>

ለጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ጊዜ መስጠትና እሳቸውን መተባበር ለምን??? (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

 ዐቢይ ሥልጣን ያዘ ከተባለ ማግስት ጀምሮ መሰንበቻውን ወያኔ ሕዝባዊ በመሰሉ ካድሬዎቹ (ወስዋሾቹ) በኩል “ጊዜ እንስጠው!” የምትባል ፈሊጥ ረጭቶ ሕዝብን ወስውሶ ማሳመን በመቻሉ ዐመፅ ተቃውሞው ጸጥ ረጭ ብሎለት ከገባበት አጣብቂኝ ውስጥ መውጣት ችሏል፡፡
አሁን ደግሞ ሕዝቡ ጊዜ ሰጥቶ የኋላ ኋላ የጠበቀው ለውጥ ሲቀርበት መጠየቁ እንደማይቀር ሲገባው በኋላ ላይ “ለውጡ መምጣት ያልቻለው ባለመተባበራቹህ ነው!” ለማለት እንዲመቸው በነዚሁ ሕዝባዊ በመሰሉ ካድሬዎቹ (ወስዋሾቹ) በኩል ምን የምትባል አዲስ ፈሊጥ አምጥቷል መሰላቹህ “ዐቢይ አንድ ሰው ነው አንድ ሰው ብቻውን ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ የምንፈልገው ለውጥ እንዲመጣ የምንፈልግ ከሆነ ሁላችንም ዐቢይን በማገዝ የለውጡ አካል መሆን መቻል አለብን!” የምትል ፈሊጥ አምጥቶ በመርጨት ላይ ይገኛል፡፡ የኛ የምንላቸው ሰዎችም እነኝህን የወያኔ ፈሊጦች ተጋርተው ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ወያኔም እነኝህ ፈሊጦቹ ያመጡለትን ውጤት ይዞ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በሚገባ እያወናበደበት ይገኛል፡፡ በዚህም እየተሳካለት ይመስላል፡፡
እጅግ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር የሚጨበጥ ነገርና ተስፋ የሚደረግበት አንድም ነገር ሳይኖር የኛ የምንላቸው ወገኖች እንዴት “ለዐቢይ ጊዜ እንስጠው!” የሚለውንና “እንተባበረው፣ እናግዘው፣ የለውጡ አካል እንሁን!” የሚለውን ለመቀበል እንደቻሉ ነው፡፡ እነኝህ ወገኖች ያለ አሳማኝ ምክንያት አብዝቶ ተስፈኛ እንደሆነው የሕዝባችን ክፍል ሁሉ እነሱም ከዚህ ተስፈኛው የሕዝባችን ክፍል እውነት ሆኖ በተግባር ሊያየውና ሊሰማው የሚፈልገውን ነገር ከሚያሳየው ቅዠት ከሆነ ሕልሙ ተቀስቅሶ ከመንቃትና ወደ ተጨባጩ እውነታ ከመመለስ ተመልሶም
ከአስከፊውና ተጨባጩ እውነታ ለመውጣት ማድረግ የሚጠበቅበትን ከማድረግ ይልቅ በጣፋጩ ቅዠት ተስበው እሱን እያለሙ ማጣጣሙን የመረጡ ይመስላሉ፡፡
