>

“ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ጎርባቾቭ እንዲሆኑ እንፈልጋለን” እስክንድር ነጋ ከአዲስ አድማስ ጋር ያደረገው ቆይታ

     “ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ጎርባቾቭ እንዲሆኑ እንፈልጋለን”

  • ህዝቡ ወደ ጎዳና የወጣው ነፃነትን ፍለጋ እንጂ ኢህአዴግን ለማደስ አይደለም
 • የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈጸመው በፖሊሶች ሳይሆን በሥርአቱ ነው
 • ትግሉ ዳር እስኪደርስ በውጭ ሃገር እኖራለሁ ብዬ አላስብም

     ለ6ዓመታት ከታሰረ በኋላ በቅርቡ ከእስር የተለቀቀው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ ከሰሞኑ የዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ በክብር እንግድነት ለመገኘት ወደ ኔዘርላንድ ተጉዟል፡፡ ጋዜጠኛው የተጀመረው ትግል ዳር ሳይደርስ በውጭ አገር የመኖር ሃሳብ እንደሌለው ጠቁሟል፡፡ ከጉዞው በፊት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን አግኝቶ ያነጋገረው ሲሆን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከህዝብ ጋር እያደረጉ ስላሉት ውይይት፣ ከጠ/ሚኒስትሩ ስለሚጠብቀው ጉልህ ለውጦች፣ ከተቃዋሚዎች ጋር መደረግ አለበት ብሎ ስለሚያምነው ድርድርና ሌሎችም ጉዳዮች አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡ እነሆ፡-
ከእስር ከተፈታህ በኋላ ወደተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጉዘሃል፡፡ የጉዞው ዓላማ ምን ነበር?
በየአካባቢው እየተጋበዝን ነበር የምንሄደው። ነገር ግን ጉዞዎቹ በሚስጥር ነበር የሚደረጉት፡፡ ምክንያቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ነን፡፡ ነገር ግን ደሙን አፍሶ ከእስር ያስፈታን ህዝብ በመሆኑ  በየአካባቢው እየሄድን ምስጋና ማቅረብ ነበረብን፡፡
በተዘዋወርክባቸው አካባቢዎች በህዝቡ ላይ ያስተዋልከው ስሜት ምንድን ነው?
ህዝብ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ያስፈልጋል የሚል ስሜት ይንጸባረቃል፡፡ አሁን በኢህአዴግ ውስጥ የተደረገው ሽግሽግ በቂ አይደለም፤ ወደ ስር ነቀል ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ልንሄድ ይገባል የሚል ስሜት እንዳለ ነው የተረዳሁት፡፡
ለህዝቡ የለውጥ ጥያቄ፣ የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር መመረጥ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል?
ለለውጦች ተጨማሪ መንገድ ይከፍታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ዓለማቀፍ ማህበረሰቡን ለማነጋገርም እድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ እነሱም ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው ተረድቻለሁ፡፡ በዲፕሎማቶቹ ዘንድ ጠ/ሚኒስትሩ የለውጥ ፍላጎት አላቸው የሚል እምነት ነው የሚንጸባረቀው፡፡ ባለፉት ንግግሮቻቸው ጥሩ ነገር ሰምተናል፤ ግን በወልቃይት ጉዳይ ህዝብን ቅር ያሰኘ ነገር ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንጻር  በንግግራቸው ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠበቁ ጉልህ ለውጦች ምንድን ናቸው?
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠበቀው ለቀጣዩ ምርጫ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ብቻ አይደለም፤ሁለት አበይት ነገሮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት ነው፡፡ ከዚያም አዋጁ ከተጣለ በኋላ የታሰሩ ግለሰቦችን ያለ ቅድመ ሁኔታ መፍታት ነው፡፡ ሁለተኛ ሃገሪቱን ወደ ሰላማዊ ሽግግር ማስገባት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉን አቀፍ ድርድር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉን አቀፍ ድርድር ሲባል፤ በህጋዊም ሆነ ከዚያ ውጪ ባሉ መድረኮች ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚያካትት የድርድር ጉባኤ መጥራት ነው፡፡ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚታገሉ ሶስት ድርጅቶችን፡- “ኦነግ”፣ “ግንቦት 7” እና “ኦብነግ”ን ማካተት አለበት ድርድሩ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ለውጥ የመጣው በገዥው ናሽናል ፓርቲና በኤኤንሲ መካከል ድርድር ከተካሄደ በኋላ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በሽብርተኝነት በተፈረጁ ድርጅቶችና በኢህአዴግ መካከል ድርድር ሲካሄድ ነው፡፡ ይሄ ካልተደረገ ህዝብ የሚፈልገው ለውጥ መጥቷል ማለት አይቻልም፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ለሚደረገው ምርጫ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማመቻቸትም ይሄ ወሳኝ ነው፡፡ ምርጫው ገና ሩቅ ነው፡፡ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ግን ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ለሚደረገው ድርድር ነው፡፡
ምን አይነት ድርድር ነው  መንግስት ማድረግ ያለበት?
