>

የሁለት ፕሮፌሰሮች ወግ (ዮና ቢር)

ባለፉት ሃምሳ አመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚወክሉ ሁለት ሰዎች ይጠሩ ቢባል የሚመጡት
– ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም   እና  –  ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ይሆናሉ።
ኢትዮጵያዊነት (አሃዳዊነት) እና የብሔር ፖለቲካ በሁለቱ ፕሮፌሰሮች ሊቋጭ ይችላል።
ፕሮፌሰር አንድሪያስ የብሔር ፖለቲካን ያቀናጁ፤ ዋለልኝን ያሰለጠኑ፤ መለስን ያማከሩ ናቸው።
ፕሮፌሰር መስፍን የብሔር ፖለቲካን የሚቃወሙ፤ አገራዊ ፓርቲን ያቋቋሙ፤ ዶክተር ብርሃኑን ያሰለጠኑ ናቸው።
ከሃምሳ አመት በኋላ እነሆ አገሪቷ በብሔር ፖለቲካ ተዋቅራለች። 
ታዲያ ዛሬም ….
– ገሚሱ ሕዝብ (በተለይ ከተሜውና ሰሜኑ) የብሔር ፖለቲካን አልተቀበለም። ምክንያቱም የብሔር ፌዴራሊዝም አገራዊ አንድነትን ይንዳል፤ የዜጎችን የመዘዋወርና የመኖር መብት ይገድባል፤ እንደ ሃገር እንዳንቀጥል ይሸረሽረናል ሲሉ ….
– ገሚሱ ሕዝብ ደግሞ (አብዛኛው ደቡብና ትግራይ) ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ሌላ ሳይሆን አማራዊነት ነው። ይህ ማንነት በግድ ተጭኖብን ማንነታችንን ሊያጠፋና ሃብታችንን ሊቀማን  ስለሚችል ድጋሚ ወደዚያ ከምንመለስ ብትንትናችን ይውጣ ይላሉ።
ይህ አመለካከት በሁለቱ ፕሮፌሰሮች ብቻ ሳይወሰን ዛሬ ድረስ አጨቃጫቂ ሆኖ  ቀጥሏል። ዛሬም በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምሁሮች በነዚህ ጥጎች መሸገው ይለጣለጣሉ።
ሁለቱ ፕሮፌሰሮች እድሜያቸው ገፍቶ እየደከሙ ነው። ሆኖም ግን ብዙ ወጣቶች ተክተዋል። ዛሬ እነዚህ ሃሳቦች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ልብ ውስጥ ሰርጸዋል።
– ድምጻዊ ቴውድሮስ ካሳሁን እና ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ
– የፖለቲካ ተንታኙ ጃዋር እና ገጣሚና ደራሲ በእውቀቱ
የዘመኑ ፕሮፌሰር መስፍን እና ፕሮፌሰር አንድሪያስ ሆነዋል።
ሁለቱም በቂ መከራከሪያ አላቸው።
ሁለቱም ሲናገሩ የሚያንዘረዝራቸው ወጣት ተከታይ አላቸው።
ሁለቱም ልዩነቱ የሚታረቅ አይመስላቸውም።
መንግስት ደግሞ ሚዛኑ ወደ አንደኛው ሲያጋድል ወደ ሌላኛው እየተጠጋ የራሱን እድሜ ያራዝማል።
መለስ ዜናዊ የብሔር ፖለቲካን ሲቀርጽ አንድ የሳተው ጉዳይ ነበር።
ይሄውም የኢትዮጵያን ውስብስ ችግር (አገር የመገንባት ሂደት) በአንድ ጥይት (One Silver Bullet) ሊገላግለው ማሰቡ ነበር።
መለስ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ በብሔር ሳጥን ውስጥ ከቶ አገሪቷን በብሔር ፖለቲካ ሲያዋቅራት ግምሹን ሕዝብ ከግምት አላስገባም ነበር።
