>

ኦህዴድ ጠቅላይ ሚንስትርነቱን ካላገኘ ይህ ሁሉ ዋጋ ከንቱ መሆኑ አይደለምን?!? (ዳዊት ሰለሞን)

ህወሓቶች በሁለተኛው ህንፍሽፍሽ ከተሰነጣጠቁ በኋላ በኢህአዴግ ውስጥ የነበራቸው ፊት አውራሪነት በመዳከሙ አፈር ልሰው የተነሱት እነመለስ ክፍተቱን ለመሙላት ከኦህዴድ ፣ብአዴንና ደህዴን ታማኝ ሆነው ያገኙዋቸውን ከፍተኛ ስልጣን እንዲቆናጠጡ ማድረጋቸው የበለጠ ከፍ ያለውን ስልጣን እንዲመኙ ሳያደርጋቸው አልቀረም ።
በኢህአዴግ ውስጥ አስፈሪና ምትክ አልባ ምስል መገንባት የቻለው መለስ በተፈጥሮ ሞት መወሰዱም ለህወሓት ትልቅ ቀውስ ለሌሎቹ ደግሞ የፍርሃት መጋረጃቸው የተቀደደበት ክስተት ሆኗል ።
ኦህዴዶች መለስን የሚተካው ሰው ከእነርሱ እንዲመረጥ ገፍተው ያደረጉት ትግል ባይሰምርም በክልላቸው ውስጥ ውስጡን ሲያሳድጉት የቆዮት ብሄርተኝነት የክልሉን ነዋሪ ማነሳሳት በመቻሉ የሆነው ሁሉ ሆኗል ።
ኦህዴድ ይህንን ሁሉ ያደረገው ዴሞክራሲ ፣ነፃ ምርጫ ፣ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች እንዲከበሩና ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ባይሆንም በኢህአዴግ ውስጥ ተገቢው ውክልና እንዲኖራቸውና አገሪቱን የመምራት ተራው የእነርሱ እንዲሆን የፈጠሩት ጫና ፍሬ ሊያፈራ ከጫፍ የደረሰ  ይመስለኛል።ህወሓትም ሆነ ሌሎቹ የኢህአዴግ ድርጅቶች የኦህዴዱን ዕጩ የግምባራቸውና የአገሪቱ መሪ በማድረግ ከመምረጥ የዘለለ ምርጫ የቀረላቸው አይመስለኝም ።
አቢይ የኃይለማሪያም ተተኪ ካልሆነም ኦሮሚያ የቀውስ ማዕከል እንደሆነች ትቀጥላለች።
በአማራ ክልል ተቃውሞ የነበረ ቢሆንም ተቃውሞው ብአዴንን ለስልጣን ለማብቃት የታቀደ አለመሆኑን ልብ ካልን ኢህአዴጎች የጀመርነውን ልማት ለማስቀጠል ሳንወድ በግድ አቢይን እናሳልፍ ማለታቸው አይቀሬ ይሆናል ።
እናስ
አቢይን ኦህዴድ በጠሚው ወንበር ቢያገኘው ለአገሪቱ ጠብ የሚያደርገው ነገር ይኖር ይሆን ?
በኦህዴድ እጅ የጣለን እድሜ ይስጠን !!!!
Filed in: Amharic