>

ታሳሪዎቹ ለኢትዮጵያም ለዶ/ር አብይም ያስፈልጓቸዋል! (አህመዲን ጀበል)

ከየካቲት አስከ ሀምሌ 2007 በቃሊቲ ማረሚያ  ቤት በዞን 2 በነበረኝ ቆይታ ከሌሎች እስረኞች ተለይተን አንዷለም አራጌና ኢንጅነር መስፍን አበበ( አቶ መላኩ ፈንታ የቀድሞ የገቢዎች የጉምሩክ ሚኒስትርን ጨምሮ) ለ3 ከታሰሩበት በተለምዶ ነጩ ቤት የሚባለው ጠባብ ክፍል እየወጡ እኔ(አህመዲን ጀበል) ደግሞ ከዞን 2 እየወጣሁ በጋራ በዞን 2 የቤተሰብ መጠየቂያ ቦታ ከቤተሰብ ጋር እንገናኝ ነበር። ሌሎች እስረኞች ከ3 እስከ 6 ሰዓት ተገናኝተው ከጨረሱ በኃላ ለኛ በተፈቀደው 30 ደቂቃ ዉስጥ ከቤተሰብ ጋር እንገናኝ ነበር። ከነአንዷለም ጋር ቆመን ቤተሰቦች ተፈትሸው እኛ ዘንድ እስኪደርሱ ድረስ የአንዷለም ልጆች ለአባታቸው ካላቸው ናፍቆትና የማየት ጉጉት የተነሳ ከእናታቸው ተለይተው እየሮጡ ቶሎ አባታቸው ዘንድ ለመድረስ ይሽቀዳደሙ ነበር። እጅግ ከመሮጣቸው የተነሳ ታሳሪዎች ወዳሉበት መግባት ባይፈቀድላቸውም በሩን ከፍተው በሩጫ ይገቡ ነበር። እጅግ መድከማቸውንና ጉጉታቸውን በማየት አንዳንድ ፖሊሶች ልጆቹን ደፍረው ለመናገር እንኳ ወኔ ያጡ ነበር። በየካቲት 2010 አንዷለም አራጌ ጭምር እንደሚፈታ በኢቢሲ ስሰማ ወዲያው የታየኝ የአንዷለም ልጆች የሚሰማቸው ደስታ ነበር ። አባታቸው ተፈትቶ ልጆቹ  ደስታቸውን አጣጥመው ናፍቆታቸውን ተወጥተው ሳይጨርሱ ዳግም የአንዷለምን መታሰር ሲሰሙ ምን ስሜት በልጁቹ ላይ እንደሚፈጥር እስቲ አስቡት!  ከእስከንድር ጋርም በ2005 ከጥር 6 እስከ ግንቦት 9 ድረስ በዞን 3፣ በ6ኛ ቤት ዉስጥ በአንድ ቤት/ጊቢ አብረን ታስረናል። የእስክንድር ጽናትና የሀገር ፍቅር ስሜት ከፍ ያለ ነው። ተመስገን ደሳለኝ ጋር ከመታሰሬ ከቀናት በፊት በእስካይፒ ቃለምልልስ አድርገን ነበር። ቃለምልልሳችን በፍትህ ጋዜጣ ሳይወጣ ጋዜጣዋም ታፍና ቀረች። ከ2 ዓመት በሗላም ተመስገንም ታስሮ በቂሊንጦ ተቀላቀለን። በፍቃዱ፣ ማህሌት ፋንታሁንም ሆኑ ሌሎቹ በተለያዩ ጊዜያት እስርን ያስተናገዱ ናቸው። አቶ ታዬ ደንደኣ እና ሌሎች መሰል  ወንድሞችንና እህቶችን ማሰር ለኢትዮጵያም ሆነ ለአሳሪዎቹ አይፈይድም። ታሳሪዎቹ ለኢትዮጵያ በተለይም በብዙዎች በተስፋ ለሚጠበቁት ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ያስፈልጓቸዋል። ከኢህአዴግም ሆነ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ህዝቡ ከሚጠብቃቸው ጉዳዮች በጣም ትንሹና ቀላሉ መነኮሳትን ጨምሮ በሀይማኖት፣ በፖለቲካና መሰል ጉዳዮች የታሰሩትን ወገኖቻችንን በሙሉ ያለምንም ልዩነት በቶሎ መፍታት ነው። የፖለቲካ እስራት ይቁም። የታሰሩትም ይፈቱ!
Filed in: Amharic