>
5:18 pm - Sunday June 16, 2080

ክቡርነትዎ የአማራ ህዝብ የናፈቀው "..ዋልታ እና ማገር.." የሚለው ስብከትዎን ሳይሆን እስረኛ ልጆቹን ነው!!! (ሚኪ አምሀራ)

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለጊዜዉ የአማራ ህዝብ ጉዳዮች እኒህ ናቸዉ፡፡ አማራ ክልል ድረስም እንዳይለፉ ስል እመክረወታለዉ፡፡ ለምን ካሉ መልሱ መጨረሻ ላይ አለልወት፡፡
1. በ 2008፤2009፤2010 በአማራ ክልል 1740 ሰወች በአጋዚ ሲገደሉ፡፡ ሰሜን ጎንደር አጠቃላይ በሁለት የእስር ቤት ቃጠሎ 96 ሰወች፤ በጭልጋ እና ላይ አርማጭሆ በተከሰተ ግጭት 120 ሰወች፤ በመተማ የአጋዚ ወታደሮች የገደሏቸዉ 56 ሰወች፤ በቋራ (26 ሰወች) ፤አምባጊዎርጊስ ላይ 24 ሰወች፤ በዳባትና ቆላ ወገራ (27 ሰወች) ጎንደር ከተማ በነበረዉ አመጽ 29 ሰወች፤ ህወሃት ታጣቂ ብሎ ንጹህ ገበሬወችን ገደልኩ ብሎ በዜና ያወጣዉ 597 አማሮች (ዜናዉ ከታች ተያይዟል በምስል):: ባህርዳር በአንዲት የተረገመች ቀን በአጋዚ 134 ሰወች ሲገደሉ፤ በደብረታቦር (55 ሰወች)፤በእንጅባራ (17 ሰወች)፤በወልድያ (34 ሰወች)፤በሽዋ ሮቢት ቀወት ወረዳ( 40 ሰወች)፤ በመራይ (9 ሰወች) በአረርቲ (4 ሰወች)፤በቡሬ (9 ሰወች)፤በፍኖተ ሰላም (4 ሰወች)፤በወረታ (8 ሰወች)፤በቻግኒ (12 ሰወች)፤ በዳንግላ (11 ሰወች)፣ ቆቦ (11 ሰወች)፤ መርሳ (17 ሰወች)፤ ጋይንት (16 ሰወች)፤ ሰማዳ፤ (22 ሰወች)፤ ደባርቅ (14 ሰወች)፤ ጭልጋና ሽንፋ (65 ሰወች )፤ ጭስ አባይ (11  ሰወች)፤ ምእራብና ታች አርማጭሆ (48 ሰወች)፤በሰሜን ወሎ እና አፋር ደንበር (18 ሰወች) በኣጋዚ ተገለዋል፡፡ ለእነዚህ ሟቾችና ቤተሰቦቻቸዉ ፍትህ እና ካሳ እንዴት ነዉ ሚካሄደዉ?
2. ትግራይ ክልል የሚማሩ በድምሩ በባለፉት ሶስት አመታት ብቻ  15 አማራወች ተገለዋል፡፡ አዲግራት (6 ተማሪዎች) አክሱም (5 ተማሪዎች) መቀሌ (4ተማሪዎች) ለእነዚህ ፍትህ እንዴት እንደሚገኝ?
3. በ2009 እና 2010 በኦሮሚያ ክልል በጂማ ዞን ጦላይ ወረዳ 12 አማራወች፤በኤሌባቦር ቡኖ በደሌ ዞን በጮራና ዴጋ ወረዳዎች 26 አማሮች፤ ከ6ሺህ በላይ ተፈናቅለዋል ንብረታቸዉ ወድሟል ለነዚህ ፍትህ?
4.  በቤንሻንጉል ከማሽ ዞን፣ በሎጅጋንፎይ ወረዳ፣ በሎደዴሳ 40 አማራወች ለነዚህ ፍትህ እንዴት ያመጣሉ?
5. በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢች ማለትም በጨለንቆ፤ በአርባ ጉጉ እና በመሳሰሉት አካባቢወች ኦነግ እንደ እንስሳ ያረዳቸዉንና ገደል ዉስጥ የጨመራቸዉ ከ 20ሺህ በላይ አማሮች የተፈናቀሉት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አማሮች ፍትህ እንዴት ሊያገኙ ይችላሉ?