በዚህ ረገድ ምሳሌ የምትሆነን ደቡብ አፍሪካ ነች፡፡ ደቡብ አፍሪካ ያደረገችው ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በድርድር የመጣ ነው። ይሄ ድርድር ውጤት ካመጣ በኋላ ለዓለም ሞዴል ሆኗል፡፡ በደቡብ አሜሪካ፣ በእስያ ሃገራት ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል፡፡ በአፍሪካም በተለያዩ ሀገራት ውጤት አምጥቷል፡፡ በኢትዮጵያም ውጤታማ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የተሞከረ ሞዴል እያለ ሌላ ለማፍለቅ መጨነቅ የለብንም። ዋናው ነገር ያለ ቅድመ ሁኔታ ሁሉንም ወገን በድርድር መድረክ ማሳተፍ ነው፡፡ የዚህ ድርድር ውጤት ምንም ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ በብዙ ሃገራት ይህ ዓይነቱ ድርድር በሽግግር መንግስት ይደመደማል፡፡ የሽግግር መንግስት ማለት ደግሞ የሚያስፈራ ነገር አይደለም፡፡ በቀላሉ የተለያዩ ድምፆችን የሚወክሉ አካላት የተሳተፉበት መንግስት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በካቢኔ ውስጥ “ግንቦት 7”፣ “ኦነግ”፣ “መድረክ”፣ “ሰማያዊ ፓርቲ”ን ወዘተ ማሳተፍ ማለት ነው፡፡ በብዙ አገሮች የተደረገው ይሄ ነው፡፡ ድርድሩ ሲካሄድ ምናልባት እንደ ደቡብ አፍሪካ በዝግ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ግን የሰጥቶ መቀበልን መርህ መከተል ይኖርባቸዋል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ከተቃዋሚዎች ምን ይጠበቃል?
በመጀመሪያ ነገር ከኢህአዴግ ብዙ ነገር ይጠበቃል፡፡ ከተቃዋሚዎች ደግሞ ግማሽ መንገድ መምጣት ይጠበቃል፡፡ ህዝቡ በተቃዋሚዎች ላይም ጫና ማድረግ ያስፈልገዋል። አሁን የሚደረገው  ድርድር የፖለቲካ ነጥብ ማስመዝገቢያ ሳይሆን የሃገር መታደጊያ ነው መሆን ያለበት፡፡ ተቃዋሚዎች ድርድሩ እንዲሳካ በኢህአዴግ የቀረበውን ጥሪ በፀጋ መቀበል  አለባቸው፡፡ ይህን እንዲቀበሉ ከሞራል መሪዎችና ከህዝቡ ግፊት ሊደረግ ይገባል። ድርጅቶች ጥቅማቸው ሊነካ እንደሚችል ጭምር አምነው ነው ወደ ድርድሩ መግባት ያለባቸው፡፡
ዶ/ር አብይ በኢህአዴግ ላይ ለውጥ ያመጣሉ አያመጡም የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል።

ጠ/ሚኒስትሩ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ይችላሉ ብለህ ታምናለህ?
