ጦማሪ ስዩም ተሾመ የካቲት 30/2010 ዓም በዋለው ችሎት ለመጋቢት 13/2010 ዓም የ14 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶበት አለመቅረቡ ይታወሳል። ጦማሪ ስዩም ክስ ያልተመሰረተበት፣ ዋስትናም ያልተሰጠው ወይንም ክሱ ያልተቋረጠ በመሆኑ ፖሊስ ሊያቀርበው ይገባ እንደነበር በተጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱ ፌደራል ፖሊስ ጦማሪ ስዩምን ያለቀረበበት ምክንያት እንዲገልፅ፣ ተጠርጣሪውንም እንዲያቀርብ ለመጋቢት 17/2010 ዓም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
ትናንት መጋቢት 17/2010 ዓም ጦማሪ ስዩም ተሾመ ፍርድ ቤት ያልቀረበ ሲሆን ፌደራል ፖሊስ ጦማሪ ስዩምን ከመደበኛው ፍርድ ቤት ውጭ በጊዜያዊ አዋጁ በተቋቋመ ፍርድ ቤት የማቅረብ መብት እንዳለው ገልፆ፣ የጊዜያዊ ቀጠሮ መዝገቡ እንዲዘጋ ጠይቋል። የፌደራል መጀመርያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በፌደራል ፖሊስ ጥያቄ መሰረት የጦማሪ ስዩም ተሾመን የጊዜያዊ ቀጠሮ መዝገብ እንደዘጋ ለማወቅ ተችሏል።
የካቲት 28/2010 ዓም የታሰረውን ጦማሪ ስዩም ተሾመ ፖሊስ የካቲት 30/2010 ዓም በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ከቀረበ በኋላ በቀጣይበሁለት ቀጠሮዎች አላቀረበውም።