>
5:09 pm - Wednesday March 3, 3706

መጋረጃው....!?! (ደረጄ ደስታ)

እያየን ነው። አይተናቸው ሰምተናቸው እማናውቃቸው ተቋማትና ግለሰቦች ብቅ ብቅ እያሉ ስለ ሥራቸው መግለጫ መስጠት ጀምረዋል። አምስቱ የፍትሕ ተቋማት የሚባሉት የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚያገናኟቸው የሥራ ዘርፎች ላይ “ውጤታማ” ሥራ እያከናወኑ መሆኑን መግለጻቸውን አንብበናል። በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር ከሚገኙ ሰባት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ፣ ከፍተኛ ቅሬታ ሲያስነሱ የቆዩ ሥር የሰደዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን “መፍታቱን” አስታወቀ- እሚል ዜናም ከሪፖርተ አይተናል። ውጤታማነታቸውንና ችግር ፈቺነታቸውን ግድ የለም እንተሳሰባለን። ያን ለማድረግ ግን የቱ ተቋም ምን እንደሚሰራ፣ ማን ምን እንደሆነ፣ በአደባባይ ማወቁ በራሱ አንድ ነገር ነው። ከሰዎች መብት፣ ህይወትና ተጠያቂነት አኳያ፣ መሪ ተዋናይ፣ ወይም አዛዥና ታዛዥ አስፈጻሚዎች የሆኑት፣ እነማን እንደሆኑ ማወቁ በጎ ጅምር ነው። የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረ ዮሐንስ ተክሉንም ሆነ አምስቱን የፍትሕ ተቋማት መሪዎች መልክ ማየታችን ጥሩ ነው። በሰው አገር ሲ.አይ.ኤይ የኤፍ.ቢ.አይ መሪዎችን እንደምናይ፣ ወደፊት ደግሞ የደህንነት ሹሞቹን እንደ ጌታቸው አሰፋ እና ምክትሎቻቸውን እነ ሀደራ አበራ ያሉትን እያየናቸው “ውጤታማ” ሥራዎቻቸውን ሪፖርት ቢያደርጉልን ነገሮች እየተገለጡ ይመጣሉ። በደፈናው ወያኔ በዚህ ገብቶ ወያኔ በዚህ ወጥቶ ማለቱንም ያስቀራል።
በሌላም በኩል ከኮማንድ ፖስቱ በስተጀርባ ሆነው ያሻቸውን እያደረጉ በቀላጤ እሚያሳዉቁን የሠራዊቱ አዛዦችም ራሳቸው እየወጡ መግለጫ እሚሰጡበት አግባብ አልፎ አልፎ ቢኖርም አይከፋም። አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር “ያሰሩታል ወይስ አያሰሩትም?” እየተባለ እሚፈራና እሚጠረጠረው ኃይልም ተለይቶ መታወቅ ይኖርበታል። ለነገሩማ መሆን የነበረበት፣ ሠራዊቱ እኛ ኢትዮጵያውያንን “ያሠራናል ወይስ አያሰራንም?” የኛ ነው ወይስ የማን ነው? ተብሎ ነው መጠየቅ የነበረበት፣ እንጂ ሠራዊቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተደቀነ ወይም በሳቸው የተደገነብን ተደርጎ መታየት አልነበረበትም። እኛ ለውጥ ፈልገናል ይህን ለውጥ ሠራዊቱ ይፈልገዋል ወይስ አይፈልገውም ተብሎ እሚጠየቅበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ለውጥ እማይፈልግ ከሆነ መለወጥ ያለበት ሠራዊቱ እንጂ እኛ መሆን አይገባንም። ስለዚህ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ስለ ሰሞኑ ሁኔታ እስከዛሬ በድረ ገጹ ሳይቀር