>

ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው..."የወያኔ ተለጣፊ ሳንሆን ወያኔ ነን" (በዘውዱ ታደሰ)

አጋር የተባሉ ፓርቲዎች በኢህአዴግ ም/ቤት እንዲታዘቡ ቢጋበዙ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ወተዋል ።
ህወሓት ወዴት እየሄደ ነው ? ከብአዴን እና ከኦህዴድ ያጣውን ድጋፍ አጋር ከሚላቸው ፓርቲዎች ጋር ከጥምረት እስከ ውህደት የሚደርስ ሥራ እየሰራ እንደሆነ ይታውቃል ።
ዛሬ በበረከት ተፅፎ የተሰጣቸውን ምግለጫ አጋር /ተለጣፊ ፓርቲዎቹ እንደሚከተለው አቅርበውታል። አብዴፓ፣ ጋህዴን፣ ሶህዴፓ ፣ ሀብሊን እና ቤህዴፓ ፓርቲዎቻችንን ወክለን በኢህአዴግ ጉባኤ የክብር እንግዳ ሆነን በመገኘታችን ደስታችን የላቀ መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን:-
“ከዚህ በሃላ እዚህ ከተሰበሰበው አካል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪም፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ “የወያኔ ተለጣፊ” ብሎ እሚናገር ካለ በአደባባይ እናጋልጠዋለን። ምክንያቱ እኛ የወያኔ ተለጣፊ ሳንሆን ወያኔ ነን፣ ወያኔነት ደግሞ ለእኛ ቆራጥነት ነው ፡፡
ከዛ ባለፈ ፌደራላዊ አስተሳሰብም ጭምር ነው።ህወሓት ወያኔ ካልሆነ ከሃዲ ነው፡ ኦህዴድ ወያኔ ካልሆነ ከሃዲ ነው፡ ብአዴንም ደኤሄደንም እንደዛው፡እዚህ አዳራሽ ወያኔ አይደለሁም የሚል ካለ በህዝብ ፊት ቀርበን ከሃዲ ብለን እንጠራዋለን። እኛ ተለጣፊ ሳንሆን ወያኔ ነን፣ ለዛዉም አሁን ሃገር ማዳን የምንችል ወያኔዎች ነን። ኢትዮጵያን ማዳን የምንችለው እኛ ነን፣ እኛ ደግሞ በተለመደው አባባል አጋር ፓርቲዎች ብላቹህ እንዳትጠሩን ፣ በመጪው ነሃሴ በሚደረገው የፓርቲው ጉባኤ ከእናንተው ጋር ህብረት ፈጥረን አንድ ሀገራዊ ፓርቲ ለመመስረት ቁርጥ አቋም ላይ እንደርሳለን ፡፡
የአዲስ አበባን እና የድሬዳዋ ነዋሪዎችን የሚውክሉ አባላትም እንዲኖሩን እንሻለን ፡፡ኢትዮጵያን በዚህ ሰዓት ማዳን እምንችለው እኛው ነን፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣ የቤንሻንጉል የጋምቤላ የሃረሪ ፣ የድሬዳዋ እና የአዲስ አበባ ተወካዪችን በድርጅት መልክ ህብረት ፈጥረን በይፋ መንቀሳቀስ መጀመራችን እወቁልን ፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሆነን ዘንድ የመቀሌው ኮንፈረንስ አንድ አብነት ተደርጎ ይወሰድልን ፡፡ አሁን የተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር እና ካቢኒአቸው በቀጣዩ ስድስት ወራት የሚያሳዩትን የስራ አፈጻጸም በተመለከተ ገምጋሚዎቹ እኛም ጭምር መሆናችንን ከወዲሁ እናሳስባለን ። አሁን ባገኛችሁት መልካም አጋጣሚ ሁላችንንም በእኩል ድርጀታዊ መነጽር የማየት እድል ሰጥተናችኋል ።
ኢትዮጵያን መምራት ለአራት ድርጅቶችና ክልሎች ብቻ በርስትነት ይዛችሁት የነበረውን ታሪካዊ አጋጣሚ ከዚህ በኋላ እንዳከተመለት ልትገነዘቡ ይገባል፡፡ አሁን ኢህአዴግ መገንዘብ ያለበት ይህን አገር እምንታደገው እኛ ነን። አሁንም ኢትዮጵያን ከዉጭና ከዉስጥ ጠላት እየተከላከልን ያለነው እኛ ነን።
 ኢህአዴግ መምራት እንዳቃተው አዉቆ ኢትዮጵያችንን መታደግ እምንችለው እኛ እንደሆንን ተገንዝቦ ታሪካዊ ሃላፊነቱ እንዲወጣ እናሳስባለን። ተራ ካለ ተራው የኛ ነው፣ ቦታዉን የምንፈልገው ደግሞ ሃላፊነታችን ለመወጣት ከናንተ የተሻለ ቁመና ስላለን ነው” አዳራሹ ፍጥጥ ፍጥጥ፣ ቁልጭ ቁልጭልጭ። ተደመጠ ። አንዳንዶቹ ባለሥልጣናት ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው በሚል ስሜት ማንሾካሾክ ጀመሩ ፡፡
ሌሎች ደግሞ እነዚህ ጓዶች ከዚህ በኋላ መላሽ የላቸውም ሲሉ አጉተመተመ… ፡፡”
Filed in: Amharic