6. በጉራ ፈርዳ የተገደሉት 260 አማራወች ይሄም በቅርብ በመንግስት ሚዲያ ተገልጻል፡፡ ከዚህም በላይ ወደ 45 ሺህ የሚደርስ ተፈናቅለዉ አሁን በየከተማዉ ወይም የቀን ሰራተኛ አለያም በልመና እየተዳደሩ ነዉ፡፡ ፍትህ ለነዚህስ?
7. የወልቃይትን ጉዳይ እንዴት እንደሚፈታ ትልቁ ጉዳያችን ነዉ፡፡
8. 100ሺህ የአማራ አስርኞች በሀገሪቱ እስርቤቶች አሉ፡፡ ከሁመራ እስከ ዝዋይ፡፡ በባለፉት ሁለት ወራቶች ወደ 3 ሺህ ገደማ ሲለቀቁ አሁን ወደ 97ሺህ ይቀራሉ፡፡ አጠቃላይ የአማራ ህዝብ 0.25 በመቶ በአሁኑ ሰአት እስር ቤት ነዉ፡፡የወልቃይት አማራ 1/3ኛዉ (33 በመቶዉ) እስር ቤት ነዉ፡፡ እዚህ ላይ ምን መፍትሄ እንዳለዎት?
9. በተለያየ ጊዜ የህወሃት አጋዚ ወታደርና ደህንነት በሚወስደዉ ግድያ በተለይም ሰሜን ጎንደር አካባቢ የወላጅ አልባ ህጻናት ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነዉ፡፡ ለምሳሌ Handicap International እና Save the Children Norway የተባሉት በህጻናት ዙሪያ የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሰሜን ጎንደር አካባቢ 118ሺህ ወላጅ አልባ ህጻናቶች ይረዳሉ፡፡ ይህ ማለት የአካባቢዉን ህዝብ 2.95 በመቶኛ የሸፍናል ማለት ነዉ፡፡ ይህ በአለም ትልቁ ቁጥር ነዉ፡፡ ሶሪያ እንኳን ይሄን ያህል ሊደርስ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ዉስጥ በወላጅ አልባ ህጻናት ዙሪያ የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሙሉ ሰሜን ጎንደር ዉስጥ ነዉ ያሉት፡፡ አካባቢዉ ላይ በወል የሚታወቅ ጦርነት አልነበረም በባለፉት 27 አመታት ግን በሚዲያ ያልተገለጸ አንዴ ሽፍታ፤ አንዴ አርበኞች፤አንዴ ግንቦት ሰባት እያለ ህወሃት ከፍተኛ ግድያ አካሂዷል፡፡ ባለፈዉ አመት ብቻ የህወሃቱ ፋና ሬድዮና ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገቡት ከነሀሴ እስከ ጥቅምት ባለዉ ጊዜ በ 3 ወር ዉስጥ ብቻ 597 ታጣቂወች ገደልኩ ብሏል (ዜናዉ በምስሉ ተያይዟል)፡፡ የተገደሉት ግን ንጹህ የአማራ ገበሬወች ናቸዉ፡፡
10. የአማራ ወጣት መሆን ከመታሰር ስለማናመልጥ ብለን ሁላችንም እኔን ጨምሮ ማታ ማታ አንድ ላይ ሁነን ቆለጣችን ላይ የሃይላንድ ዉሃ እያንጠለጠልን እንለማመዳለን፡፡ እኔ እና ጓደኞች ቢያንስ በወር ሁለቴ እንዲህ አይነት ልምምድ እናደርጋለን፡፡እንደማይቀርልን ስለምናዉቀዉ ነዉ፡፡ ገብተዉ የወጡ ጓደኞቻችንም ይሄን ኢ-ሰባዊ ድርጊት እንደተፈጸመባቸዉ ስለምናዉቅና ስላየን ነዉ፡፡ ይሄን የጅምላ እስር እንዴት ነዉ የሚያስቆሙት?
