>

 ሩጋ አሻሜ - ጉራጌዎች በአሮጌይቱ ኢትዮጵያ በንግድ ታዋቂነትን እና ከፍተኛ ተዋናይተን እንዲጎናፀፉ ያስቻሉ ባለውለታ! (ብሩክ አበጋዝ)

የዛሬን አያድርገውና ቀደም ባለው ጊዜ ከኢትዮጵያ የተለያዩ ነገዶች በተለየ ጉራጌዎች በንግድ እንዴት ታዋቂ ሊሆኑ ቻሉ ብላችሁ አልጠየቃችሁም?
.
ጉራጌዎች ለምን ከሌላው ማህበረሰብ በተለየ በሰፊው የንግድ ሥራ ላይ ተሰማሩ? አምባሳደር ዘውዴ ረታ ስለዚህ ጉዳይ እንደሚከተለው ያብራራሉ። በተጨማሪም የወሎዬዎች እና የትግሬዎችም ከሌላው ነገድ በተለየ በንግድ ላይ ያላቸው ሻል ያለ ተሳታፊነት ከሚቀጥለው ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው።
.
. . . . ጠላት [ጣልያን ለሁለተኛ ጊዜ] ድል ሆኖ የኢትዮጵያ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ፤ በአዲስ አበባ እና በየጠቅላይ ግዛቱ ባሉት ዋና ዋና ከተሞች ከየመን እየፈለሱ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ዓረቦች፤ ኪዎስኮች በብዛት እያቋቋሙ ለየሠፈሩ ነዋሪ ሕዝብ የሸቀጣ ሸቀጥ ችርቻሮ ንግዳቸውን አስፋፍተው ይኖሩ ነበር። [እንግዲህ በዚያ ዘመን ዓረቦች ተቸግረው ወደ ኢትዮጵያ እየተሰደዱ የመከራ እና የችግር ጊዜያቸውን በኢትዮጵያችን ያሳልፉ ነበር ዛሬ ደግሞ በተቃራኒው ነው]። ኢትዮጵያውያንም ይህን በየሰፈራቸው የተመሰረተውን ንግድ “የዓረብ ቤት” እያሉ በመጥራት ለዕለት ኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ዘይት፣ ስኳር፣ ጨው፣ ቅመማቅመም፣ ሻይ፣ ቡና፣ ክብሪት፣ ሻማ፣ ወዘተ የመሳሰሉትን ሥለሚገዙ፤ የዓረቦች ንግድ እጅግ እየተስፋፋ ሄደ።
.
ይህን የመሰለው የንግድ ሥራ ኢትዮጵያውያንን በገዛ አገራቸው እጅግ የሚጎዳቸው መሆኑን የተገነዘቡት አቶ መኮነን ሀብተወልድ፣ እሳቸው በሚመሩት በንግድ ሚኒስቴር ውስጥ ሰፊ ጥናት ተደርጎ አንድ መፍትሄ እንዲገኝለት ልዩ ኮሚቴ አቋቋሙ። የአቶ መኮነን ሀብተወልድ ጭንቀት እና ስጋት፣ የውጭ ዜጎች የሆኑት ዓረቦች፣ የኢትዮጵያውያን ቀጥታ መብት የሆነውን የየመንደሩን የችርቻሮ ንግድ በሙሉ ይዘው ከበርቴ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ ዓረቦች በሚኖርባቸው ቀበሌዎች ወጣት ሴት ልጆችን በገንዘብ እየደለሉ እንደ ሚስት በመያዝ ብዙ ልጆች ካስወለዱ በኋላ፤ በመጨረሻ ለወለዷቸው ልጆች አንዳች የመኖሪያ ገንዘብ ሆነ የመቋቋሚያ ንብረት ሳያዘጋጁላቸው፤ ያከማቹትን ጥሬ ገንዘብ ይዘው የንግዳቸውን ድርጅት ለሌላው ዓረብ ወገናቸው አስተላልፈው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ነው።
.
እነዚህ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ከዓረቦቹ የተወለዱ ህፃናት፤ አባቶቻቸው ባዶ ሜዳ ላይ ጥለዋቸው ሲሄዱ፤ በየተወለዱበት ሠፈር ሲንገላቱ እና ሲቸገሩ ማየት እጅግ የሚያሳዝን ነበር። እነዚህን የዓረብ ልጆች ማን ያኑራቸው? ማን ያሳድጋቸው?. . . እናቶቻቸውም በየሠፈሩ እነዚህ የዓረብ ሚስቶች እየተባሉ፤ እንኳንሥ ለትዳር የሚፈልጋቸው፤ ለሠራተኝነትም የሚቀጥራቸው ማግኘት አልቻሉም ነበር።
.
