>

ኢህአዴግ መግለጫ ሰጠ - ምን ገልጦ?

 

ደረጀ ደስታ

የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ሃላፊና ታጭቶ ተሸናፊው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ የነበሩ ሂደቶችን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
“በምርጫው ሂደት ላይ የብአዴን ተወካይ አቶ ደመቀ መኮንን ከምርጫ ሂደት መውጣት ከምርጫው ውጤት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።”
እስቲ ይህን አባባል ልብ ብላችሁ ተመልከቱት፣ “ከምርጫው ሂደት መውጣት ከምርጫው ውጤት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም” ማለት ምን ማለት ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ የተገመቱትና የተዶለቱት የአቶ ደመቀ በስተመጨረሻ መውጣት ውጤቱ ላይ ተጽእኖ አይኖረውም ብሎ ማሰቡ እማይመስል ነው። ድርጅቱ ምላሽ ከሌለው አሉባልታዎችን ማስተናገድ የግድ ሊሆን ነው። አቶ ደመቀ እንደተባለው “በችሎታዬ ተማምናችሁ ሳይሆን፣ እኔን መጠቀሚያ ቱቦ ማድረግ ፈልጋችሁ ነው…” ብለው ማንነታቸውን አስከብረው ከሆነ፣ ደመቀም ጊዜያቸን ጠብቀው ይደምቃሉ። ካልሆነም ሁሉንም ጊዜ ይፈታዋል። አቶ ሽፈራው፣ ደብረጽዮን አገኟት በተባለችዋ ሁለት ድምጽ መሳቂያ ሆኗል የተባለው ህወሓትን ስም ለመከላከል “ድርጅቱን ወክሎ የተወዳደረ እጩ የለም” ማለታቸውም ያሳፍራል። ደብረጽዮን ድርጅታቸውን ወክለው ባይወዳደሩ እንኳ የድርጅቱ መሪ መሆናቸው ሽንፈቱን ይበልጥ ያጎላዋል እንጂ አያሳንሰውም። መቸም ከድርጅቱ የላቁ ሰው ናቸው ተብለው ነው በሊቀመንበርነት የተመረጡት። ለማንኛውም አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በመግለጫው ከተናገሩት ውስጥ ፍሬ ነገር ያላቸው ጥያቄም እሚያጭሩም ነገሮች ቢኖሩ እነዚህ ነጥቦች ብቻ ይመስሉኛል።
• ዶክተር አብይ በአሰራሩ መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የሚሰየሙ ይሆናል። (አልቋል ማለት ነው)
• የምክር ቤቱ አባላት በሚስጥር ድምፅ በሰጡበት አካሄድ መፈፀሙን ገልጠዋል (በሚስጢር ከሆነ ሤራ የለም ቢኖርም ከሽፏል ማለት ነው)
• በምርጫው የቀረቡ እጩዎችም ግልጽ ጥቆማ ቀርቦባቸው ጥልቅ ግምገማ የተደረገባቸው እንደሆኑም አስረድተዋል። (ድርጅቱ ጥልቅ ግምገማ አካሂዶባቸዋል ማለት አምኖባቸዋል ማለት ነው፣ ሲነጋ ሌላ ነገር መቀባጠር አይሆንም) 
• ኢህአዴግ ከግንባር ወደ ፓርቲ ይቀየራል በሚለው ጉዳይ ላይም ለቀጣዩ የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ጥናት ቀርቦ ውይይት እንዲደረግበት አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቁመዋል። (አራት ድርጅቶች አንድ ሆነው ካስቸገሩን አንድ ሲሆኑብን ምን ልሆን ነው? ዛሬ ምን መጣ?)
ይልቁንስ ቀጣዩ መግለጫ ቢሆን ደስ የሚለን ሰሞኑን በድጋሚ የታሰሩት ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ሰዎችን የመፍታቱ ዜና ነው። በየትኛውም መመዘኛ የከፋ ግፍና ጭካኔ ነው!! እነሱም ሆኑ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች በአሰቸኳይ ካልተፈቱ እንኳን ለሽጉጤ፣ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ፣ ጆሮ መስጠት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ለሱም ጭምር መስሎኝ የፈለግናቸው።

Filed in: Amharic