11. የኢኮኖሚዉን ጉዳይ ለእርስወ አሁን አጀንዳ እንዲያደርጉት አልሰጠወትም፡፡ የክልሉ ኢኮኖሚ አሳሳቢ ደረጃ ወይም crisis በሚባል ደረጃ ያለ ሲሆን ይሄን ክልሉን ለሚያስተዳድረዉ ብአዴን በዋነኛነት እንተወዋለን፡፡ ነገር ግን ግድያ፤እስር፤ እና ስደት ክልሉ ላይ ከቀነሰለን እኛ የአማራ ህዝቦች በታታሪነታችን ኢኮኖሚዉን ማስተካከል እንችላለን፡፡ ነገር ግን 100ሺህ አምራች የሆነዉ የወጣት ክፍል እስር ቤት ነዉ፡፡ እነሱን ብቻ እንዲለቀቁልን ነዉ የምንፈልገዉ፡፡ የኢኮኖሚዉን ጉዳይ እኛዉ እንወጣዋለን፡፡
እርስዎ  ወደ አማራ ክልል በመምጣት ጊዚወን እንዳያባክኑ እመክረወታለዉ፡፡ እኛ የመገንጠልም አገር የማፍረስም ፍላጎት የለንም፡፡ አገር ለመገንጠልና ለማፍረስ እየሰሩ ያሉ አካባቢወችን መጎብኘትዎ ተገቢ ነዉ እላለዉ እንኳንም ጎበኟቸዉ፡፡ ቢሆንም የአማራ ክልልን ህዝብ ማግኘትና ችግሩን መስማት አለብኝ ብለዉ ከወሰኑ ደግሞ፤ ከሁሉም የአማራ ግዛት የተወጣጡ አዲስ አበባ ዉስጥ ቃሊቲ፤ቂሊንጦ፤ማእከላዊና ሌሎች  ስዉር እስር ቤቶች ዉሰጥ እድሚያቸዉ ከ 14 እስከ80 አመት፤ ከወንድ እስከ ሴት፤ የሃይማኖት መሪዎች፤ሃኪሞች፤ ፓሎቲከኞች፤ አስተማሪዎች፤ የጦር አመራሮች፤ የሃገር ባለዉለታወች ስላሉ እነሱን ያናግሩ የአማራን ህዝብ በእድሜ በጾታ፤ በሃይማኖትና በሌሎችም መስፈርቶች የሚወክሉ 39 ሺህ አማሮች በእነዚህ እስር ቤቶች ዉስጥ እዛዉ ከቤተመንግስትዎ የአንድ ታክሲ ፌርማታ እርቀት አሉለዎት ፡፡ አይ ያንሳል ካሉ ደግሞ ለአንድ ቀን ዝዋይ ካሉት 22ሺህ የአማራ እስረኞች በመኪና ወደ አዲስ አበባ የተወሰኑትን እስመጥተዉ ያወያዩዋቸዉ፡፡ 1/3ኛዉ የወልቃይት ህዝብም እዛዉ ቃሊቲ እና ማእከላዊ አለልወት፡፡ ጎንደር ድረስ መምጣት አያስፈልገወትም፡፡ ስለዚህም የእኛ የአማሮች በጣም አፋጣኝ ችግር ይሄ ነዉ፡፡ ለነዚህ መፍትሄ ነዉ የምንፈልገዉ፡፡ ኢትዮጵያችን፤ጀግኖች እነ አጼ ሚኒሊክ የወጡበት፤ የሃገር ዋልታ፤ ማገር ወጋግራ ቢሉን ለኛ ሲቃችን አይደለም እናዉቀዋለንም፡፡ እኛ የምንፈልገዉ ከእርስወ ተግባር ነዉ፡፡ ያኔ እናመሰግነወታለን፡፡ አይ የግድ መምጣት አለብኝ ካሉ ግን ቢያንስ እስከ 25 ሺህ የሚሆኑትን የአማራ እስረኞች ይዘዉ ይምጡ፡፡ወርቅነህ ገበየዉን አስከትሎ መምጣት ለኛ የሚፈይደዉ የለም፡፡
በመጨረሻም ፈረንጆች gaffe የሚሉትን በንግግር ዉስጥ የሚሳሳቱትን እርሰወም ትናንት በተደጋጋሚ ሲሳሳቱ ነበር፡፡ እሱ ስለማይጠቅም ለጊዜዉ አልፌዋለዉ፡፡
በተረፈ መልካም የስራ ዘመን ይሁንልዎ፡፡
Filed in: Amharic