አዎ! ሶቪየት ህብረትን በኮሚኒስት ፓርቲው ውስጥ ሆኖ ወደ ለውጥ ያስገባው ሚኻኤል ጎርባቾቭ ነው፡፡ የአፓርታይድ ዋነኛ ባለቤት በነበረው የደቡብ አፍሪካው ናሽናል ፓርቲ ውስጥም ዴክለርክ ነው ለውጥ ያመጣው። የእነዚህን ሰዎች የመሪነት ክህሎት እስከ ዛሬ የምናደንቀው እኮ የድርጅታቸውን አስተሳሰብ ቀይረው ወደሚፈለገው ለውጥ ስለመሩት ነው፡፡
ዶ/ር አብይም በተመሳሳይ በፓርቲያቸው ውስጥ የሚገጥማቸውን ተቃውሞ አሸንፈው ዲሞክራሲን እውን በማድረግ ድርጅታቸውን ወደ ህዝቡ የለውጥ ፍላጎት እንዲያስገቡ ነው የምንጠብቀው። የአመራር ክህሎታቸው የሚፈተነው በዚህ ነው። ይሄን ማድረግ ካልቻሉ ታሪክ የጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት አልቻሉም ማለት ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ሰፊ ተቀባይነት ካስገኘላቸው ጉዳይ አንዱ ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀናቸው ነው።

ኢትዮጵያዊነትንና የብሔር ማንነትን ሚዛን አስጠብቆ ለመጓዝ አያስቸግራቸውም…?
ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦች እንዳሉ የምንክድበት ዘመን ላይ አይደለንም። እኚህ ሰው ኢትዮጵያዊነትን ሲያነሱ፣ ብሔር ብሔረሰቦችን ይክዳሉ ማለት አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ብሔር ብሔረሰቦችን ሲያነሱም፣ ኢትዮጵያዊነትን ይክዳሉ ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነትንም የብሔር ማንነትንም ሚዛናዊ አድርጎ የመሄድ ጉዳይ ነው። ሁለቱንም ይዞ መሄድ ችግር የለውም፡፡ ጎን ለጎን መሄድ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገር ያለ ነው፡፡ ህንድ ውስጥ ህንዳዊነት አለ፤ የአካባቢ ማንነቶች ደግሞ አሉ፡፡ ጎረቤት ኬንያም ተመሳሳይ ነው፡፡ በብሔረሰቦችና በኢትዮጵያዊነት መሃል ያለውን ቀመር አጣጥሞ የመሄዱ ጉዳይ ነው ዋናው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያደርጓቸው ንግግሮች ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ጠቀሜታ አላቸው ብለህ ታምናለህ?
ጠቀሜታ አላቸው፡፡ ነገር ግን በጥያቄና መልስ ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በወልቃይት ጥያቄ ላይ የሰጡት ምላሽ ጥሩ አልነበረም፡፡ የወልቃይት ጥያቄ የዲሞክራሲ ነው እንጂ የልማት ተብሎ ሊታለፍ የሚችል አይደለም። የአንድን ህዝብ ዲሞክራሲ የሚጋፋ ነገር እንዳይናገሩ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ንግግሮቻቸው ወደ ተግባር እስካልተለወጡ ድረስ ትርጉም አልባ ነው የሚሆኑት፡፡ በእርግጥ ሰውየው የለውጥ ፍላጎት እንዳላቸው የመጡበት መንገድም ያሳያል፡፡ በከፍተኛ ፍላጎት ወደ ስልጣን መምጣታቸው በራሱ የለውጥ ፍላጎት እንዳላቸው ያመላክታል፡፡ የኦህዴድን አቋም የኢህአዴግ ማድረግ ከቻሉ ደግሞ ለውጡ ሁሉን አቀፍ ሊሆን ይችላል፡፡
በተረፈ አሁን የጫጉላ ጊዜ ላይ ናቸው፡፡ ግን ይሄን የጫጉላ ጊዜ ተጠቅመው የሚፈለገውን ነገር ማምጣት ካልቻሉ ህዝብ በድጋሚ ወደ ጎዳና የማይወጣበት ምክንያት የለም፡፡ ይሄን ጉዳይ በቅጡ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ፤ “የኢትዮጵያ ጎርባቾቭ” ወይም “የኢትዮጵያ ዴክለርክ” እንዲሆኑ ነው የምንፈልገው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉን አቀፍ ድርድር የማይጠሩ ከሆነ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄው ወደ ጎዳና ሊወጣ ይችላል፡፡ ይሄ በሌሎች ሃገሮችም ያየነው ልምድ ነው፡፡ ህዝቡ በኢህአዴግ የስልጣን ሽግሽግ ረክቶ አይቀመጥም፡፡ ሥር ነቀል ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ይፈልጋል፣ ነፃነቱን መቀዳጀት ይሻል፡፡ ህዝቡ ወደ ጎዳና የወጣው ነፃነትን ፍለጋ እንጂ ኢህአዴግን ለማደስ አይደለም፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን የስልጣን ሽግሽግ በፀጋ የተቀበለው ነፃነት ለማምጣት መሸጋገሪያ ይሆናል በሚል ነው፡፡ የነፃነት አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች ወደ ስልጣን መጥተዋል ብሎ ነው የተቀበለው፡፡ ስለዚህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይጠይቃል፡፡
ለረዥም ጊዜ የውዝግብና የግጭት መነሻ ሆኖ የዘለቀው የወልቃይት ጉዳይ እንዴት መፈታት አለበት ትላለህ?