የንግድ ሚኒስቴር ዋና ዋና ኃላፊዎችና የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገር ፍቅር ማህበር አባሎች የተገኙበት ኮሚቴ ጥናቱን አካሂዶ ባቀረበው ሀሳብ፤ “. . . . ምንም እንኳን የየመን ዓረብ ተወላጆች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ የሸቀጣ ሸቀጦች የንግድ ሥራ የጀመሩት ከጠላት በፊት ቢሆንም፤ ዛሬ በየከተማው ሱቆች በብዛት እያቋቋሙ የየሠፈሩን የችርቻሮ ንግድ አስፋፍተው ያዙት፤ በፋሽስት አስተዳደር ዘመን በገፍ በተሰጣቸው የንግድ ሥራ ፈቃድ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ሠዐት የቀደማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት አዲስ አዋጅ በማውጣት፤ ከእንግዲህ ወዲህ በየሠፈሩ የሚካሄደው “ዓረብ ቤት” እየተባለ የሚጠራው የችርቻሮ የንግድ ፈቃድ ለውጭ አገር ተወላጆች የተከለከለ መሆኑን ማስታወቅ የመጀመሪያው እርምጃ ይሆናል። በዚሁ አዋጅ ላይ በተጨማሪ ማብራራት የሚያስፈልገውም፤ ወደፊት አዲስ የችርቻሮ የንግድ ፈቃድ ለውጭ አገር ተወላጆች በሙሉ የተከለከለ መሆኑ ሲገለፅ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ፈቃዱ ተሰጥቷቸው ንግዳቸውን ሲያካሂዱ የቆዩት የውጭ አገር ተወላጆች፤ የያዙት ፈቃድ ጊዜው እስከሚያልቅ ድረስ፤ ሥራቸውን ለመቀጠል እንደሚችሉ ማስታወቅ ይጠቅማል የሚል ነበር።
.
የንግድ ሚኒስተሩ በዚህ ከኮሚቴው በቀረበላቸው ሐሳብ ውስጥ፤ ወደፊት በየሠፈሩ ለሚካሄደው የችርቻሮ ንግድ ሥራ ለውጭ አገር ዜጎች መከልከሉን አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ ነው ብለው ቢያምኑበትም፤ የችግሩ የመጨረሻው መፍትሄ አለመሆኑን በማየት፤ ዓረቦቹ እስከዛሬ የያዙትን ሥራ ኢትዮጵያውያን ወዲያውኑ እንዲረከቡ ለማድረግ ዘዴው ምን እንደሆነ ኮሚቴው ጥናቱን እንዲቀጥል ጠየቁ። በዚህ ውሳኔ መሰረት የንግድ ሚኒስቴርና የአገር ፍቅር ማህበር አባሎች ተሰብስበው ጥናታቸውን በሚያካሂዱበት ጊዜ፤ ለዚህ ኮሚቴ ቃለ ጉባኤ ያዥ እና ላይዘን ኦፊሰር ሆኖ እንዲሰራ መኮነን ሀብተወልድ የመረጡት “ሩጋ አሻሜ” የተባለ ዕድሜው ሠላሳኛውን ዓመት ያልሞላ ወጣት አንድ ሀሳብ ተገለጠለት። ይኸውም ለወጣቱ ሩጋ የታየው በዚህ የሰፈር ችርቻሮ ንግድ አረቦቹን ተቋቁመው የተያዙትን ቦታወች ማስለቀቅ የሚችሉት የትውልድ አገሬ ተወላጆች ጉራጌዎች ብቻ ናቸው የሚል ነበር።
.
ይኽንንም ሃሳቡን በቀጥታ ለኮሚቴው ያቀረበ እንደሆነ ወጣቱ ሩጋ እሱ ራሱ ጉራጌ በመሆኑ ነው ብለው አባሎቹ ሊያፌዙብኝ ይችሉ ይሆናል የሚል ሥጋት ሥላደረበት በቅድሚያ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እና የእርሻ ሚኒስቴር ለሆኑት ለአቶ መኮነን ሀብተወልድ በአንድ ብርቱ ሚስጥር በሚል ማስታወሻ ሐሳቡን እንደሚከተለው ገለፀ።
.
