>

"መታሰርም መፈታትም ያው ነው" አባ ገ/ኢየሱስ

ከዋልድባ መነኮሳት አባቶቻችን ጋር የነበረኝን ቆይታ እነሆ፦ (ያሬድ ሹመቴ)
ከቀናት በፊት “የዋልድባ መነኮሳት ተፈቱ” የሚል ዜና በስፋት ተሰራጭቶ ነበር። ከደስታ ብዛትም የታማኝ ጓደኞቻችንን መዘገብ ብቻ በማየት ብዙዎቻችን ተመሳሳይ ስህተት ስተናል። የዚህ ስህተት አባል ከሆኑትም መሐል አንዱ እኔ ነኝ። ይቅርታ መጠየቅ ብቻውን አይበቃም በማለት ስህተቱ ከተፈጠረበት ቀን አንስቶ ይህንን ጽሁፍ እስከጻፍኩበት ሰዓት ድረስ በዚሁ የፌስቡክ መድረክ (የፋሲካ መልካም ምኞትን ጨምሮ) ምንም ነገር በዚህ ገጼ ከመጻፍ ታቅቤ ቆይቻለሁ። ዛሬ ፀፀቴን የሚቀንስ እና ድፍረት የሚሰጠኝ እድል በማግኘቴ ይቅርታ ታደርጉልኝ ዘንድ ለመጠየቅ መጥቻለሁ።
ማክሰኞ ጠዋት ሚያዝያ 2 / 2010 ዓ.ም.
2:00 ሰዓት ቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ደረስኩ። የዞን 1 (አባቶች ያሉበት እስር ክልል) ሰልፍ ከሁሉም የበለጠ እስረኛ ጠባቂ ይበዛበታል። ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ በሰልፉ ላይ ቆየሁ። መዝጋቢ ፖሊስ ሙሉ ስሜን እና አድራሻዬን ከጻፈች በኋላ ከእስረኛው ጋር ያለኝን የዝምድና አይነት ጠየቀችኝ።
“የኃይማኖት አባቶቼ ናቸው” አልኳት
“የንስሐ አባት” ብላ ሞላችው።
ብጣሽ ወረቀት ሳይቀር ተፈትሼ ካስረከብኩ በኋላ ወደ ውስጥ ገባሁ። የዞን አንድ እስረኛ መጠየቂያ ፤ ከፍተሻው በኋላ የቀኝ አቅጣጫ ይዞ የሁለት ደቂቃ ጉዞ ያስፈልገዋል። ቀጥሎ ባለው የግራ በር ላይ ዘልቄ ገባሁ በርካታ ሰዎች እስረኛ ቤተሰቦቻቸውን የሽቦ አጥሩን ተጠግተው ያነጋግራሉ ከበሩ ትይዩ መነኮሳት አባቶቻችንን ከርቀት አየኋቸው። እነሱ ብቻ ማንም ጠያቂ ሰው የላቸውም። ለብቻቸው ቆመው አገኘኋቸው።
ሰላምታ ከተቀያየርን በኋላ ራሴን አስተዋወቅኳቸው። የመጀመሪያ ስሜን እንደነገርኳቸው አባ ገብረ ኢየሱስ አስታወሱኝ። መልካም ሀሳቦችን ተቀያየርን። በእጅጉ ደስም አለኝ። ከኔ ኋላ ሌላ ጠያቂ ስላልነበራቸውን የበቃኝን ያህል ለመነጋገር ግዜ አልገደበኝም ነበር።
በመጨረሻም “እንግዲህ አባቶቼ አይዟችሁ” አልኳቸው።
“ምን ችግር የለውም ወንድሜ። ብንፈታም ብንታሰርም ለውጥ የለውም” አሉኝ አባ ገ/ኢየሱስ።
“እንዴት” አልኳቸው
“ምንኩስና እኮ እንዲሁ ነው። አጥር ስለሌለው፤ ጠባቂም ስላልተመደበበት እንጂ ምንኩስናም ያው መገለል ማለት ነው” አሉኝ።
አባ ገ/ኢየሱስ ቀጥል አድርገውም እንዲህ አሉ። “እኛ እድለኞች ነን። ህማማቱን እዚህ በማሳለፋችን ደስ ብሎናል። ትንሳኤንም እዚሁ ደስ ብሎን ውለናን። እግዚአብሔር ፈቅዶ ተደስተን ነው የዋልነው። ትዕዛዙም የሚለው እኮ እንዲሁ ነው። እኛ ብንፈታም ባንፈታም ችግር የለውም። ብቻ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ሰላም ያድርጋት። ይህ ነው እንጂ ፀሎታችን ስለኛ መፈታት ግድ የለንም።”
የእነ አባ ገብረ እየሱስን ምርቃት ተቀብዬ ልወጣ ስል “የታሰረን መጠየቅ ኃይማኖታዊ ተግባር ነውና ስለጎበኛችሁን ደስ ብሎናል” አሉኝ።
አባ ገ/እየሱስ ኪ/ማርያም እና አባ ገ/ስላሴ ወ/ሐይማኖት ሚያዝያ 18 ቀን ቀጣይ የፍርድ ቤት ቀጠሮ እንዳላቸው ነግረውኛል።
በረከታቸው ይድረሰን!!
ለቀደመው ስህተቴም ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ።
Filed in: Amharic