የወልቃይት ጥያቄ በመሰረታዊነት የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ ችግሩ ሊፈታ የሚችለው በአካባቢው ህዝብ ፈቃድ ብቻ ነው፡፡ ህዝብ ነው መወሰን ያለበት፡፡ በህዝበ ውሳኔ እልባት ማግኘት አለበት፡፡ በመሰረታዊነት የሃገሪቱ የዲሞክራሲ ጥያቄ ሲመለስ የአካባቢው ህዝብ ጥያቄም መልስ ያገኛል፡፡ ህዝቡ የወልቃይትን ጉዳይ “እኛ ሳንጠየቅ ሌሎች ናቸው በኛ ላይ የወሰኑት፣አሁን ራሳችን መወሰን አለብን” እያለ ነው፡፡ ይሄም ህገ መንግስቱ ያረጋገጠው መብታችን ነው ይላል፡፡ የህዝቡን ጥያቄ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገባ ሊያዳምጡ ይገባል። የወልቃይት ዲሞክራሲያዊ መብት ተነካ ማለት አጠቃላይ የሃገሪቱ ህዝብ መብት ተነካ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው አጠቃላይ ሃገራዊ የዲሞክራሲ ጥያቄ አካል ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ኮንግረስ ያጸደቀው HR 128፣ በኢትዮጵያ ላይ በተግባር የሚያሳድረው  ተፅዕኖ ምንድን ነው?
ወደ ደቡብ አፍሪካ ጉዳይ እንደገና ልመለስና ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ሲለቀቁ፣ ሽብርተኛ የተባለው ኤኤንሲ ፍረጃው ተነስቶለት ወደ ሃገር ውስጥ ገብቶ፣ ቢሮ ከፍቶ መንቀሳቀስ ጀመረ። ይሄኔ የምዕራቡ አለም ሰዎች፣ “በቃ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚፈለገው ለውጥ መጥቷል፤ ፖለቲከኞች ተፈተዋል፤ ኤንኤንሲም ሽብርተኛ የሚለው ፍረጃ ተነስቶለት ወደ ሃገር ውስጥ ገብቶ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ስለዚህ በደቡብ አፍሪካ ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ መነሳት አለበት” የሚል እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ በዚህ ሃሳብ ላይ ኤኤንሲ እና ኔልሰን ማንዴላ ተጠየቁ፡፡ ምላሻቸው ግን ፈፅሞ ማዕቀቡ መነሳት የለበትም የሚል ነበር፡፡ “ገና ጅማሮ ላይ ነው ያለነው፤ ይሄ ማዕቀብ ጅማሮ ላይ እያለን የሚነሳ ከሆነ ሊቀለበስ ይችላል፡፡ ወደ ለውጥ ሂደቱ ያስገባን ማዕቀቡ ነው፤ ነገሮች ገና ሳይበስሉ የሚነሳ ከሆነ ወደ ቀድሞ ሁኔታ የማንመለስበት አስተማማኝ ነገር የለም፡፡ ከተቀለበሰ በኋላ እንደገና ማዕቀብ ለመጣል ረዥም ጊዜ ይፈጃል። ስለዚህ ማዕቀቡ መነሳት የለበትም” ሲሉ ተከራክረው ነበር፡፡ ክርክራቸውም ተቀባይነት አግኝቶ ማዕቀቡ  ቆይቷል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታ ስንመጣ “ኢትዮጵያ ወደ ለውጥ እየገባች ነው፤ HR 128 ለማጽደቅ ጊዜው አይደለም” የሚል ክርክር ተነስቷል፡፡ ግን የለውጥ ጅማሮው ዳር መድረስ አለበት፡፡ ጅማሮው ዳር እንዲደርስ ደግሞ HR 128 ያስፈልጋል፡፡ የውሳኔ ሃሳቡ ጠቀሜታ ከዚህ አኳያ ነው፡፡
በመንግስት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥረው በምን መንገድ ነው?