“. . . . ጌታዬ የተጨነቁበትን ጉዳይ እኔም በአቅሜ ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ ያለማቋረጥ ሳስብበት ቆይቻለሁ። ለችግሩ መድሀኒት ተፈልጎ በአስቸኳይ እንዲቀርብልዎ፤ ጌታዬ መመሪያዎንና አደራዎን ለኮሚቴው ሲሰጡ፤ ኃላፊነቱ የሁላችንም ነው። . . . በእኔ በትንሹ ሠራተኛዎ አስተያየት በገዛ አገራችን በችርቻሮ ንግድ የወረሩንን እነዚህን ዓረቦች ማስለቀቅ እና ማሰናበት የምንችለው፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ለጊዜው ቁጥራቸው አምሳ የሚሆኑትን ወጣት ጉራጌዎች መርጠን፤ ዓረቦቹ በከፈቷቸው ሱቆች አጠገብ ተመሳሳይ ሱቅ እየከፈቱ፤ ነዋሪውን ህዝብ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ እና በዋጋ ቅናሽ እየማረኩ በርትተው ሲሰሩ ነው። ዓረቦቹ በዚህ አኳኋን የመጣባቸውን ውድድር ተቋቁመው ለማሸነፍ ስለማይችሉ ሱቆቻቸውን እየዘጉ በሰላም ወደአገራቸው ከመመለስ በስተቀር ሌላ ምርጫ አይኖራቸውም።
.
ትግላችንን በዚህ ሁኔታ እንድንቀጥል ክቡርነትዎ የሚስማሙበት ከሆነ፤ ለሥራ የሚመረጡት ጉራጌዎች በየተወለዱበት አካባቢ በሚገኙት ታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች የታመኑ እና ዋስትና የሚሰጣቸው ሥለሚሆኑ፤ ለንግዳቸው ማቋቋሚያ ወጭው ተተምኖ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ብድር መንግስት ሊሰጣቸው የሚገባ ይሆናል። . . .  በእኔ በትንሹ ሠራተኛዎ ዕምነት የክቡርነትዎ የሌሊትና የቀን ጭንቅ መድኃኒት ሊያገኝ የሚችለው በዚህ ባቀረብኩት ዕቅድ የሚሆን ስለመሰለኝ፤ ሐሳቡ በክቡርነትዎ በኩል ለኮሚቴው ቀርቦ ዝርዝር ጥናት እንዲደረግበት አሳስባለሁ። እኔን ትንሹን ሠራተኛዎን የኮሚቴው ቃለ ጉባዔ ያዥና ከክቡርነትዎ ጽ/ቤት ጋር ላይዘን ኦፊሰር አድርገው ለሰጡኝ ሹመት፤ ይህንን ሐሳቤን ለአባሎቼ አቅርቤ መከራከር ባልቸገረኝ ነበር። ነገር ግን ጌታዬ እንደሚያውቁት የዓረቦቹን ንግድ ተወዳድረው የሚያሸንፉት ጉራጌዎች ስለሆኑ፤ ኃላፊነቱ ለእነሱ ቢሰጥ ይሻላል ብዬ ስናገር፤ ‘ሩጋ አሻሜ ተሻምቶ ለተወላጆቹ አደላ’ ብለው እንዳያፌዙብኝ በማሰብ ነው። . . . .
.
ከክቡር ጌታዬ አጠገብ የመስራት ዕድል ካጋጠመኝ ጊዜ ጀምሮ አንድ ትልቅ ነገር ተምሬአለሁ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተግባሩ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ አንድነት መጣር የመጀመሪያ ግዳጁ መሆኑን ነው። በዚህም መሰረት አገራችን የምትለማውና የምታድገውም በየአውራጃው ያለው ኢትዮጵያዊ በሞያውና በዝንባሌው ተግቶ ሲሠራ ነው ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌም ከዓረብ ነጋዴዎች ጋር ለሚያስፈልገው ውድድር ተወላጆቼ ጉራጌዎች የተሻሉ ይሆናሉ ብዬ ስናገር፤ ሞያቸውንና ችሎታቸውን በመመርኮዝ እንጂ፤ በተለይ ወገኖቼን ለመጥቀም በተመሠረተ ሐሳብ ላይ አለመሆኑን ጌታዬ እንደሚገነዘቡልኝ ዕምነቴ ሙሉ ነው። ጌታዬ፤ እንደ አለቃ፣ እንደ መሪ ሳይሆን እንደ አባት ሆነው በየጊዜው ለሚሰጡኝ ትምህርት እና ማበረታቻ ተደፋፍሬ የሚመሥለኝን ሐሳብ አቅርቢያለሁ።”
.
