>

«የዶክተር አቢይ ደጋፊዎች እንደምን አደራችሁ?» (ዮናስ ሀጎስ)

«እንዴዴዴ? ምነው ድምፃችሁ ሰለለ?»
አይ ዶክተር አቢይ ባንዴ የደጋፊዎችህን መጠን እንደዚህ ታሽቆለቁለው?
•°•
እኔ ግርም ይለኛል በእውነት… ሰዉ ዶክተር አቢይ መቀለ ሲደርስ ምን ዓይነት ንግግር እንዲያደርግ ጠብቆ እንደነበረ አላውቅም።
•°•
«እናንተ ሌቦች! እናንተ ዘራፊዎች! ሐገሪቷን ቦጠቦጣችኋት! መከላከያውንና ደህንነቱን ተቆጣጥራችሁ ሌላው ብሔር ስልጣን እንዳያገኝ አደረጋችሁት! በመወልወያ መጥረጊያ ሻጭነት ተሰማርታችሁ በድብቅ ለወያኔ እየሰለላችሁ… እናንተ ሞላጫዎች…!» ምናምን ይላል ብለው ጠብቀውት ነነረ መሰለኝ?
•°•
ሰውዬው ምን ሐሳብ አለበት! አምቦ በኦሮምኛ ያደረጋትን ንግግሩን ለትግራይ እንደሚስማማ አድርጎ ሞዲፋይ አደረጋትና ያቺኑ አነብንቦ ተመለሰ። ልዩነቱ አምቦ የኦሮሞ ሕዝብ በጠቅላላ ሳይሆን ቄሮ ብቻ በሞተርነት ሲወደስ ትግራይ ግን ሕዝቡና ክልሉ በሙሉ ሞተር ነው ተባለ። (በየስድስት ሴኮንዱ ለሞራሉ ይሰጠው የነበረው ጭብጨባ ሌላም ያስብል ነበረ በእውነት!)
•°•
ከዛ በተረፈ መቼም ትግራይ ድረስ ሄዶ እሱ አሁን የተቀመጠበትን ወንበር እንዲይዝ መስመር የጣሉትን የሕወሐት ሰማዕታት ሳያመሰግን መመለስ መቼም የማይታሰብ ነገር ነው።
•°•
የኢሳቱ «ተንታኝ» ኤርምያስ ለገሰ ባለፈው በዶክተር አቢይ ካቢኔ መካተት አለባቸው ያላቸውን ሰዎች ይፋ ሲያደርግ የቀልዱን መስሎኝ ካፌዙት መሐከል አንዱ ነበርኩኝ። ትላንትና ማታ በተሰራጨው የኢሳት ዝግጅት ላይ የዶክተር አቢይን የመቀለ ጉዞ አስመልክቶ የተቃወማቸውን ነገሮች «በታላቅ ቁጣ» ሲገልፅ ግን ሰውዬው ጤነኛነቱን ራሱ እንድጠራጠር አደረገኝ። እንደርሱ ላለ በኢህአዴግ ውስጥ ተኮትኩቶ ያደገ ሰው የኢህአዴግን ባህርይ ለመረዳት አቅቶት ዶክተር አቢይ ከተቃዋሚው ሐይል በሕዝብ ድምፅ እንደተመረጡ መሪ አድርጎ «ይህን ለምን አደረጉ ያንን ለምን አላደረጉም…» ሲል መስማት በእውነቱ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። ባጭሩ ከድምፁ የሆነ ነገር ጠብቆ እንዳላገኘ ሕፃን ልጅ ዓይነት ሆነብኝ።
ይልቅስ ትኩረት ሰመቼ ያዳመጥኩት ነገር «ሰውዬው የፌደራል ተወካይ ስለሆኑ በኦሮምኛም በትግርኛም ሳይሆን በአማርኛ ብቻ ማውራት ነበረባቸው…» ያላት ነገር ናት። በእርግጥ የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑን በደንብ እናውቃለን። የዛኑ ያህል ግን ሐገሪቷ የብዙ ቋንቋዎች ባለቤት መሆኗ መረሳት የለበትም። ሰውዬው አፉን የፈታው በኦሮምኛ ቋንቋ ሆኖ እንደገና አድማጩ በሙሉ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሆኖ በአማርኛ የሚናገርበት ምክንያት ግን ምንም አይታየኝም። ሰውዬው ትግርኛ ስለሚችልም ለትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪው በትግርኛ መልዕክቱን ማስተላለፉም ችግር የለውም። ኤርምያስ ይህቺን ነጥብ የአምቦው ጉብኝት ጊዜ ሳያነሳት ትላንት ለምን እንዳነሳት ስናስብ ግን ነገሮች መልካቸውን ይቀይራሉ።
•°•
ለማንኛውም ሰሞኑን ፋታ! ፋታ! ምናምን እያሉ በዶክተር አቢይ ፉርጎ ተሳፍረው ሲያደነቁሩን ከነበሩት «ደጋፊዎቻቸው» መሐከል የተወሰኑት ከባቡሩ መውረዳቸውን ትላንት አውጀዋል። ለኔ «100 ቀናት ይሰጠውና ይገምገም…» ስንላቸው «100 ቀናት በቂ አይደሉም ቢያንስ ስድት ወራት ሊሰጠው ይገባል!» ሲሉን የነበሩ ሰዎች በ12 ቀናት ውስጥ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ደርሰው ሰውዬውን ሲሰናበቱ ማየት ሐገራችን ምን ያህል የፖለቲከኛ እጥረት እንዳለባት የሚያሳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁኝ።
•°•
ለማንኛውም ግዴላችሁም… ሰውዬው አንዱ የፌስቡክ ወዳጄ እንደፃፈው «…ገና ስራ አልጀመረም!» ይህ ደግሞ ስልጣን ከያዘ 12 ቀናት የሞላው ግን ስራ ያልጀመረ የመጀመርያው መሪ ያደርገዋል። ስለዚህ በዚህ ሬከርድ እየተፅናናችሁ ሰውዬው የሙሽርነት ጉዞዎቹን አዳርሶ አራት ኪሎ ከሚከትምበት ቀን ጀምራችሁ «ትንሽ ጊዜ ስጡትና እዩት… ቂቂቂቁቂ!»
•°•
በቀጣይ ጉዞው ወዴት ነው? ደቡብ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋር ወይንስ ጋምቤላ?
•°•
የቀጣዩን የዶክተር አቢይ የጉዞ አቅጣጫ ንገሩኝና እኔ በእለቱ የሚያደርገውን ንግግር ከወዲሁ ፅፌ ላስደምማችሁ… ለምሳሌ በአማራ ክልል ያደርገዋል ብዬ ከምጠብቀው ንግግሩ ቀንጨብ አድርጌ ላስነብባችሁ…
•°•
«… ያለ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ ያለ ጎንደር ከባህር የወጣ አሳ ማለት ነው! የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት አሁን ላለው ቅኝት ዋናውን አስተዋፅዖ ያደረጉ ከመሆናቸው አንፃር ኢትዮጵያ ያለ አማራ ክልል ማለት በደንብ የተሰናዳ ግን ጨው ያልገባበት ዶሮ ወጥ ማለት ነው! እነ በላይ ዘለቀ ነፃነታችንን ለማስጠበቅ በጎበዝ አለቃ ተደራጅተው ያለ መሪ ጣልያንን ሲያርበደብዱ፤ ቆራጡ መሪያችን አፄ ቴዎድሮስ እጄን ለጠላት አልሰጥም በማለት ሽጉጡን ጠጥቶ በመሞት የኢትዮጵያዊነት ወኔን አርቆ የሰቀለ ጀግናን ያፈለቀ የአማራ ክልል አሁንም በልማቱ መስክ…»
•°•
ዶክተር አቢይ ውስጤ ነው!
Filed in: Amharic