
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አሁንም ማስተዋል ያለባቸው ነገር ያለ ይመስለኛል። ዛሬ የሶስተኛውን የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ጥሪ ሰምተዋል። አራተኛው ላይ ሊኖሩም ላይኖሩም ይችላሉ (ዘላለም አይኖርም)። ከሳቸው በኋላ ለሚረከበው ሰው ስራ ቀንሰውለት ቢሄዱ መልካም ቢሆንም ዋናው ነገር ግን የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች እያጡት ያለው ሰላም እና የቀውሱን ገሃዳዊ እና ድብቅ ኪሳራዎች ማስላት አለባቸው። በነጻነት ትግሉ ወቅትም ተመሳሳይ ጠንካራ አቋም ይዘው “መጀመሪያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከኤርትራ ይውጡና እንደራርደራለን” የሚል ክችች ያለ አቋም ይዘው ነበር። በኋላ ግን መደራደር አልቀረም። አሁንም ለሰላማዊ ድርድር “መጀመሪያ የባድመን ውሳኔ ተቀብላችሁ ዉጡልንና” ነው።
የድንበር ችግሮቻቸውን ወደጎን አስቀምጠው ሰላማዊ ግኑኙነት ላይ ያሉ አገሮች ብዙ ናቸው። ቻይናና ህንድ ከብዙ ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ወስን ሳይካለል ግኑኙነታቸውን ቀጥለዋል። ሩሲያን ጃፓንም ሶቪዬት ሕብረት በያዘቻቸው የጃፓን ደሴቶች ዙሪያ ያለባቸውን ችግር ወደጎን ትተው ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ግኑኙነታቸውን ቀጥለዋል። ለኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ለመደራደር በር መክፈት የባድመን ጉዳይ መተው ማለት አይደለም። ማንም የኦኢትዮጵያ መሪ እንደፈለገው የሚፈታው ጉዳይም አይደለም። ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ መሪ እንዲህ አይነቱን ጉዳይ የሚፈታው ከክልሉ ጋር እየተወያየ ነው። በዚህ ሁኔታ ደግሞ የትግራይ ፓርቲ ከሆነው ሕወሃት ጋር ነው። ህወሃት ደግሞ ከሕዝባዊ ግምባር ሓርነት ኤርትራ ጋር ያለው ቂም አዘል ቁራሾ፡ የትግራይ ሕዝብ እይታ እና ሊውሎችም ጉዳዮች ግምት ውስጥ ሲገቡ ሁኔታውን የተወሳሰበ ስለሚያደርገው ፕሬዚደንት ኢሳያስ ይህን ግምት ውስጥ ሊያስገቡት ይገባል። ድርድሩ ቢጀመር ግን ብዙ የተሻሉ ነገሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እሳቸው ባይፈቱት ቀጣዩ የኤርትራ መሪ ጉዳዩን በተለየ መልክ ሊፈታው መቻሉ አይቀርም። አለም እየተለወጠ ነው። ድርድር ዘመናዊው ደም አልባ የጦርነት መሳሪያ ነው።
የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኤርትራና ኤርትራውያን ያለውን በጎ እይታ ኤርትራ ልታተርፍበት ይገባል። ኢትዮጵያም እንዲሁ። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እጅዎን ይዘርጉ። የሚያጡት ነገር የለም። ጊዜው አሁን ነው። ቀጣዩ የኢትዮጵያ መሪ ምን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል መገመት አይቻልም። ዘመኑ ሌላ ነው አብይ ጥሩ እድል ነው።