ፍጹም ታዛዥዎ ሩጋ አሻሜ
.
መኮነን ሀብተወልድ ወጣቱ ሩጋ ባቀረበላቸው ሐሳብ በጣም ተማረኩ። በማግስቱም በሀገር ፍቅር ማህበር ጽ/ቤታቸው ኮሚቴውን ሰብስበው የሩጋ አሻሜን ስም ሳያነሱ፤ ከአንድ ትጉህ ሠራተኛዬ የቀረበልኝ በሚል መነሻ ሐሳቡን ተንትነው ለአባሎቹ ገለፁ። በመጨረሻም “. . . . እኔ በቀረበልኝ ሐሳብ ተስማምቼበታለሁ። እናንተ የአፈፃፀሙን ቅደም ተከተል በዝርዝር አጥንታችሁ በአንድ ሳምንት ውስጥ እንድታቀርቡልኝ . . .” የሚል ውሳኔ ሰጥተው ስብሰባውን በተኑ። የኮሚቴው አባሎች በየፊናቸው ልዩ ልዩ ሐሳብ እየነደፉ ከመጨቃጨቅ፤ ሚኒስትሩ የተስማሙበትን ተከትለው የአፈፃፀሙን አሠራር ማዘጋጀት የቀለለ ሆነላቸው። ከአጥኒዎቹ መካከል አንዳንዶቹ፤ አዲስ የሚፈጠረውን የንግድ ሥራ ለጉራጌዎች ብቻ ከመደልደል፤ ለሌሎችም ነገዶች ለምሳሌ ለወሎየዎችና ለትግሬዎች እንዲከፋፈል ቢታሰብበት ይሻል ይሆናል የሚል ሐሳብ የሰነዘሩ ነበሩ።
.
ሚኒስትሩ ወዲያው በሰጡት መልስ “. . . . ይህን ሐሳብ የምንድገፈውብቻ ሳይሆን ከልብ የምናምንበት ነው። እንደምታውቁት ዓረቦቹ ንግዳቸውን ያስፋፉት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም የአውራጃ ከተሞች ነው። አሁን እንዳላችሁት ከወሎና ከትግሬ ወንድሞቻችን መካከል ዓረቦቹ ይዘው የሚጠቀሙብንን የንግድ ሥራ እየተወዳደርን እጃችን ለማስገባት እንችላለን ብለው ሲቀርቡልን፤ ዕድሉን የምንሰጣቸው በደስታ ነው፤ ለእነሱም ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹ በሩ ክፍት ነው . . .” አሉ።
.
በመጨረሻም በወጣቱ ሩጋ አሻሜና በጓደኞቹ ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርጠው የቀረቡት አርባዎቹ የጉራጌ ነጋዴዎች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ተቀብለው በአዲስአበባ ከተማ ሥራቸውን በአስቸኳይ እንዲጀምሩና በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የሚሰጡት ውጤት ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት የኮሚቴው አባሎች በሙሉ ከስምምነት ላይ ደረሱ። እነዚህም አርባዎቹ ወጣት ነጋዴዎች በየሠፈሩ ከሚገኘው ዓረብ ቤት አጠገብ፤ ሱቅ እንዲያቋቁሙ ንግዳቸውን ለመጀመር ወደፊት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ከሚያገኙት ትርፍ የሚከፍሉት ለእያንዳንዳቸው ሰባት መቶ የኢትዮጵያ ብርመንግስት እንዲያበድራቸው ኮሚቴው የተስማማበትን መኮነን ሀብተወልድ ለንጉሰ ነገስቱ አቅርበው አስፈቀዱ።
.
ይህ ሰባት መቶ ብር የተተመነው
    ሀ/ ለሱቅ መሥሪያ ሁለት መቶ ብር
    ለ/ ለንግድ ዕቃዎች ማዘጋጃ አምስት መቶ ብር እንዲሆን ነበር።
.
