ዓይኖች ሁሉ ወደ ዶ/ር አቢይ ያያሉ
******
«እኛ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞቢትዮጵያ እንሆናለን» የሚለው የጠ/ም ዶ/ር አቢይ አህመድ ንግግር የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ቀልብና ልብ የሳበ መሆኑን ከቪኦኤና ከሌሎች ሚዲያዎች አስተያየት መረዳት ተችሏል፡፡
ቪ ኦ ኤ በዛሬው ፕሮግራሙ ከመቀሌ ባስተላለፈው ፕሮግራም የትግራይ ተወላጆች ለጠ/ምኒስትሩ ያላቸውን አስተያየት የሰጡት ከሁለት ቀናት በፊት ከተደመጠው የተቃውሞ ድምጽና አስተያየት እጅግ በተለየ ሁኔታ በድጋፍና በተስፋ የተሞላ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
የመቀሌ ነዋሪዎች በሚደንቅ ሁኔታ በጠ/ምኒስትሩ የተገለስጸው የኢትዮጵያዊ አንድነት ጉዳይ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳገኘ ከተደመጠው አስተያየት መረዳት ተችሏል፡፡
የትግራይ ነዋሪዎች የአንድነትን አገላለጽ፤ ተቃዋሚን የገለጹበት ተፎካካሪ አገላለጽ እንደተወደደላቸውና ጠ/ምኒስትሩን ለመደገፍ እንደተነሳሱ ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ በተካሄደው አስተያየት የመሰብሰብ ሙከራ ቪ ኦ ኤና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን በተስፋ፣በጉጉት እና በአድናቆት የተሞላ አስተያየቶችን ድምጽ ሲያተጋቡልን ማድመጥ ችለናል ፡፡
የክቡር ጠ/ም ዶ/ር አቢይ አህመድ ንግግር በተለይም ስለ ግል እናታቸውና ሴቶች የገለጹበት አገላለጽ፣ዘረኝነትን በተጠየፈና ብሎም ሀገራዊ አንድነትንና እኩልነትን በኢትዮጵያዊነት ስር የተገለጸው አገላለጽ የንግግራቸው አስኳል እንደሆነ ከአስተያየት ሰጪዎቹ አንደበት መስማት ተችሏል፡፡
የ42 ዓመት አፍላ ጎልማሳና የሶስት ልጆች አባት የሆኑት ዶ/ር አቢይ አህመድ ሀገራችን ካለችበት እጅግ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች አንጻር እጅግ ከፍተኛ ሃላፊነትና ስራ የሚጠብቃቸው ቢሆንም በእሳቸው ላይ ተስፋውን ጥሎ በከፍተኛ መነቃቃት ተግባራዊ እርምጃ እየተጠባበቀ ያለው ኢትዮጵያዊ ወገኔ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካን፣የካናዳ መንግስታትና የአውሮፓና የአፍሪካ ህብረትም ጭምር እንደሆነ ማወቅ ተችሏል፡፡
አንድ ወዳጄ ጠ/ም ዶ/ር አቢይ ኢትዮጵያዊው ኦባማ ናቸው ስትል የገለጸችልኝ ሲሆን የእሷን አስተያየት የሚጋሩ ሰዎችም ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ማየት ችያለሁ፡፡
ለሰባት ዓመታት በከርቸሌ ሲማቅቅ የነበረው የ18ዓመት ፍርደኛ ጋዜጠና እስክንድር ነጋ በህዝባዊው ትግልና መስዋእትነት በቅርቡ ከተፈቱት ውስጥ አንዱ የነበረ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ግን በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤት በተዘጋጀ ፓርቲ ላይ ተይዘው ከታሰሩ በሃላ ዛሬ በእለተ ሐሙስ እሱና 11ሰዎች ምሽት ላይ ተፈተዋል፡፡
እስክንድር ለቪ ኦ ኤዋ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ስለ ጠ/ም ዶ/ር አቢይ አህመድ ሲናገር «እኔ ብቻ ሳልሆን ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብና ብሎም የዓለም ህዝብ ተስፋ በጣለባቸው ዶ/ር አቢይ አህመድ አመራር ታላቅ ተስፋ ጥያለሁ » ሲል ተናግሯል፡፡
«እኔ ከኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ ሌላ አቋም አይኖረኝም » ያለው እውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሀገሪቱ ያለችበትን ውስብስብ ችግር ዶ/ሩ በተቻላቸው መጠን ይፈታሉ ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጾ «የሰጡንን ታላቅ ተስፋ በተግባርም ያሳዩን ዘንድና በተለይም በቅድሚያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በማንሳት፣የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት እንደጂምሩ እንጠብቃለን» ሲል ተናግራል፡፡
በእለተ ሰኞ በህማማቱ የመጀመሪያ ቀን ከኢትዮጵያ ፓርላማ የተደመጠው የዶ/ር አቢይ ንግግር ንዝረትን በመፍጠር ታላቅ ተስፋንና መነቃቃትን በኢትዮጵያዊያን ዘንድ መፍጠር መቻሉን ማወቅ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ምን ያህል በሀገር ፍቅር ያበዱና ያንንም ፍቅር በማጣታቸው ምን ያህል ሲቃትቱ እንደነበር የክቡር ጠ/ምኒስትሩ ዶ/ር አቢይ አህመድ ድንቅና ታሪካዊ ንግግር ምስክር ሆኗል ማለት ያስችሏል፡፡
ጠ/ምኒስትሩ በሚደንቅ ሁኔታ 35ደቂቃ በፈጀው ንግግራቸው 39ግዜ የኢትዮጵያን ስም በፍቅር መጥራታቸውን የኢሳቱ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና የወርድ አፕ መቁጠሪያ ተጠቅሞ ማረጋገጡን የገለጸ ሲሆን ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም ደግሞ በ40ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይህን መሰል ሁለገብ ንግግር ያደረገ መሪ ዶ/ር አቢይ የመጀመሪያ ናቸው ብለዋል፡፡፡
ዓይኖች ሁሉ ወደ ዶ/ር አቢይ ያያሉ፣ ጆሮዎች ሁሉ የዶ/ር አቢይን ንግግር አቅንተው ይጠባበቃሉ፡ ከተስፋ ሰጪ ንግግራቸው ቀጥሎ ተግባር የሚናፍቁም ቁጥር የትየለሌ ሆኗል፡፡
ሆኖም የጠ/ምኒስትሩ ቀኝ እጅ ክቡር አቶ ለማ መገርሳ «ይህ በክፍተኛ ትግል የተገኘ ታላቅ ህዝባዊ ድል ነው» በማለት የዶ/ር አቢይን ወደ መሪነት መምጣት ገልጸው «ይህ ታላቅ ለውጥ ጅምር እንጂ ፍጻሜ አይደለም፡፡ ሁላችንም ይህን ለውጥ መጠበቅና መደገፍ አለብን ሲሉ » አስገንዝበዋል፡፡
ታላቅ ተስፋ የተጠላበት የጠ/ም ዶ/ር አቢይ ንግግር ተተግብሮ ይታይ ዘንድ አሁንም ሆነ ነገ የመላ ኢትዮጵያዊያን ድጋፋዊ ትግልና ሃይል እንደሚያስፈልጋቸው ሁላችንም ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል፡፡
ሕዝባዊው ትግል የጀመረውን የለውጥ ትግል ጠ/ም ዶ/ር አቢይን ባካተተ መልኩ በማፋፋም ተስፋችንን እውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ!!