>

የዶክተር አብይ አህመድ ሲመተ ንግግርና የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ፈላጊ ኃይሎች ፍላጎት (ልዩ ርዕስ አንቀጽ-አግ7)

ዶክተር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ሲቀበሉ ያደረጉትን ንግግር አርበኞች ግንቦት 7:  የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በአንክሮ አዳምጧል፤ አጢኗል። 
ከህወሓት/ኢህአዴግ ድርጅታዊ ባህል ውጭ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የአገራችን ኢትዮጵያን ዝናና ክብር ከፍ የሚያደርጉ፤ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ፤ ፍቅርና ስምምነትን የሚሰብኩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።  “ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ የሚተጉ ልጆችን አፍርታለች። ልጆቿም ወደቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምና ፍትህ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ እድልኦ ለመላው ዜጎች ይደረስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ፤ ይደክማሉ” በማለት ሀገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ መስማት የናፈቀውን አባባል ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ንግግር ባለተሰማበት  ፓርላማ ውስጥ ተናግረዋል።
“አባቶቻችን በመተማ፣ በማይጨውና በካራ ማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆይዋት አገር አለችን። እኛ እድለኞች ነን። ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን። እኛ መነሻችንን እናውቃለን። በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ህዝብ ነን“ ሲሉ የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ አኩሪ ታሪክ አስታውሰዋል። በአገራችን ውስጥ ያለውን በጎ የማኅበረሰብ ትስስር ምሳሌዎችን በማንሳት አወድሰዋል።  ”ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር፤ የሁላችን ቤት ናት!” በማለትም በህወሓት አገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያዊያን የተራቡትን የእኩልነት ዜግነት መብት ሊከበር የሚችል መሆኑን ፍንጭ ሰጥተዋል። ከዚህም በላይ የሀሳብ ልዪነቶች መኖር ለቁልፍ ችግሮቻችን የተሻሉ የመትፍሄ ሀሳቦች መገኘት መሠረት ሊሆኑ እንደሚችሉ በመግለጽ “በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ።ስንደመር እንጠነክራለን” የሚል አዎንታዊ ኃይለ ላት ተናግረዋል። ዲሞክራሲን በሚመለከትም “እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲና ነጻነት ያስፈልገናል፣ ይገባናልም !” ብለዋል።
እነዚህን ተስፋ ሰጪ ንግግሮች ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት መስማት አጅግ በጣም የሚያበረታታ ነዉ። ሆኖም እነዚህ ተስፋዎች በንግግር ብቻ የምንሰማቸዉ ሳይሆኑ በቶሎ በተግባርም መተርጎም አለባቸዉና በቅርቡ አብረን የምናያቸዉ ይሆናሉ።