ቀደም ሲል እንደ ተገለፀው፤ ሩጋ አሻሜ (በኋላ ፊታውራሪ) በዓረቦቹ የተያዙትን የሠፈር ንግዶች ተቋቁሞ ለማሸነፍ የተሻለ ዘዴ ይሆናል ብለው ያቀረቡትን ሐሳብ፤ የንግድ ሚኒስተሩ በይፋ እንዲታወቅላቸው ለማድረግ የወሰኑት፤ ጉዳዩን ኮሚቴው አጥንቶ ከተስማማበት በኋላ እንዲሆን ነበር። በዚህ ጊዜ ሩጋ አሻሜ ለመኮነን ሀብተወልድ ባቀረቡት ልዩ ማስታወሻ የሚለተለውን ገለጹ።
.
“. . . እኔ ትንሹ ሠራተኛዎ ባለኝ ችሎታና አቅም በማሳየው የሥራ ጥረት፤ ከጓደኞቼና ከታላላቆቼ የተለየ አድናቆትም ሆነ ምሥጋና እንዳገኝ ክቡርነትዎን ማስቸገር አልፈልግም። ይልቁንም ወደፊት የተደቀኑብኝ የኃላፊነት ሥራዎች ብዙ ስለሆኑ፤ ከጌታዬ የሚሰጡኝን አድናቆቶችም ሆኑ ሽልማቶች ተቆጥበው እንዲቀመጡልኝ አጥብቄ እለምናለሁ። አሁንም፤ ጌታዬ በጣም የተጨነቁበት ንጉሠ ነገሥታችንም ከልባቸው ያሰቡበት፤ በየመንደሩ የተጥለቀለቁትን የዓረብ የንግድ ቤቶች ወደ ኢትዮጵያውያን እጅ ለማዛወር፤ ሥራው እንዲጀመር ተወሰነ እንጂ ፍሬውን አላሳየም። ይሁን እንጂ ሁላችንም ቃል እንደገባነው፤ ከዛሬው ዕለት ጀምሮ በዚህ በመጭው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ቆርጠን የተነሳንበትን ለማሸነፍና ለማስፈጸም ስንችል፤ በተለይ እኔ ትንሹ ሠራተኛዎ ከጌታዬ የምጠብቀው ምስጋና ብቻ ሳይሆን ትልቅ ሽልማት ነው . . .” አቶ መኮነን በሩጋ አሻሜ ላይ ከቀድሞው የበለጠ ከፍ ያለ አድናቆት አደረባቸው። የሩጋን ብልህነትና አርቆ አሳቢነትም ምን ያህል የጠለቀ መሆኑን ለጃንሆይ ነገሩላቸው።
.
እንደታሰበው ጉራጌዎቹ ነጋዴዎች በየዓረቡ መደብር አጠገብ ሱቆቻቸውን እየተከሉ ንግዳቸውን ሲጀምሩ፤ የሠፈርተኛው ሕዝብ መልካም ትብብር ስላልተለያቸው ያደረባቸው ትጋትና የጋለ ስሜት እጅግ የተለየ ሆኖ ይታይ ነበር። አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከአርባዎቹ ጉራጌዎች መካከል ሰላሳ ሦስቱ በዓረቦቹ ተይዞ የነበረውን ንግድ በሙሉ ቀልብሰው ስለወሰዱት ዓረቦቹ የነበራቸውን ሱቅ እያፈረሱ ከሠፈሩ መጥፋት ግዴታ ሆነባቸው። የየሠፈሩም ነዋሪ ሕዝብ ለዕለት ኑሮው የሚያስፈልገውን ሁሉ ለመገብዬት በወገንና በውጭ ዜጋ ነጋዴዎች መካከል ያለውን ልዩነት ስለተረዳው፤ የዓረቦቹን መደበር እየተወ ግልብጥ ብሎ ወደ ኢትዮጵያውያኖቹ ሱቆች ለማምራት ጊዜ አልፈጀም። ኢትዮጵያውያኖቹም ነጋዴዎች ሕዝቡ ለዕለት ኑሮው የሚያስፈልጉትን ሁሉ ከየዓረብ ቤት በተሻለ አኳኋን አሟልተው መገኘታቸው ብቻ የሚያስፈልጉትን ሁሉ ከየዓረብ ቤቱ በተሻለ አኳኋን አሟልተው መገኘታቸው ብቻ ሳይሆን መጠነኛ የሆነ የዋጋ ቅናሽ በማድረጋቸውም ተጠቃሚዎቹን ለመማረክ ችለዋል።
.
