>
5:16 pm - Monday May 24, 3915

ጎንደር አብይን እንዴት ተቀበለችው? (ጌታቸው ሺፈራው)

ጠዋት 1:30 አካባቢ  በመኪና እየዞሩ እየለፈፉ ነው። ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዲቀበል። ሆኖም ሰሞኑን  ለመቀበል የሚገቡት ሰዎች ተለይተው እንደታወቁ፣ ወረቀትም እንደደረሳቸው ሕዝቡ ሰምቷል። ካድሬ ነው የሚሰበሰበው ተብሏል። ስለዚህ ለመሄድ ፈቃደኛ አይደለም።
 ወደ ፋሲለደስ ስቴዲየም ከመግባቴ በፊት ቡና ልጠጣ ተቀምጫለሁ። ሁለት ወጣቶች ቡና እየጠጡ ያወራሉ። “በሙሉ ካድሬ ነውኮ የሚገባው” ይላል አንዱ።
“እኔ ለምሳሌ ለመታዘብ ልገባ ነው፣ ለምን አትገቡም?” አልኩት። “ምን ላረግ?   የተለየ ነገር አይመጣም ባክህ። ያው ነው! ሕዝቡም መረረው መሰለኝ ከማሾፍ ውጭ ሌላ ነገር አያደርግም።” አለኝ። ጓደኛው ዶ/ር አብይ ስለ ወልቃይት በተናገረው እንደበሸቀበት አወራኝ።
እነሱን ተሰናብቼ ወደ ስቴዲዬሙ ሳቀና መሃል ላይ ባጃጅ አገኘሁ። ዝግ ስለሆነ የተወሰነ ርቀት ብቻ ነው የሚሰሩት።
“ስቴዲዬም ልሄድ ፈልጌ ነው። የት ድረስ ትወስደኛለህ?”
“እስከ አውቶፓርኩ አደርስሃለሁ”
“አንተ አትገባም እንዴ?”
“ምን ያደርግልኛል? ለወጣቱ ብድር ያመጣል?”
“እኔ እንጃ! የሚባለውን ከሰማህ ብየ ነው።”
“የሚባለው ምን ያደርግልኛል?”
ምንም ሳልመልስለት ወርጄ ወደስታዲዬም።
የመጀመርያውን የፍተሻ መስመር አለፍኩ!
ሁለተኛው የፍተሻ መስመር ላይ  ስደርስ በርካታ ሰልፎች አሉ። ሰልፈኞቹ ፊት ለፊት በርካታ አማራ ክልል ልዩ ኃይል አለ። ከእነሱ ቀጥሎ ፈደራል  ፖሊስ ይታያል።
እንደመጀመርያው ፍተሻ መስመር መስሎኝ በተናጠል ላልፍ ስል “ተሰለፍ” ተባልኩ። ተማሪዎች በየ ትምህርት ቤታቸው  ተሰልፈዋል። ገበሬዎች በየ ወረዳቸው ተሰልፈዋል። “አርማጭሆ፣ ወገራ፣ ደንቢያ
…ወደዚህ!” ይባላሉ። የጥቃቅንና ሌሎች አደረጃጀቶች አሉ።
ፖሊሱን “እኔ በግል ነው የመጣሁት። ማን ጋር ልሰለፍ አልኩት?”
ከፖሊሱ ጎን ሆኖ  ተሰላፊውን በየ ወረዳው የሚጠራ ካድሬ “እንዴት በግል?” ብሎ ጠየቀኝ።
“የከተማው ነዋሪ በግሉ መጥቶ መከታታል አይችልም?” አልኩት። ግራ ገባው! “ሰው ግን ምን ነክቶት ነው የማይደራጀው?” ብሎ መሰለኝ። የካድሬ ነገር።
ፖሊሱም በቡድን ነው ሲያሰልፍ የቆየው። እንደኔ ብቻቸውን የመጡ የተወሰኑ ሰዎች ከኋላየ ቆመዋል። ፖሊሱ በቡድን አሰልፍ ስለተባለ “በቃ ከአንዱ ቡድን ግባ! ብቻህን ማለፍ አትችልም” አለኝ።
ወደ ግራዬ ሳይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተሰልፈዋል። በቀኝ በኩል አርሶ አደሮች ተሰልፈዋል። ህፃናት ጋር መሰለፉ ትንሽ ከበደኝ። ግራር መስየ ልታይ ሆነ። ፖሊሱም ጭንቀቴ ገባው መሰለኝ።
“በቃ ከአርማጭሆ ጋር ተሰለፍ! የአርማጭሆ ወረዳ ነህ” ብሎ ሳቀብኝ።   በአይሱዙ ተጭነው ከመጡት የአርማጭሆ ገበሬዎች ጋር ተሰልፌ ገብቻለሁ።
ወደ ስቴዲዬሙ ስገባ ከውጭ ካየሁት በባሰ በተማሪዎች፣ በእናቶችና ገበሬዎች ተሞልቷል።  ከጥላ ፎቁ ጎን ያለው አንድ አካባቢ በሙሉ ተማሪ ነው። ትንሽ እንደተቀመጥን ሙዚቃ ተከፈተ።
ማረሻው ምንሽር መጎልጎያው ጓንዴ፣
የእነ ስበር ሀገር ወልቃይት ጠገዴ!