“ለመሆኑ ለዐቢይ ወይም ዐቢይን እየተጠቀመ ላለው አገዛዝ ጊዜ ለመስጠትና ለመተባበር የሚገፋፋ፣ የሚስብ፣ የሞራል (የቅስም) ግዴታ የሚጭን ነገር አለ ወይ???” ተብሎ ቢጠየቅ “ከቁም ቅዠት በቀር ምንም ነገር የለም!” የሚለው ትክክለኛ መልስ መሆኑን አስተዋይና በቁም ቅዠት የማይነሆልል ልብ ያለው ሁሉ የሚረዳው እውነት ነው፡፡ ይሄንን እውነት ለመረዳት ብዙ ብስለትና ዕውቀት የማይጠይቅ ነገር ሆኖ እያለ መረዳት አለመቻሉ ነው አስቂኙ ነገር፡፡
ተጨባጩን እውነታ የሚያሳዩ ሁለት ነገሮችን ብቻ ልጥቀስ፦
1ኛ. አዲስ የተባለውን የዐቢይን ካቢኔ (ሸንጎ) ያየን እንደሆነ ተሿሚዎቹ በሙሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለደረሰው ሰቆቃ፣ ግፍ፣ በደል፣ ክህደት ወዘተረፈ በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ወያኔ እነኝህን ሕዝብ ተጠያቂ የሚያደርጋቸውን ሹማምንቶቹን ትቶ ሕዝብ በግልጽ የማያውቃቸውን የራሱን ሰዎች ሾሞ ቢሆን ምንም እንኳ ሰዎቹ የወያኔ/ኢሕአዴግ አባል በመሆናቸው የወል ተጠያቂነት ቢኖርባቸውም እነኝህ አዲሶቹ እንደ በፊቶቹ ሕዝብ በግልጽ የሚያውቅባቸው ወንጀል ስለማይኖር ሕዝቡ አዲስ ፊት በማየቱና ወንጀለኞቹ በመወገዳቸው ተስፋ እንዲጥል ሊገደድ ይችል ነበረ፡፡ ይሄ ግን አልሆነም፡፡ የተሾሙት በሙሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያሰቃዩ፣ ሲፈጁና ሲያስፈጁ፣ ሲዘርፉና ሲያዘርፉ የነበሩና ለዚህ ወንጀላቸው፣ ግፋቸው፣ ክህደታቸው ለፍርድ መቅረብ የነበረባቸው ወንጀለኞች ናቸው በዐቢይ ካቢኔ የተሾሙት ወይም ሥልጣን የተሰጣቸው፡፡ ይሄ ነው ወይ ተስፋ የሚሰጠውና ለእነ ዐቢይ ጊዜ እንስጣቸው እንተባበራቸው የሚያሰኘው??? በእነኝህ ወንጀለኞች ነው ወይ የሚጠበቀውና የሚፈለገው ለውጥ የሚመጣው???
በነገራችን ላይ ስለዚህ ስለዐቢይ ካቢኔ (ሸንጎ) ሹመት ስናወራ አንድ ሳልነግራቹህ የማላልፈው ጉዳይ፦ 
ይገርማቹሀል! ወያኔ ዐቢይን በሾመ ማግሥት ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘትና “ለውጥ እያደረኩ ነኝ!” የሚለውን ባዶ ጩኸቱን የሚቃረን ነገር እየተናገሩ ነገር እንዳያበላሹበት አፋቸውን ለመዝጋት ምን አደረገ መሰላቹህ በአዲሱ የዐባይ ካቢኔ ውስጥ ቢያንስ አምስት የሚሆኑትን ከተቃዋሚ መሪዎች እንደሚሾም በምሥጢር አስወራ፡፡ ወያኔ እንዳሰበውም ተቃዋሚዎቹ ከአምስቱ አንዱ ሆነው ለመመረጥ በማሰብ አፋቸውን ይዘው ጭጭ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ለውጥ እንዳለ አፋቸውን ሞልተው መናገር ጀመሩ፡፡ ወያኔ ይሄንን በምሥጢር ያስወራውን ወሬ እውነት ለማስመሰልም ለአቶ ልደቱ የገጽታ እድሳት ዘመቻ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ እንዲጧጧፍ አደረገ፡፡ በዚህም ተቃዋሚዎቹ ከሚሾሙት ውስጥ አንዱ ልደቱ እንደሆነ “አሃ እሱንማ በቀር እንዴት ሊተውት ይችላሉ?” እያሉ ሲያሽሟጥጡ ሰነበቱ፡፡ መጨረሻ ላይ ግን እንዳያቹህት ወያኔ ተቃዋሚዎችን ጦጣ አድርጎ አጃጅሎ እንኳን ከተቃዋሚዎች ከገልተኛ ምሁራን እንኳ አንድ ሰው ሳያካትት እነዚያኑን ወንጀለኛ ባለስልጣናቱን ቦታ አቀያይሮ ሾመና ምድረ ቃዣታምና የሥልጣን ጥመኛ ተቃዋሚዎችን ኩም አደረጋቸው፡፡ ተቃዋሚ ተብየዎቹ የሆነውን ለማመን በእጅጉ ተቸግረው ነበረ፡፡ ንዴታቸውን መቋቋም ተስኗቸው ነበረ፡፡
2ኛ. ዛሬም እንደትናንቱ ወያኔ እያሰረ፣ እየገደለ፣ እየዘረፈ….. መሆኑ ነው፡፡ ወያኔ ጎንደርና ጎጃም እንደአዲስ እስር እያኪያሔደ ነው፡፡ ዛሬም እንደትናንቱ ወያኔ የራሱ ሕግ ሕገወጥ መሆናቸውን ባረጋገጠባቸው የንግድ ድርጅቶቹ ሀገሪቱንና ሕዝቧን እየዘረፈ ነው፣ እንደ ፋና ባሉ በብዙኃን መገናኛዎቹ የፓርቲውን (የቡድኑን) ሕገወጥ ጥቅም እያስጠበቀ ይገኛል፡፡
ባለፈው ጊዜም እንዳልኩት ስለእነኝህ ሕገወጥ የወያኔ የንግድ ድርጅቶቹና የብዙኃን መገናኛዎቹ ዐቢይ ምንም ያለው ነገር የለም፡፡ እስከአሁን ባለው ጊዜ “እነኝህ ሕገወጥ ድርጅቶች ተዘግተው ንብረታቸው ውርስ ለመንግሥት ይደረጋል!” ተብሎ ሕጋዊውና ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድ አልተነገረም፡፡ ጨርሶ ምንም ዓይነት ሹክሹክታ እንኳ የለም፡፡ እነኝህን ድርጅቶች የመዝጋቱና ንብረታቸውንም ለመንግሥት ገቢ የማድረጉ ነገር ወያኔ እስካለ ጊዜ ድረስ ሊታሰብ የሚችል ነገርም አይመስልም፡፡ እውነታው ይሄ በሆነበት ሁኔታ ምን ተስፋ ታይቶ ወይም ተይዞ ነው ታዲያ ጊዜ የሚሰጠውና ጭራሽም መቃወማችንን እርግፍ አድርገን ትተን ዐቢይን በማገዝ በመተባበር ሽፋን ወያኔ/ኢሕአዴግን ማገዝ መተባበር፣ ለወያኔ/ኢሕአዴግ መሥራት የሚኖርብን?????…. ሰው እንዴት በተለይ ደግሞ ሕዝብን እንመራለን የሚሉ ሰዎች እንዴት የዚህን ያህል ቂልና ተላላ ይሆናሉ???
