>
5:21 pm - Wednesday July 20, 2383

ይህች ሃገር ስለምን ገብርየን እረሳች? (ሙሉጌታ አንበርብር)

የታማኙ ፊታውራሪ ገብርዬ ሚያዚያ 3 / 2010 ዓ.ም 150ኛ ዓመት ሙት ዓመት መታሰቢያ
ፊታውራሪ ገብርዬ የጋይንት ሰው ናቸው፡፡ ሙሉ ስማቸው ገብረሕይወት ጎሹ ነው፡፡ የዐጼ ቴዎድሮስ የጦር አዛዥ፣ እጅግ የተደነቁ ስመ-ጥር የጀግኖች ጀግና ነበሩ፡፡ ከሽፍትነት ዘመናቸው ጀምሮም ታማኛቸው ናቸው፡፡
የእንግሊዝ ጦር ወደ ኢትዮጵያ በዘመተበት ወቅት የዐጼ ቴዎድሮስ ጠቅላላ የወታደር ብዛት ተመናምኖ ተመናምኖ ከ5000-6000 ብቻ የሚገመት ነበር፡፡ በመቶ ሺህ ይቆጠር የነበረው ወታደራቸው በዚህን ወቅት የለም፡፡ በአንጻሩ የእንግሊዝ ደግሞ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀ 12000 ገደማ የሚደርስ ነበር፡፡ ይህንን የእንግሊዝ ጦር 5000 ገደማ የሚሆን ወታደር እየመሩ ይገጥሙ ዘንድ ገብርዬ ተጠሩ፡፡
ገብርዬም አንድም ለአገራቸውም አንድም ለንጉሣቸው እስከሞት የታመኑ ናቸውና ሰናድር አንግቶ፣መድፍ ጎትቶ፣በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቆ የመጣውን የእንግሊዝ ሠራዊት በጦርና ጎራዴ ለመውጋት ሳያንገራግሩ ዘመቱ፡፡
ገብርዬ- በወርቅ ዝምዝ ያጌጠ የሐር ቀሚሳቸውን እንደለበሱ፣ባለሜጫ ሾተል፣በወርቅ የጌጤ ጋሻ አንግተው፣ሁለት አፏጭ ጦር ይዘው፣ ‘’ገብሬ የፈሪ ጅራት’’ ብለው በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ፎክረው ነው ወደ እሮጌ የዘመቱት፡፡ ሽበት ጸጉራቸውን የወረረው የጀግኖቹ ጀግና ገብርዬ የጠገበ ፈረሳቸውም ‘’ቼ’’ ብለው በእሮጌ ውጊያ መሃል ለማሃል በመሰለፍ ገጠሙ፡፡
ኋላ ቀር የጦር መሣሪያ የታጠቀ፣በቁጥርም አነስተኛ የሆነ ወታደር ይዘው የስቅለት ቀን በጀግንነት እየተዋጉ ሳለ እርጌ ላይ ገጥመው ሲዋጉ ተሰው፡፡ የገብርዬ ፈረስም ጌታውን አልከዳም፤ አብሮ ተሰውቶ ከጎናቸው ተኛ እንጂ!
ገብርዬም ለአገር ክብርና ፍቅር በእለተ ስቅለት ልክ እንደ ክርስቶስ ራሳቸውን ሰጡ፡፡ ምናልባትም ማሸነፍ እንደማይችሉ ቢያውቁም 700 ገደማ ወታደር አብሯቸው ተሰዋ፤120 ገደማ ቆሰለ፡፡ ከእንግሊዝ የቆሰለው 20 ብቻ ነበር፡፡
የገብርዬን ልብሳቸውን ባሻ ፈለቀ (ካፒቴን ስፒዲ) ለበሰው፤ጋሻቸውን አነገተ፤ ጦራቸውንም ያዘ፡፡
የጦራቸውን መሸነፍ በመነጥር ይመለከቱ የነበሩት ንጉሥ የገብርዬን ሞት ግን ዘግይተው ሰሙ፡፡ መርዶውን ሲሰሙም ልክ ዮሐንስ የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት ሲመለከት “ወዮ ወዮ” ብሎ እንዳለቀሰውና አንጀቱ እንደእሳት እንደነደደው (በአንጻረ መስቀል ቀዊሞ ዮሐንስ በክየ፣እንዘ ይብል ወይልዬ ወይልዬ አማዑተ ከርሡ ከመ ነደ እሳት ውዕዬ….ተብሎ እሴብሕ ጸጋከ ላይ እንደተጻፈው!) የመይሳው ልጅም እንባቸው በአንገታቸው እስቲወርድ “የእናቴ ልጅ ጓዴ የእናቴ ልጅ ጓዴ” እያሉ አለቀሱ፡፡ መቅደላ አምባ ላይ ባሉት ሰፈሮች ዋይታና ለቅሶ ሆኖ አደረ፡፡
አፄ ቴዎድሮስና ፊታውራሪ ገብርዬ እንዴት ተገናኙ
የታንጉት ምስጢር በተሰኘው ታሪካዊ ልብወለድ መጽሐፍ እንደተገለፀው ፊታውራሪ ገብርዬ ወላጆቹን በሙሽርነቱ ጊዜ በተፈጠረ ግጭት ካጣ በኋላ ወደ ጫካ ገባ። የቋራውን ጀግና የካሳ ሐይሉን ዝና ሰምቶ ወደ እሱ ሄደ ፤ ተገናኙ ከዚያም በጣም የሚዋደዱ ጓደኛሞች ሆኑ! ገብርዬ የካሳ ቀኝ እጅ ሆነ።
የገብርዬ ዕረፍት
1860 ዓ/ም – የስቅለት ዓርብ ዕለት ሚያዝያ 3 በ ሎርድ ናፒዬር የሚመራው የእንግሊዝ ሠራዊት እና የ ዓፄ ቴዎድሮስ ሠራዊት በ መቅደላ ተራራ ሥር በምትገኘው እሮጌ በምትባል ሥፍራ ላይ ጦርነት ገጥመው የዓፄ ቴዎድሮስ የጦር አዛዥ የነበሩት ፊታውራሪ ገብርዬ ሞቱ።
ምንጭ፡- ተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ዐጼ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት፤ ጳውሎስ ኞኞ፣አጤ ቴዎድሮስ ፉሴላ ያሳተመው ስሙ የማይታወቀው ደራሲ የጻፈው (አለቃ ለምለም?)፣ያጤ ቴዎድሮስ ታሪክ
Filed in: Amharic