ወዲያውኑ ደህና ሲሰራ የነበረውን ሞንታርቮ ነካክተው አጠፉት። በድንጋጤ አበላሹት መሰለኝ። ተሰብሳቢው ገብቶታል። ሙዚቃው መቋረጥ የለበትም ብሎ አፏጨ።
የተቀባን፣ የገዱንም የአብይንም ንግግር በደንብ ማዳመጥ አልተቻለም። ሰው አብይ ተናግሮ ሳይጨርስ መውጣት ጀመረ። ዶ/ር አብይ ተገድዶ ነው የመጣው። ትግራይ ክልል ያደረገው ንግግር ብዙ ሰው አላስደሰተም። ብአዴን ተጨንቆ ሰንብቷል። የወልቃይት ጥያቄ እንዳይነሳበት። ይች ጥያቄ በአለቆቹ ታስኮረኩመዋለች። ስለዚህ አደራጅቶ ማስገባት አለበት። ተማሪ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ፣ ገበሬ………። ተደራጅቶ የሚገባውን  ለማመላለስ የጎንደር መኪና ባለሀብቶች ግዴታ ተጥሎባቸዋል። የአሽከርካሪ ማሰልጠኛዎችም እንዲሁ።
ይህ ግን በቂ አልነበረም። ትናንት ከሰዓት የከተማው ባለስልጣናት የቅማንት ጥያቄ የሚያነሱትን ሰብስበው ነበር። ዛሬ የወልቃይት ጥያቄ በባነር ያሰሩ ወጣቶች እንዳይገቡ ሲከለከሉ፣ የቅማንት ተፈቅዷል። ለወልቃይት ጥያቄ አፀፋ መሆኑ ነው። በዚህ ላይ የአማራ አክቲቪስት ነኝ የሚለው ሁሉ አጋጣሚውን እንዴት መጠቀም እንዳለበት ጠንቅቆ ያወቀ አይመስለኝም። አብይ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ አይደለችም” ብሎ ተናግሮ አምቦ ላይ ስብሰባ ቢያደርግ እነ ጃዋር ካድሬውን ሳይቀር ያስጮሁታል። ወደዚህ ሰፈር ግን   ቁሞ ቀርነት እየበዛ መሰለኝ። (ስለ አማራ አክቲቪስቶች ጉዳይ ሌላ ጊዜ በስፋት ብመጣ ይሻላል) ብአዴን  አብይን ሹልክ አድርጎ ከስቴዲየም ይዞት ወደ ጎሃ አቅንቷል። በመጠኑም ቢሆን ለአብይ ጥሩ ሆኖለታል። ንግግሩን ሳይጨርስ ከወጣው ሕዝብ ውጭ የበረታ ተቃውሞ አልገጠመውም።  ግን ከሕዝብ ጋር ተወያየሁ ለማለት አያስችለውም። የብአዴን ጉዳይ እንደሁሌው አሳፋሪ ነው። የ9 እና የ10 አመት ህፃናትን ሳይቀር ሰብስቦ አብይን ተቀብሎታል።ይህን ካወቀ አብይም የሚገረም ይመስለኛል! ያም ሆነ ይህ በአማራ ክልል፣ የአብይ ካድሬዎቹ የብአዴን ካድሬዎች  ናቸው። አብይን የተቀበሉት ድሮ መለስን በየ ስቴዲየሙ ሲቀበሉት የነበሩት አደረጃጀቶች ናቸው።  ከሕዝብ ጋር ተወያየሁ ማለት አይችልም።
Filed in: Amharic