እዚህ ላይ ነባሮቹ ተመልሰው በዐቢይ ካቢኔ ስለመሾማቸው ተቃውሞ ሲቀርብ ወያኔ ምናልባት “ይቅርታ ጠይቀናልና ወደኋላ አትመለሱ፣ በአዲስ መንፈስ ወደፊት እንቀጥል!” በማለት ለመከላከል ይሞክር ይሆናል ብሏልም፡፡ ዐቢይም “ይቅርታ የተጠየቀበት ጉዳይ ነውና እንዲህ ዓይነት ነገር አታንሡ!” ብሏል፡፡
ነገር ግን ወያኔ ለ27 ዓመታት ሙሉ በዚህች ሀገርና በሕዝቧ ላይ የፈጸመው ከባባድ ክህደቶች፣ በርካታ አረመኔያዊ ግፎች፣ ካዝና ያራቆተ ዝርፊያ ወዘተረፈ. ለይስሙላ በተነገረ ይቅርታ ሊታለፍ የሚችል ነው ወይ??? ያውስ ቢሆን ይቅርታውን ማግኘታቸው በሕዝቡ ፈቃድና ይሁንታ የሚወሰን ነው እንጅ ሕዝቡ “እሽ አሳምናችሁኛል ይቅርታ አድርጌላቹሀለሁ!” ሳይል ወያኔ “ይቅርታ!” ስላለ ብቻ የዚያ ሁሉ ግፍ፣ የዚያ ሁሉ ክህደት፣ የዚያ ሁሉ ዝርፊያ…. ነገር በቃ አለቀለት ማለት ነው ወይ??? የሕግ የበላይነቱስ ጉዳይ??? የሕግ የበላይነት ካልተረጋገጠ ምን መተማመኛ አለ??? በተለይ በተለይ ደግሞ እነዚህ ሰዎች “ይቅርታ ጠይቀንበታል!” ያሉትን ያንኑ ስሕተትና ወንጀል አሁንም ቀጥለውበት ባለበት ሁኔታ የይቅርታ ትርጉሙ፣ እርባናውና ዋጋውስ ምንድን ነው??? መታረም መስተካከል በሌለበት ሁኔታ ይቅርታ ትርጉምና ዋጋ ሊኖረው ይችላል ወይ??? ባጠቃላይ ወያኔ በዚህ ሕዝብ ላይ  ጢባጢቦ ነው እየተጫወተ ያለው፡፡
ወያኔ “በተጨባጭ እለወጣለሁ!” ካለ በኋላ እንደ አዲስ የተያያዘው እስር ግድያና የሕገወጥ የንግድ ድርጅቶቹ በሥራ ወይም በዝርፊያ ላይ መሆን ሌላም ሌላም ነገሮች እንደነበሩ መቀጠላቸው የዐቢይን አሥተዳደር ስም ሊሠብርና ተቀባይነት አሳጥቶ ሕዝቡን ተስፋ አስቆርጦ ዐመፅና ተቃውሞ እንደገና መቀስቀሱ አይቀሬ መሆኑ የገባው ወያኔ ይሄ ችግር እንዳይከሰት ወይም የወያኔ ሠራዊት በሚያደርሰው ጥቃት የወያኔ ሁነኛ ጭምብል የሆነው ዐቢይና አስተዳደሩ እንዳይወነጀልና ተስፋ እንዳይቆረጥበት ከወዲሁ ለመከላከል እንዲሁም የወያኔ ሠራዊትም የፈለገውን እያሰረና እየደገለ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ብሎ ወያኔ አሁን ደግሞ ምን ፈሊጥ አምጥቶ እያስወራ ነው መሰላቹህ “ኮማንድ ፖስቱ (የዕዝ ሹሙ) ለዐቢይ አልታዘዝም ብሏል!” ወዘተ ወዘተ ብሎ እያስወራ ይገኛል፡፡
የሚገርሙኝ የኢሳት ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሌሎችም የነጻው የብዙኃን መገናኛ ተንታኞች ወያኔ ሾልኮ የወጣ መረጃ እያስመሰለ የሚያቀብላቸውን የፈጠራ ወሬ እንደወረደ እያቀረቡ ዕድሜ ዘመናቸውን መጠቀሚያው ሆነው መቀጠላቸው፣ ትናንት “አፈትልኮ የወጣ መረጃ!” እያሉ ባስተላለፉት የወያኔ የፈጠራ ወሬ ወያኔ ምን ያህል እንደተጠቀመ ዕያዩ፣ ስንት የሚያነቃ ነገር እያለ አንድ ቀን እንኳ አለመንቃታቸውና መቀጠላቸው ነው፡፡ እነዚህ እነዚህ ናቸው እንግዲህ ሕዝባዊ ዐመፁን