በHR 128 ውስጥ አንድ አንቀፅ አለ፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ ባለስልጣናት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ማዕቀብ ይጥላል፡፡ አንዱ ጠቀሜታ ይሄ ነው፡፡ በመንግስት በኩል እውነተኛ ለውጥ ሳይሆን ጥገናዊ ለውጥ ብቻ የሚደረግ ከሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ መቀጠሉ አይቀርም። ከዚህ አንፃር HR 128 እውነተኛ ለውጥ እውን እስኪሆን ድረስ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህ የሚደረገው አሁን በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን ለውጥ በመቃወም አይደለም። እንደውም ለውጡ በቂ አይደለም፤ አጠናክሩ ለማለት ነው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ መለወጥ ይገባናል ለሚለው ድምፅም አጋዥ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ተጨባጭ ለውጥ ከሌለ ኢህአዴግ ከህዝብ ብቻ አይደለም የሚነጠለው። ከ27 ዓመት በኋላ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብም ይነጠላል ማለት ነው፡፡ ይህ የመነጠል አደጋ ከፊት ለፊቱ ተጋርጧል፡፡ በአንድ ወቅት የዚምባቡዌው ሙጋቤ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ እንደተነጠሉት ማለት ነው፡፡
የማዕከላዊ ምርመራ ቢሮ መዘጋት የሰብአዊ መብት ጥሰትን ለመከላከል ፋይዳ ይኖረዋል ብለህ ታምናለህ?
በነገራችን ላይ ማዕከላዊ ለኔ ሌላኛው ቤቴ ነው። ከጥፊ ጀምሮ ተገልብጦ እስከ መገረፍ የሚደርስ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞብኛል፡፡ ይህን የፈጸሙብኝ ፖሊሶቹ አይደሉም፤ ሥርአቱ ነው፡፡  የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚፈፅመው ስርአቱ እንጂ እንደኛ ሰው የሆኑት ፖሊሶች አይደሉም፡፡ ከዚህ አንፃር ማዕከላዊን በመዝጋት ብቻ የሰብአዊ መብት ጥሰትን ማስቆም አይቻልም፡፡ ከምንጩ ለማድረቅ ከተፈለገ ስርአቱን ነው መለወጥ ያለብን፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ከምንጫቸው የሚያደርቀው የዲሞክራሲያዊ ስርአት መመሥረት ብቻ ነው። ለፖሊሶች ስልጠና መስጠትና ማዕከላዊን መዝጋት ብቻውን መፍትሄ አይሆንም፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰት የአምባገነናዊ ስርአት ባህሪ ውጤት ነው፡፡ አምባገነናዊ ስርአት እስካለ ድረስ ግድያ፣ እስራት፣ የሃሰት ክስ አለ፡፡ ስለዚህ ከምንጩ ነው ማድረቅ ያለብን፡፡ ምናልባት የማዕከላዊ መዘጋት ኢህአዴግ ለውጥ እንደሚያመጣ   ምልክት ከሆነ እሰየው ነው።
ዛሬ ወደ ውጪ አገር ትበራለህ፡፡ እዚያው የመቅረት ሃሳብ አለህ ወይስ ትመለሳለህ?
እኔ ልቅር ብልም ባለቤቴ እዚያ አታስቀምጠኝም። ህዝብን ከድተህ እኔ ጋር አትቀመጥም ብላ ነው የምታባርረኝ፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እስክናገኝና ትግሉ ዳር እስኪደርስ ድረስ ውጭ ሃገር እኖራለሁ ብዬ አላስብም፡፡ የተነሳንበት፣ የታሰርንበት ዓላማ ከዳር መድረስ አለበት፡፡ የሚቻል ነው ብዬ ስለማምን እስከ መጨረሻው ድረስ እታገላለሁ፡፡ ይሄ ደግሞ የኔ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቤም አቋም ነው

Filed in: Amharic