
1. ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆኑ እስከዛሬ በነጻነት የተናገሯቸውን አሁን ይፈጽማሉ ወይስ ምን ያደርጋሉ?
2. ያላጸደቁትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምን ያደርጉታል? እንዴትስ አድርገው ያስከብሩታል?
3. ዶ/ር አብይን ሲያወግዙና ሲያጣጥሉ የነበሩት የሕወሃት ደጋፊዎች ቅስማቸው ቢሰበርም አሁንም አርፈው ይተኛሉ ማለት አይደለም። የዚህ መንግሥት ቁልፍና የፕሮፖጋንዳ ቀላጤ የሆኑትን እነዚህን ሰዎች እንዴት ያስተናግዷቸዋል?
4. ህወሃት ጨርሶ ለዚህ አልተዘጋጀም። የነገውን የመቀሌ ኮንፈረንስ አቅዶ የቆየበት እንጂ ዛሬ ማለዳ ያደረገው አልነበረም። ስለዚህ ዋንጫ ሊያነሳ ቢዘጋጅም ያልጠበቀው ነገር የደረሰበት መሆኑን መገመት አያዳግትም። ሁለት ድምጽ ብቻ ያገኙትን ደብረጽዮንን ይዞ ለዚያ ህዝብ አይዟችሁ አብይ ማለት ኃይለማርይም ነው ሊል አይችልም። የነገው ኮንፈረንስ ህወሓትና ደጋፊዎቹ ስለ አብይ ምን እንደሚያስቡ ፍንጭ እሚሰጡበት መሆኑን እሚታለፍ ነገር አይደለም።
5. አብይ ለዓመታት ያልተነቀሉትንና የብዙ ሰዎች ደም በእጃቸው እሚገኘውን የሠራዊቱና የደህንነቱን ሹሞች ይዘው መቀጠል አይችሉም። ይሄ እጅግ መሠረታዊና የአብይን ትክክለኛ ሥልጣን የሚያረጋግጥ ውሳኔ ነው።
6. ምክትሎች እና ልዩ አማካሪዎች እየተባሉ ከሥር ሥር እሚለጠፉ ታኮዎችን ማስወገድ ወይም ከነሱ ነጻ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
7. ኢህአዴግን ከህወሓት ነጻ ማውጣት፣ ክልሎች ሥልጣንና አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በብቃት መምራት አለባቸው።
8. እድል እንስጣቸው ወይም ለወያኔ ምንም እድል መስጠት አያስፈልግም በሚሉ ወገኖች መካከል ያለው ብርቱ ክርክር ይጠብቃቸዋል።
9. በኦሮምያ ክልል ለተነሱ ጥያቄዎች፣ ለተገደሉትና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ያላቸው ምላሽ ሌላው ትልቅ ፈተና ነው። እነ ለማ መገርሳ ያሉበት ኦህዴድም የልብ ልብ ካገኘ አብይን እንዲህ በቀላሉ ይቀበላቸዋል ማለት አይሆንም። ከእንግዲህ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የመጣ ት ዕዛዝ ነው እሚባል ነገር ከሞተም ቆይቷል።
10. ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ያላቸው ግንኙት ምን ይሆናል? የፖለቲካ ምህዳሩን ድጋሚ የታሰሩትን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ሰዎች ጨምሮ እስከን አንዳርጋቸው ጽጌ ድረስ ያሉትን የፖለቲካ ሰዎች በመፍታት ሥልጣናቸውን ማሳየት ይገባቸዋል። ዶ/ር አብይ የሽግግር ወይም የለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ይችላሉ ወይ እሚለው ጥያቄ ግን እጅግ ወሳኝ ነው።