>
5:01 pm - Friday December 2, 1481

ፋታ ለማን? (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

 

በጃንሆይ ዘመነ መንግስት ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ፋታ ስጡኝ እያሉ ቢጣሩም፥ ሰሚ አጥተው አቶ ጥድፊያ ኢትዮጵያን ላለፉት ዓመታት ለመከራ አሳልፎ እንደሰጣት እናውቃለን። ከታሪክ ጠባሳ ካልተማርን ታሪክ ራሱን ይደግማል። ለዶ/ር አብይ አህመድ ፋታ እንዲሰጥ የሚያስፈልገው ለእርሳቸው ስልጣን ማራዘሚያ አይደለም። ፋታ የምትፈልገው ኢትዮጵያ ናት። አሁንም ዶ/ር አብይን የሚያዋክቡ ወገኖቻችን ዓይናቸውን ከእሳቸው ላይ አንስተው እናት ሀገር የምትባለው ኢትዮጵያ ያለችበትን ምጥ ማየት ቢችሉ መልካም ነው። ጊዜው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለመወለድ ጫፍ ላይ ያለችበት ወቅት ይሆን ይሆንን? በማለት የአዋላጅነት ሚና እንድንጫወት ሁላችንም መጣር ያለብን ወቅት ነው። ከጥንቃቄ አንጉደል።

ዶ/ር አብይ የሕዝብን ድምፅ አድምጠው፥ ይህንንም የሕዝብ ድምፅ ገንዘብ በማድረግ ከሌሎች ጋር ተቀናጅተው በሕዝብ ትግል እየተደገፉ እዚህ ደርሰዋል። በዚህም ምክንያት መላውን ሕዝብ ያስደመመና ከተዐምር የማያንስ ጉዳይ የሆነውን ኢትዮጵያዊነትን ሞሽረውና ሸልመው ሲያበቁ፥ ኢትዮጵያዊነትን ከወደቀችበት ጓዳ አውጥተው ብርሃኗ እንዲፈነጥቅ አድርገዋል። ለውስጥም ሆነ ለውጭ ተፎካካሪ አካላት የፍቅር ጥሪ በማድረግ ብዙ ተስፋ የሰነቀ ንግግር ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በማስረገጥ አሳውቀዋል። እርቅና መግባባት በምድራችን ዕውቅና ያገኘበትም ወቅት ነው። ሙያ በልብ ነው የሚለውን መርህ ያነገቡ የሚመስሉትን እኚህን የኢትዮጵያ ልጅ ማስተዋልን በተፋታ መልኩ ጥላሸት እየቀቡ መሞገት አሁን ጊዜው ነውን? “ሰሚ ያጣ ሕዝብ” በሚል ርዕስ የዛሬ ሁለት ዓመት (2016) ለንባብ ካበቃውት ፅሁፍ ልጥቀስ፦

“ከእንግዲህ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የለም። ማንም ላይታመን፥ ሕዝቡ ራሱን ብቻ ሊያምን ተነስቷል። ስልጣን የሕዝብ ነው እያሉ በስሙ የሚነግዱ ከእንግዲህ በቃችሁ ተብለዋል። ስልጣን የሕዝብ መሆኑን የሚናገር ሳይሆን በሕዝቡ ለመመራት ራሱን የሕዝቡ ተከታይ የሚያደርግ ብቻ ይፈለጋል። ከትልቅ ትዕግስት በሁዋላ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሕዝቡ የተነሳው፥ ለመንግስት ስልጣኑን የሚያስረዝምበትን መላ ለማፈላለግ፥ ወይም ለተቃዋሚ የስልጣን ውርስ እንዲያደርጉ ለማመቻቸት ሳይሆን፤ መሪዎቻችን የሕዝቡን ድምፅ እንዲሰሙ እና ስልጣንን ለባለቤቱ (ሕዝብ) ማስረከቢያውን መንገድ እንዲፈጥሩ ነው። ፈሪሃ ፈጣሪ ያለው ይህ ሕዝብ አምላክ እንዳለለት ይታወቅለት።”

ከዶ/ር አብይ የቁርጠኝነት ቃል በመነሳት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰሚ አግኝቼ ይሆንን? እያለ በተግባር ለማየት በተጠንቀቅ በሚጠብቅበት በዚህ ወቅት፥ አፍራሽ የሆነ ነገር መናገርና ማደናገር ለማን ይጠቅማል? ይልቁንስ እነዚህ ትዕግት የጎደላቸው ወገኖቻችን የትግላቸውን ስልት ጊዜውን እንዲመጥን በማደስና ከሕዝብ የልብ ትርታ ጋር በማጣጣም ፋታ ለኢትዮጵያ ቢሰጡ አይበጅምን? የሩስያው ፕሬዚዳንት ጎርቫቾቭና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሬገን “እመን ግን አረጋግጥ” እያሉ ታሪክ ሰሩ። ይህንን መርህ በመጠቀም ትግሉን በቀና መንፈስ አጠናክሮ ገንቢ በሆነ አካሄድ መንቀሳቀስ ማስተዋል ነው።

ለሁላችንም ልቦና ይስጠን።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

ኢሜል፡ ethioStudy@gmail.com

Filed in: Amharic