በዜና እንኳ ሳያቀር ምንም ትንፍሽ ያላለው ሠራዊቱ ተጠያቂነቱን በአሰቸኳይ ቀርቦ ማስረዳት ይኖርበታል። የሰራዊቱ መሪ የሆኑት ጀኔራል ሳሞራ የኑስም በጡረታ የተገለሉ ሆነው ሳለ፣ አሁን ድረስ ሥልጣናቸው ላይ ናቸው። እንደሚባለው ኮንትራታቸውን በየዓመቱ ስለሚያሳድሱ፣ አሁን ዓመታዊ የዕድሳት ጊዜው አልቆ፣ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር መንግሥት ጋር “የአድስ አላድስም” ግብግብ መያዙ እየተሰማ ነው።
የደህንነቱም ሹም የሆኑት አቶ ጌታቸው በፓርቲው (በህወሃት ሥራ አስፈጻሚነት) እና ገለልተኛ መሆን ይገባዋል በሚባለው የደህንነት ተቋም ኃላፊነታቸው መቀመጥ ስለማይኖርባቸው ከሁለቱ አንዱን የግድ መምረጥ እንዳለባቸው እየተነገራቸው መሆኑም እየተነገረ ነው። “እሺ በቃ ደህንነቱን መርጫለሁ!” ቢሉ ምን ሊደረግ እንደሚችል ባይታወቅም፣ ተጠያቂ መሆን መጀመራቸው በራሱ አንድ ነገር ነው። እየተባለ እየተሰማ ያለው ነገር ሁሉ እያስገረመ እያስደመመ መሄዱ እርግጥ ቢሆንም ህዝቡ ግን ጥያቄውን እነዚህ ሰዎች “ያሰሩናል ወይስ አያሰሩንም” ማለቱን ትቶ “ይሰሩልኛል ወይስ አይሰሩልኝም” እሚላቸውን ወገኖቹን አደራጅቶ እሚመርጥበት ትክክለኛ የምርጫ ሥርዓት ጥያቄን ቢያቀርብ ይበጀዋል። አብይም ህዝብ እሚፈልገውን እንዲመርጥ ማድረግ እስኪችሉ ድረስ የኢህአዴግ ሰው ሆነው ይቆያሉ። ህዝብም ራሱን አደራጅቶ የራሱን ሰዎች አዘጋጅቶ ምርጫውን ቢጠባበቅ ይበጀው ይመስለኛል። ካለበለዚያ ኢህአዴግን በእንዶድ እያጠቡ ሰው ፊት አሳምረው ያቀረቡት ሰዎች መሰንበታቸው አይቀርም።
ታዲያ ለዚህ መድሃኒቱ ህዝብንም እንመራለን እሚሉ ሰዎች ከመጋረጃው በስተጀርባ ብቅ ብለው ከወዲሁ ለይተን እያወቅናቸው እንዲቆዩ ማድረግ ነው። የምርጫ ሰሞን ያለው ግርግርና ሽኩቻ ያመጣውን ጣጣ የ2005ቱ ምርጫ አስተምሮናል። ምርጫ ቦርዱንም ሆነ ሁሉንም ነገር ገላልጠን ክፍትና ነጻ አድርገን እንየው “እኛን ሊያሸንፍ እሚችል ማንም ተቃዋሚ የለም” እሚሉ በርካታ ወገኖቹ ከኢህአዴግ መጋረጃ በስተጀርባ መኖራቸውንም አለመዘንጋት ነው። በቅንጅት ጊዜ አቶ መለስ ዜናዊ የወጣላቸውን ሰልፈኛ ብዛት አይተው “ይህን ማዕበል ይዘን ልንሸነፍ አንችልም” ያሉትን ባንዘነጋም፣ ይህኛው ሊለይ መቻሉንም አለመርሳት ነው። እስከዛሬ የቆምንላቸው ጥያቄዎች ሀሳቦችና የዘመርንለት አንድነትና ኢትዮጵያዊነት እየተወሰደብን መሆኑን እያየን ነው። ታዲያ ቢሆንስ “እኛ እኮ ድሮም ጥያቄያችን እንዲመለስና ኢትዮጵዊነት ሰፍኖ አገር ሰላም ሆኖ ማየት ነው…” እሚሉ ወንድሞቻችንም ከወዲያኛው መጋረጃ ሲንሾኳሾኩ እየሰማን ነው። አንድ እማንክደው እውነት ግን አለ። እነ ዶ/ር አብይ፣ ለማም ሆኑ ገዱ ህወሓትን አሸንፈው መጥተዋል። ህወሓት ግን ካሁን በኋላ ሊጠቀምባቸው ካልሆነም ጠምዝዞ ሊጥላቸው አይችልም ብሎ ለሰከንድ ማሰብ አይቻልም። እኛስ ለኛ ዓለማ እንጠቀምባቸው ወይስ አግዘን እንጣላቸው? ወይስ የአብይና ጸረ አብይ ሆነን መከፋፈያችን ይሁነን? እንግዲህ ብልህ አንተ ታውቃለህ!
Filed in: Amharic