ያመከኑት፡፡ የመከነ ቢመስልም ግን ለጊዜው ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ቆይ እነዚህ ወያኔ የሚያቀብላቸውን የፈጠራ ወሬ እያራገቡ ሳያውቁት ወያኔን እያገለገሉ እያገዙ ያሉ ነፈዞች ዐቢይ ወያኔን ለማትረፍ ይሄንን ያህል እየጣረ እየጋረ ባለበትና ውጤት እያመጣላቸውም ባለበት ሁኔታ ኮማንድ ፖስቱም ሆነ ሠራዊቱ ምን ከፋኝ ብሎ ነው ለዐቢይ አልታዘዝም የሚለው??? ሲጀመር ዐቢይ ለእነሱ ታዛዥ ነው እንጅ እነሱ ናቸው ወይ ለዐቢይ ታዛዦቹ??? ከላይ የጠቀስኩላቹህ ሁለት ማሳያዎች በግልጽ የሚያሳዩት እውነት የዐቢይን ታዛዥነት ነው እንጅ አዛዥነቱን ነው ወይ??? በሕገመንግሥታቸው መሠረት ዐቢይ የተሟላ የጠ/ሚ ሥልጣን ቢኖረውማ እነሱም አላበዱም “አንታዘዝም!” አይሉም እሱም ይሄንን ተግዳሮት ለደቂቃ እንኳ የሚታገሰው አይሆንም፡፡ ምንም ማድረግ ባይችል እንኳ ወዲያውኑ ነው የይስሙላ ሥልጣኑን በፈቃዱ የሚለቅ የነበረው፡፡ ዐቢይ ይሄንን እርምጃ የማይወስድበት ምክንያት ታዛዥነቱን ተቀብሎ አምኖ ስለገባ ነው፡፡
ዐቢይን ለምን እንደምጠላው ታውቃላቹህ? በምንም ተአምር ቢሆን ወያኔ እንዲጠየቅ፣ ጥቅሙም እንዲነካ ባልፈለገበት ሁኔታ እያወራው ያለውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ተግባራዊ ሊያደርገው እንደማይችል እያወቀ በከፍተኛ የአስመሳይነት ብቃት ድካምና ጥረት በጥፋት ስብከታቸው ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱበትን ኢትዮጵያዊነትን በሽፋንነት በመጠቀም ሕዝብን እየደለለ ወያኔን ከጉድ ለማውጣት የሚባትል የሚጥር የሚግር የወያኔ ሙሴ ወይም ቅጥረኛ በመሆኑ ነው፡፡
ዐቢይ ለሕዝብ ከፍተኛ ንቀት ስላለው ካልሆነ በስተቀር ይሄንን ነገ የሚያፍርበትን ነውረኛ ትወና ሊተውን አይችልም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ዐቢይ ከሌላ ዓለም የመጣ ሰው አይደለም፡፡ ምን ሲሠራ የነበረ ሰው እንደሆነና ማን እንደሆነ በሚገባ እየታወቀ ዐይኑን በጨው አጥቦ ሀገርና ሕዝብ አፍቃሪ መስሎ ለመታየት የሚያደርገው ጥረት እጅግ እንድታዘበው አድርጎኛል፡፡
እናም ወያኔ ሆይ! ባጃጃልሻቸው ምድረ ነፈዝና ዘገምተኛ አክቲቪስት (ስሉጥ) ነኝ፣ ፖለቲከኛ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ነኝ፣ ምንትስ ነኝ ባይ ተደግፈሽ አሁን ላለሽበት እፎይታ ብትበቂም ይሄ ድልሽ ጊዜያዊ እንጅ ዘላቂ አይደለምና ደስ አይበልሽ!!! ነገ ይሄንን ሁሉ ቅጥፈትሽን ማታለልሽን ሕዝብ ሲደርስበት በምንም ተአምር ቢሆን ልትቀለብሽው በማትችይው የሕዝባዊ ዐመፅ ማዕበል ተጠራርገሽ መወገድሽ አይቀሬ መሆኑን ዕወቂ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
Filed in: Amharic