ከዚህ በላይ ደግሞ የንግድ ሚኒስተሩን እጅግ አድርጎ ያስጨነቃቸው፤ ነጋዴዎች በነጭ ወረቀት ላይ እየፈረሙ፤ እያንዳንዳቸው ከመንግስት የተበደሩትን ሰባት መቶ ብር የውሉ ዘመን ሊፈፀም ሲቃረብ፤ ንግድ ሚኒስተር እየሄዱ ዕዳችንን በደረሰኝ ተቀበሉን እያሉ ማስቸገራቸው ነበር። ከላይ እንደተገለፀው ነጋዴዎቹ ገንዘቡን የተቀበሉት በብድር ስም በነጭ ወረቀት ላይ እየፈረሙ ስለሆነ አሁን ገንዘቡን ሲመልሱ እነሱ እንደጠየቁት በገንዘብ ሚኒስተር ደረሰኝ “ከመንግስት የተሰጠ ብድር” እየተባለ ካርኒ መቁረጡ በጣም የሚያስቸግር ሆነ። ለአሠራሩ የሚሻለው ነጋዴዎቹ በነጭ ወረቀት ላይ የፈረሙት የዕዳ ሰነድ እየተመለሰላቸው ገንዘቡን ቢያስገቡ ነበር። ነገር ግን ጉራጌዎቹ ዘንድ በገንዘብ ክሽ ክሽ የለም። እኛ ገንዘቡን ስንቀበል “ብድር ነው” ብለን መፈረም ብቻ ሳይሆን ተያዥም እየሰጠን ነው፤ ስለዚህ የተበደርነውን ስንመልስ ካርኒ የተቆረጠበት የመንግስት ደረሰኝ ካልተሰጠን ገንዘቡን ገቢ አናደርግም አሉ።
.
በመሰረቱ የዓረቦቹን ንግድ ለመወዳደር ለተመረጡት ለአርባዎቹ ነጋዴዎች ንጉሠ ነገሥቱ የፈቀዱት ሃያ ስምንት ሺህ ብር (40×700 = 28,000) በብድር ስም እንዲሰጣቸው አልነበረም። ነገር ግን በነፃ የተሰጣቸው እርዳታ መሆኑን ነጋዴዎቹ ካወቁ ምናልባት የኃላፊነት ስሜት ላያድርባቸውና ገንዘቡንም ተቆጣጣሪ የለብንም በማለት ለታሰበው ጉዳይ በትክክል ላያውሉት ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጠረ። ስለዚህ በብድር ስም በነጭ ወረቀት እየፈረሙ ገንዘቡን እንዲቀበሉና ትርፍ ካገኙበት ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ኪሳራ ላይ ከወደቁ ደግሞ በዕዳ እንዳይጠየቁ ሚኒስትሩ ፈቅደው ሥራው የተጀመረው በዚህ መልክ ነበር። አሁን ከአርባዎቹ ነጋዴዎች ውስጥ ሠላሳ ሦስቱ ትርፍ ሲያገኙ ገንዘቡን ለመመለስ መቅረባቸው የሚያስደስት ሲሆን፤ የገንዘብ ሚኒስቴር የገቢ ደረሰኝ ካርኒ ካልተቆረጠልን ማለታቸው ለአፈጻፀሙ አስቸጋሪ በመሆኑ ሌላ ዘዴ መፈለግ ግዴታ ሆነ። ዘዴው ተፈልጎ ከመገኘቱ በፊት፤ ነጋዴዎች ቀድመው ለንግድ ሚኒስትሩ አንድ የተለየ ሐሳብ አቀረቡ።
.
