዙትን ይዞታችንን በቀን በፀሐዩ ፣ በብርሃን ስንነጠቅ ከማዘን ፣ ከመቆጨት በቀር ምን እንላለን ።
~ እንደ ዕድል ሆኖ የግብጽ ኦርቶዶክሳውያን ሃይማኖቱም ባይሆን የሚረዳቸው መንግሥት ሲኖራቸው ፤ የእኛዎቹ ግን የነበረንን ታሪክ እንደ ውጭ ወራሪ ኃይል ድምጥማጡን ለማጥፋት ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥተው የሚራወጡ ጉደኞች እየገዙን እንኖራለን ። እውነቱ ይኸው ነው ።
~ ወዮልሽ ቤተክህነት ፣ ወዮ ለሲኖዶስ ፣ ወዮ ለጳጳሳት ፣ ወዮ ወዮ ወዮ በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያኒቱንም ሆነ ሀገሪቱን ለመምራት ዕድል አግኝታችሁ ሳትጠቀሙበት ለቀራችሁ ። ወዮ ወዮ ወዮ ። እግዚአብሔር ሆይ ፣ የኢትዮጵያ አምላክ ሆይ ኧረ ለመሆኑ አንተስ ምነው ዝም አልክ ?
~ #ስጋቴ ~ ለወትሮው ግብጻውያን የሚበጠብጡንና ጠብ የሚፈጥሩት በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበረው የትንሳኤ በዓል ላይ የቅዳሚት ሥዑር ዕለት መብራት ይዘን በእኛ ይዞታ ላይ እንለፍ ሲሉ ነበር ። ከመላው ዓለም የሚመጡ ኢትዮጵያውያን በዕለቱ በስፍራው ስለሚገኙ እስከዛሬ ግርግር ከመፍጠር በቀር ምንም ለማድረግ አይችሉም ነበር። ዘንድሮ ግን ከትንሣኤ በፊት በዚህ መልኩ ግርግር ከፈጠሩ ዘንድሮ በተለመደው ቀን እንደድሮው የሚፈጥሩት ግርግር ካለ ምን ሊከሰት እንደሚችል ሳስበው ትንሽ ይዘገንነኛል ።
~ #ምስጋና ~ የፎቶና የሰነድ እንዲሁም የቪድዮ መረጃዎችን ያደረሱኝ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወንድሞች ናቸው ። በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ ባለው ሴራ ደስተኞች ያይደሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ናቸው ። ከዚህ የባሰ መረጃ በየጊዜው ያደርሱኛል ። እናም ከልቤ አመሰግናቸዋለሁ ።
~ድልና ትንሣኤ ለኢትዮጵያ ሀገሬና ለተዋሕዶ ሃይማኖታችን.!  ውድቀትና ጥፋት ፤ ለሁለቱም ጠላቶች ። አራት ነጥብ ።
¶ እነሆ ለዛሬ አበቃሁ.! ነገርግን እግዚአብሔር ቢፈቅድ ነገ ደግሞ እቀጥላለሁ ።
” እኔ ግን እላለሁ !!! እምዬ ኦርቶዶክስ አንቺ እናት ዓለም ፤ የእነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ፣ የእነ ቅዱስ አትናቴዎስ እና ቅዱስ ቄርሎስ የእነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ የእነ ቅድስት አርሴማ ፣ የእነ አቡነ ተክለሃይማኖት ፣ የእነ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ፣ የአባ ሳሙኤል ዘዋልድባና የአቡነ አረጋዊ ሃይማኖታቸው የሆንሽ ንጽህት ተዋሕዶ ሃይማኖቴ ሆይ ! ብረሳሽና ብከዳሽ ቀኜም ትርሳኝ፣ ትክዳኝም ። ባላስብሽና ባልሞትልሽ ምላሴ ከጉሮሮዬ ይጣበቅ ። ሳለጎበድድና ሳለከዳሽ እንድኖር አምላክሽ ይርዳኝ ። ይህን ባለደርግና ሳልጮህልሽ ዝም ብዬ ብሞት ስሜ ከህይወት መጽሐፍ ይደምሰስ ።
“ጌታ ሆይ! ከዚህ በፊት በሆነው ፤ አሁንም እየሆነ ባለው እና ወደፊትም በሚሆነው ነገር ፤ ክብሩን ሁሉ አንተ ውሰድ  አሜን. !
“ድንግል ሆይ እናቴ !  አዛኝቱ ዛሬም እንደትናንቱ ቅደሚ ከፊት ከኋላዬ “
ይህንንም ራሴው በእጄ ጻፍኩት ። 004915217428134 ደግሞ የቫይበር ፣ የቴሌግራም ፣ የኢሞና የኋትስአፕ መልእክቶችን የምቀበልበት የእጅ ስልኬ ነው ።
ሻሎም.!  ሰላም.!
ዘመድኩን በቀለ ነኝ.! 
መጋቢት 16/2010 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic