>
5:13 pm - Tuesday April 19, 2687

የት ይደርሳል የተባለ ወይፈን ስጋው ሉካንዳ ተገኘ! (አቻምየለህ ታምሩ)

ያገራችን ሰው  ለጥሩ ያሰበውን አንድ ሰው ቅርስና ውርስ  ለትውልድ አርአያ ይሆን ዘንድ፣ ታሪኩን በወርቅ  ለመጻፍ ብራናውን ፍቆ ቀለም ሲበጠብጥ እንዳህያዋ ልጅ እንደ ውርንጭላ ሲሆንበት  «የት ይደርሳል የተባለ ወይፈን ስጋው ሉካንዳ ተገኜ ይላል።»
ፋሽስት ወያኔ ጫካ የገባው ለኤርትራ ነጻነት፣ በአማራ መቃብር ላይ  የታላቋን ትግራይ ሪፑብሊክ ለመመስረት እንጂ ለኢትዮጵያ ነጻነትና ዲሞክራሲ ለማምጣት አይደለም። ይህ ወያኔ ጫካ የገባለት  አለማ በድምጽ፣ በጽሁፍ፡ያውም በሶስት ቋንቋ[ በእንግሊዝኛ፣ በአማርኛና በትግርኛ] ተጽፎ ለነ ፖል ሔንዚ «ምስጋና» ይድረስ የአደባባይ ሚስጥር የሆነ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ስድሳም ሆነ ሰባ ሺህ የትግራይ ወጣት ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ሲዋጋ ቢሞት፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠር የአካል ጉዳተኛ ቢሆን  ለኤርትራ ነጻነት፣ በአማራ መቃብር ላይ  የታላቋን ትግራይ ሪፑብሊክ ለመመስረት እንጂ ለኢትዮጵያ ነጻነትና ዲሞክራሲ ለማምጣት አይደለም።
ሰባ ሺህ የትግራይ ወጣት ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ሲዋጋ መሞቱ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠር የትግራይ ወጣት የአካል ጉዳተኛ መሆኑ   እንደ ሰው የሰው መጎዳት ቢያሳዝንም  የትግራይ ወጣቶች ሞቱለትና  ቆሰሉለት የሚባለውን  አላማ ግን  ትክክል አያደርገውም። ዓብይ አሕመድ «የትግራይ ሰማዕታት» ያላቸውን የትግራይ የገበሬ ወታደሮች ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲና ነጻነት ለማምጣት የተሰው ሰማዕታት አድርጎ በትግርኛ ባደረገው  ንግግር አቅርቧቸዋል። በዚህ ንግግሩ ዓብይ አሕመድ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ሆኗል።
ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ለመግባት ሲወስን በጎንደር፣ በወሎ፣ በሸዋ፣ በጎጃምና በወለጋ  ሲያልፍ  ገበሬው የተሻለ ነገር የሚመጣ መስሎት ቋንጣና ቆሎ ሕይወቱንም ጭምር ሳይሳሳ ገብሮለታል።  ሆኖም ግን ውሎ አድሮ በጊዜያዊ ፕሮፓጋንዳ ደብቆት የነበረውን እውነተኛ  ባህሪውን በማውጣት የታገለለትን አላማ   ታሪካችንን በማበሳበስ፤  አገራችንን እየቆረጠ በመሸጥ፤   ሲቪሉንና ወታደሩን ከስራው በመቀነስ በትግራይ ተወላጆች ሲተካ፣ ገበሬውን እትብቱ ከተቀበረበት ካያት ከቅድሚያ አያቱ አገር እያፈናቀለ ሲያሳድድና ሲገድል፤ አርሷደሩ በማንነቱ ምክንያት  ሞትና በግፍ መጋዝ የሕይወቱ አካል ሲሆን በማየቱ፤ ለጊዜው  ተከድኖ የነበረው የወያኔ  አላማ  ሳይውል ሳያድር ምርጊቱ  ተከፍቶ   የታገለለት  ለሁሉም  መታየት ሲጀምር፣  ለነጻነት ታገልሁ ያለው ነውረኛ ቡድን  የታገለው ነጻነትንና ዲሞክራሲን ለመቅበር  መሆኑን ሲረዳ  የተጫነበርን የባዕድ   አገዛዝ  ውስጡን ከፍቶ አይቶ   አንቅሮ መትፋቱን  ለመግለጽ እንዲህ ሲል ቋጠረ፤
ጠጅ መስሎን ነበር ምርጊቱ ሲከፈት፣
ጠላነው ይመለስ ወደነበረበት።
ትናንትና መለስ ዜናዊ «እንኳን ከእናንተ ከወርቅ ሕዝብ ተፈጠርኩ፤ እንኳን ከሌላ አልተፈጠርሁ፤ እንኳን እንደ ወርቅ በእሳት ከተፈተነ ሕዝብ ወጣሁ!» ሲል የተናገረውን መረን የለቀቀ የዘረኝነት ንግግር ብዙዎች ተስፋ የጣሉበት ዓብይ አሕመድም «በእሳት የተፈተናችሁ ወርቆች ናችሁ» በማለት  በመድገም  ከነውረኛው ዘረኛ መለስ ዜናዊ  በኋላ ሰውነትን በወርቅ፣ በመዳብና በጨርቅ በመለካት  ሁለተኛው  ሰው ሆኗል። ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራና የኦሮሞ ልጆች በትግራይ ወታደሮች በግፍ ተገድለዋል፤  የሰባትና የስድስት ወር ነፍሰ ጡሮች፣  የሶስት አመት ሕጻንና የሰባ  አመት አዛውንት ጭምር  በትግራይ ወታደሮች በጭካኔ ተረሽነዋል፤ እናት በልጇ አስከሬን ላይ ተቀመጭ ተብላ ተደብድባለች፤ እምቦቀቅላ ሕጻናት በጥምቀት በዓል ላይ በትግራይ ወታደሮች ጭንቅላታቸው ተበርቅሶ በብቀላ ታርደዋል፤ ታቦት  በትግራይ ወታደሮች ባሩድ አረር ታፍኖ ተሸካሚው ቄስ ራሱን ስቶ ታቦቱን እንደያዘ መሬት ወድቋል። ይህንን ሁሉ ግፍ የተቀበልነው፣ ከባድ   መስዕዋትነት የከፈልነው  በኢትዮጵያ ውስጥ እኩልነትና ዲሞክራሲ ይመጣ ዘንድ ነበር።
የሚያሳዝነው  ግን የዚያ ሁሉ መስዕዋትነት ውጤት የሆነው ዓብይ አሕመድ መቀሌ ሄዶ የሕሊና ጸሎት ያደረገውና «ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት ያለው» ኢትዮጵያ ውስጥ እኩልነትና ዲሞክራሲ ይመጣ ዘንድ ሳይታጠቁ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወጥተው  በትግራይ ወታደሮች ተገድለው ሳይመለሱ ሰማዕት ሆነው ለቀሩ  የአማራና የኦሮሞ ልጆች ሳይሆን  ለኤርትራ ነጻነትና  በአማራ መቃብር ላይ  የታላቋን ትግራይ ሪፑብሊክ ለመመስረት  መሳሪያ ታጥቀው  ራሱ ዓብይ ጠቅላይ ሚንስት ሆኖ የተሰየመ እለት  ካራ ማራ ላይ  ለኢትዮጵያ አንድነት ሲል ተዋደቀ ሲል ያሞካሸውን  የኢትዮጵያን  ሰራዊት  ለመውጋት ዱር ቤቴ ያሉትን  አጥፍቶ ጠፊዎችና ዛሬ እየገደሉን ያሉትን ወያኔዎች  ነበር።  ከሁሉ በላይ  ዓብይ አሕመድ ኦሮምያና አማራ  በሚባሉት ክልሎች  ተፈጠረ ባለው ቅጭት የትግሬዎች  ንብረት በመጎዳቱ  ማዘኑን  ለታዳሚው ገልጾና ድርጊቱን አውግዞ፤ በትግራይ ወታደሮች የተረሸኑት  በሺዎች የሚቆጠረው  የአማራና የኦሮሞ ልጆች ነፍስ ግን ምንም ሳይመስለው መቅረቱም  በጣም ሳይገርመኝ አልቀረም። መቼ ይሆን  በኛ ላይ የሚሰየሙት  የወያኔ እንደራሴዎች  በአስር ሺዎች የሚቆጠረው የኛ ነፍስ ቢያንስ  የአንድ የትግራይ ቱጃርን   ሀብት ያህል እንኳ የሚያሳስባቸው??
የሆነው ሆኖ ሰዓቱ እየቆጠረ ነው፤ ሰውም ዓብይ የሚለውን ሁሉ እየተመለከተ ነው፤ «ጠቅላይ ሚንስትር» ተብሎ ለመሰየም የበቃበትን አገራዊ ችግር ፈጽሞ ዘንግቶና  አሳንሶ «ትንሽም ችግር ካለች እሷን ማባባስ የሚፈልጉ፣ ትንሿ  ችግር ካልተባባሰች የእለት ጉርሳቸውን የማያገኙ፣ ኦሮምያ ሁሉ እስር ቤት ሆኗል እያሉ በውሸት የሚያባብሱ፣ ወዘተ. . . » በማለት  በየሚሄድበት የሚያገኘው ሕዝብ እንዲሰማ የሚፈልገውን  በማውራት የሚጠመድ ከሆነ የወያኔን  ድርጊት አይቶ «ጠላነው ይመለስ  ወደ ነበረበት» ያለው ሕዝብ   እንደ ኃይለ ማርያምን ካልሆንሁ  ሞቼ እገኛለሁ የሚለውን ዓብይንም «ጠላነው ይመለስ ወደነበረበት» የሚልበት  ቀን ሩቅ አይሆንም።
https://www.facebook.com/alebachewguadie/posts/1291520460980709
Filed in: Amharic