ዶ/ር አቢይ በፀጥታ ኃይሎች ሕይወታቸው ለተቀጠፉ ወገኖቻችን የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን ገልፀዋል፤ ይቅርታም ጠይቀዋል። ለወደፊቱም ተመሳሳይ የመብት ጥሰት እንዳይፈፀም ስለእርቅ ተናግረዋል፤ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እንደሚደረግ፤ በአጠቃላይ በህገመንግሥቱ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ መብቶች ሁሉ መከበር እንደሚኖርባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ባለፈዉ የካቲት ወር አጋማሽ የታወጀዉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የዜጎችን መሠረታዊ መብትና ነጻነት የሚቀማና በተወሰነ መልኩ ህገ መንግስቱንም የሚያግድ ነዉ፥ ስለዚህ ጠ/ሚኒስትር አቢይ “ህገ መንግስታችንን በአግባቡ መተግበር” አለብን ብለዋልና አርበኞች ግንቦት ሰባት አዲሱ ጠ/ሚኒስትር የዜጎች መሰረታዊ መብትና ነጻነት እንዲከበር ለማድረግ የሚያስችሏቸዉን ዕርምጃዎች በአጭር ግዜ ዉስጥ ይወስዳሉ ብሎ ተስፋ ያደርጋል።
“ዲሞክራሲ ያለነጻነት አይታሰብም። ነጻነት ከመንግስት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም። ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንዱ ሰው የተፈጥሮ ጸጋ እንጂ” በማለት ዶክተር አቢይ አህመድ የገለጹት ሰፊ ተቀባይነት ያለው ጽንሰ ሀሳብ እንዴት ተግባራዊ ሊደረግ እንደታሰበ አርበኞች ግንቦት 7  ማወቅ ይሻል። ዲሞክራሲ ያለነፃነት የማይታሰብ መሆኑ የአርበኞች ግንቦት 7 እምነትም ነው፤ የሚታገለውም ይህ እምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ነው።  እነዚህን ነጻነቶች ሲረግጥ የኖረው አገዛዝ እና የፓለቲካ ድርጅት ነጻነትን በማስከበር ሂደት ውስጥ ምን ዓይነት አስተዎጽኦ ሊያደርግ እንዳቀደ እና ለዚህ ስላደረገው ድርጅታዊ ዝግጅትም በቂ መረጃ ሊኖረው ይሻል።
ዶ/ር አቢይ አህመድ “ኢትዮጵያ የጋራችን፣ የኛ የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉም ድምጽ የሚሰማበት፣ ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን” ያሉት በምን መንገድና  በማን ለመፈጸም እንዳሰቡ በሚወስዷቸው ተከታታይ እርምጃዎች ማየት እንሻለን።
በሰላም፣ ማኅበራዊ መግባባትና  ፍትህ ረገድ የተናገሯቸው ቁምነገሮች ኢትዮጵያዊያን መስማት የሚልጓቸው ነገሮች ናቸው። በአጠቃላይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያን ችግሮች በጥሩ ሁኔት ዘርዝረዋል። በቀጣይ ንግግሮችና በተለይም በተግባር በሚሰሩ ስራዎች የእነዚህ ችግሮች መፍትሄና በአጠቃላይ አገራችን በሳቸዉ አመራር የምትሄድበትን አቅጣጫ ያሳያሉ ብለን እንጠብቃለን።
 አርበኞች ግንቦት ግንቦት 7  ለሚከተሉት ጥያቄዎች ምላሽ ይሻል
1. ለመሆኑ ዶ/ር አቢይ አህመድ እያሰቡት ያለው ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ ነው ወይስ ጊዜዓዊ ማስታገሻዎችን ነው?
2. የዶ/ር አቢይ ለውጥ የመጨረሻ  ግብ ምንድነው? የኢትዮጵያን ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ማድረግ ወይስ ኢህአዴግን ከቀውስ ማዳን?
3. በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የህወሓት/ኢህአዴግ ሚና ምንድነው? የችግሮቹ ፈጣሪ የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ እንደምን የመፍትሄ  አካል መሆን ይቻለዋል?
4. በለውጡ ሂደት ውስጥ ከህወሓት/ ኢህአደግ ውጭ ያሉት አካላት ሚና  ምንድነው? በለውጡ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ያላቸው መተማመኛስ ምንድነው?
5. የኢትዮጵያ ሕዝብ የለውጡ ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጠው እንዴት ነው?