“. . . እኛ የሸቀጣ ሸቀጥ ችርቻሮ ነጋዴዎች፤ ለጀመርነው የንግድ ሥራ ማስፋፊያ እንዲሆን አንድ ማህበር አቋቁመናል። የማህበራችን ዋና ተግባር መንግስታችን ለእኛ በቀየሰልን መንገድና በሰጠን ከፍተኛ ድጋፍ እስካሁን ከፍተኛ ውጤት ስለአገኘንበት ይኽንኑ ዓላማ ዜጎች ከሆኑት ነጋዴዎች ጋር ለመወዳደር እንድንችል አስፈላጊውን እርዳታ መስጠት ነው። ባለፈው አመት ለሥራችን መቋቋሚያ መንግስታችን ያበደረንን ገንዘብ ገቢ ለማድረግ ተዘጋጅተን ስንቀርብ የንግድ ሚኒስቴር ስለ ደረሰኝ አሰጣጥ ጥናት በማድረግ ላይ ስላለሁ ለጊዜው ገንዘቡን መቀበል አልችልም ብሎ መለሰልን። ክቡርነትዎ እንደሚታወቀው ይህ የተበደርነው ገንዘብ ሳንሠራበት በየኪሳችን ቢቀመጥ አንዳች ትርፍ ሊሰጥ አይችልም። ስለዚህ ያቋቋምነው የንግድ ማስፋፊያው ማህበራችን ይህንን እጃችን ላይ የሚገኘውን ገንዘብ በብድር ተቀብሎ እንዲሠራበት እና ትርፍ ሲያገኝ ለመንግስታችን ገቢ እንዲያደርግ እንዲፈቀድለት ክቡርነትዎን እንለምናለን . . . ” የሚል ነበር።
.
መኮነን ሀብተወልድ ይህን ሐሳብ የተመለከቱት በከፍተኛ አድናቆት ነበር። በአቀራረቡም ስለተደሰቱ፤ ጉዳዩን ለማስፈፀም ጊዜ አልወሰዱም። ልዩ ጸሀፊያቸውን ጠርተው “. . . ይህ የቀረበልኝ ሐሳብ የጉራጌዎችን ንቃት እና ብልህነት ደህና አድርጎ የሚያመለክት ነው። የመስሪያቤታችንን የአሰራር ድክመት ተገንዝበው “እምቢ” የማይባል ጥያቄ አቅርበውልናል። በመሰረቱ እኛ የምንፈልገው እነሱ ብርታታቸውን ቀጥለው ዓረቦቹን እንዲያባርሩልን ነው። እስካሁን ያስገኙት ውጤት በጣም ጥሩ ስለሆነ፤ አሁን የጠየቁትን በአቃቤ ሠዐት ለጃንሆይ አቅርቤ እንዳስፈቅድላቸው ማስታወሻው ይዘጋጅልኝ . . .” ብለው ወሰኑ።
.
ሚኒስትሩ ከልባቸው ስለአሰቡበት አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የንጉሠ ነገሥቱን መልካም ፈቃድ አግኝተው የጉራጐዎቹ ማህበር ገንዘቡን ተቀብሎ “የዓረብ ቤት” በሚል መጠሪያ በየከተማው የተጥለቀለቀውን ንግድ ቤት በውድድር እያዘጋ፤ የኢትዮጵያውያኑን መብት እንዲያስከብር ሙሉ ዕምነታቸውን ጣሉበት። በዚህ አኳኋን ጉራጌዎቹ ተጠናክረው ባሳዩት ብርቱ ጥረት የየመን ዓረቦች አብዛኛዎቹ ሱቆቻቸውን እየዘጉ ወደየአገራቸው ሲመለሱ፤ ጥቂቶች ደግሞ ሌላ ባላንጣ ደርሶ እስከሚያባርራቸው ወደ ዋናው ገበያ ወደ መርካቶ እየተዛወሩ በልዩ ልዩ የጨርቃ ጨርቅ ንግድ ለመቋቋም ሞክረው ነበር። ሙከራቸው ብዙ ሊያቆያቸው ስላልቻለ እነሱም ቀስበቀስ እየመነመኑ ጠፉ።
.
እንግዲህ የጉራጌዎች የንግድ ባህል እንዲህ ባጋጣሚ በሩጋ አሻሜ ሀሳብ አመንጭነት ተጀምሮ አንዱ ሌላውን ሲስብ እና ሲያሰባስስብ ብዙ ዘመናትን ካሳለፈ በኋላ ይኸው በዛሬው ጊዜ ጉራጌዎች በአሮጌይቱ ኢትዮጵያ በንግድ ታዋቂነትን እና ከፍተኛ ተዋናይተን እንዲጎናፀፉ አስችሏቸዋል።
Filed in: Amharic