በአርበኞች ግንቦት 7 እምነት የለውጡ ግብ መሆን ያለበት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ የተከበረበት ሀገር እንዲኖረው ማስቻል፤ ማለትም የኢትዮጵያን ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ማድረግ መሆን ይኖርበታል። አርበኞች ግንቦት 7 ወደዚህ ግብ የሚወስዱን  ጥረቶች ሁሉ ይደግፋል።
የዶ/ር አቢይና ባልደረቦቻቸው ጥረት የኢትዮጵያን ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ከሆነ አርበኞች ግንቦት 7 አጋራቸው ነው። እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ፍትህ ማስፈን የአርበኞች ግንቦት 7 ግብ ነው። ወደዚህ ግብ የሚያቀርቡ ጥረቶች ሁሉ የአርበኞች ግንቦት 7 ትግል አካላት ናቸው። ይሁን እንጂ ከፍላጎቶች ባለፈ ተጨባጭ የተግባር ጥረቶችን ማየት ይሻል።
በዚህም መሠረት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካቢኔያቸውን እንዳቋቋሙ 
1. ኢትዮጵያ ዉስጥ በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መብቶችና ነጻነቶች በሙሉ መከበራቸዉንና ባጠቃላይ ህገ መንግስቱ መከበሩን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፤ ይህ ደግሞ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለበትና ሀገሪቱን በሙስና የተጨማለቁት ወታደራዊ መሪዎችና የደህንነት አካላት ሙሉ ለሙሉ በሚቆጣጠሩት ሀገር የሚሆን አይደለምና የመጀመሪያ ስራቸው የሚሆነው ይህንን ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት ነው። የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ሲባል ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ያጠቃልላልና ጓዳችን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ሊለቀቁ ይገባል፤ ለወደፊቱ ሰዎች በአመለካከቸው ምክንያት እንደማይታሰሩና ስቃይ እንደማይደርስባቸው ተቃማዊ ዋስትና ሊሰጥ ይገባል፣ ይህ እርምጃ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር በንግግራቸው የተናገሩትን በተግባር ለማዋል ያላቸውን ቁርጠኝነትና እንዲሁም ሕዝባዊ ትግልም ወደ ለውጥን ተግባራዊ ወደማድረግ አቅምም ለመቀየር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያጠቃልላል።
2. ከህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነን ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር መመራት በሚኖርባቸው መንገዶች ላይ በህጋዊ መንገድም ሆነ ከአገዛዙ ህጎች ውጭ እየተንቀሳቀሱ ካሉ የፓለቲካና የሲቪል ማኅበራት ጋር  መምከር መጀመር ይኖርባቸዋል፣
3. አርበኞች ግንቦት 7፣ የዶ/ር አብይ የመጀመሪያ ንግግር የተለያዩ ጥቅምና ፍላጎት ያላቸውን ኃይሎች (ለውጥ ፈላጊውን ሰፊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፤ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚጥሩና ቢያንስ ሀገሪቱን ለማተራመስ ጊዜያዊም ቢሆን አቅም ያላቸውን በድርጅታቸው በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ኃይሎችና ከነኝህ ጋር በመተባበር ሀገሪቱን ሲግጡ የቆዩ ዘራፊዎች) ለማማለል ተብሎ የቀረበ ጥቅል አቅጣጫ አመላካች ንግግር መሆኑን ይገነዘባል። ስለዚህም በዚህ አይነት ንግግር ሁሉንም ያገሪቱን ችግርና ይህንን የሚቀርፉበትን ተጨባጭ የፖሊሲ እርምጃዎች ይዘረዝራሉ ብለን አልጠበቅንም። ዶ/ር አቢይ በንግግራቸዉ ላይ ብዙ ነገሮችን አሳይተዉናል፥ ሆኖም አንድን ሀሳብ በንግግር ማቅረብና በተግባር መተርጎም አንዳንዴ በተለይም በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ ሊሆን ይችላልና አዲሱ ጠ/ሚኒስትር የተናገሯቸዉን ንግግሮችና ያቀረቧቸዉን ሀሳቦች በተግባር ለመተርጎም ያላቸዉ ቁርጠኝነት የወደፊቱን አቅጣጫ ያሳያል የሚል እምነት አለን። ዶ/ር አብይ የለውጡን ኃይል ይዘው ለመራመድ ከፈለጉ ያላቸውን አጭር ግዜ ከአሁኑ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይህንን ካላደረጉ ወይም ግዜ በወሰዱ ቁጥር ለውጡን ለመጎተትና ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎችን ጉልበት ነው የሚያጠናክሩት። ከዚህ በተጨማሪ ተግባር በዘገየ ቁጥር የለውጥ ፈላጊውን ኃይል ትዕግስት ተሟጥጦ ያልቅና ለዚህ ያደረሳቸውንና በእርግጥም ለሚወስዱት የለውጥ እርምጃ ጉልበት ሊሆናቸው የሚችለውን ኃይል ያጣሉ። ይህ ደግሞ ለሳቸውም፤ ለሀገሪቱም አይበጅም።
አንድነት ኃይል ነው!!!
                ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!
Filed in: Amharic