ይሄ በሃገራችን ፖለቲካ የተለመደ ችግር ነው። ውስብስ ለሆኑ ችግሮቻችን አንዲት መፍትሄ አበጅቶ የማለፍ በሽታ። የፖለቲካ ጥያቄ በማመቻመች፤ ሰጥቶ በመቀበል፤ በመደራደር እንጂ በአንድ መፍትሄ ሊፈታ አይችልም።
የብሔር ፌዴራልዝም ግማሹን ሕዝብ በማግለሉ እስከዛሬ ድረስ ቅቡልነት (legitimacy) ሊያገኝ አልቻለም። ከብሔራቸው እርቀው የሄዱ ከተሜዎችና ሰሜነኞችን አንድ ላይ ብሔር ሳጥን ውስጥ ለመክተት መሞከር ከባድ ስህተት ነበር።
መለስና ጓዶቹ የሰሩት ስህተት የተገለጸላቸው አስር አመት ሳይሞላ ነበር።  ወቅቱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አገር ለመቀጠል ኢትዮጵያዊነት የሚለው ስሜት አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘቡ።
– የዛን ጊዜ ባንዲራችን ከክልሎቹ ባንዲራ ተለይቶ ከፍ ተደረገ።
– የዛን ጊዜ የጥላሁን ገሰሰ <ኢትዮጵያ የእኛ መመኪያ> የሚለው ዘፈን ብሔራዊ መዝሙራችን መሰለ።
– የዛን ጊዜ የወላይታ ወጣት ክልሌ ስላልሆነ ባድመ አልሄድም ብሎ እንዳይቀር አገርህ ትፈልግሃልችና ድረስ ተባለ።
ቀጥሎ ደግሞ መለስ የባነነው ምርጫ 97 ላይ ነበር። ምርጫ 97 መለስ በርግጎ እንዲነቃ (Rude Awakening) አስገደደው።
ፕሮፌሰር መስፍን የጠነሰሱት የኢትዮጵያዊነት ፓርቲ አገር ምድሩን ገለባበጠው። ተቀብሯል የተባለው አሃዳዊነት እንዳልሞተ ተረጋገጠ።
በዚህ ጊዜ መለስ ማርሹን ለውጦ ልማቱ ከከተማ እንዲጀመር አደረገ። አዲስ አበባ መስፋፋት ጀመረች። ገጠሩን ማእከል ያደረገው ልማት ተሻረ። የብሄር ፖለቲካ ቀስ በቀስ መቀነስ ጀመረ።
ሰሞኑን ደግሞ አስገራሚ ድርጊት ተከናወነ፤ 
የኦሮሞ ወጣቶችና ገበሬዎች የኢትዮጵያ መንግስትን አንቀጥቅጠው የጀመረውን የከተማ መስፋፋት እንዲያቆም አሰገደዱት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ መንግስት በይፋ ይቅርታ ጠየቀ።
በዚህም የብሄር ፖለቲካ በቂ ድጋፍ ያለውና ሊጨፈለቅ የማይችል እንደሆነ አስመሰከረ።
ሲጠቃለል
የኢትዮጵያ ምሁራን ላለፉት ሃምሳ አመታት የሰሩትን ስህተት ዛሬም  እየደገሙት ነው። እኔ ካልኩት ውጪ በመቃብሬ ላይ (My way or the highway) የሚባለው አካሄድ በፖለቲካ ውስጥ ቦታ የለውም።
የብሄር ፖለቲካ ሊቀር አይችልም!!!
ኢትዮጵያዊነት ሊቀበር አይችልም!!!
እነዚህ ሁለት አመለካከቶች እኩል ድጋፍ አላቸው።
ስለዚህ ሁለቱን አንድ ላይ አጣጥመንና አሳምምተን ለመሄድ በጠረጴዛ ዙሪያ ቀጭ ብለን መምከር አለብን። አንዱ አንዱን ሊያጠፋ መሞከሩ አገሪቷን ያጠፋታል። ጊዜው ከረፈደ ሱማሊያ፤ ሶሪያ፤ የመንና ሊቢያ ላለመሆናችን መተማመኛ የለም።
ሁለቱ ፕሮፌሰሮች እየደከሙ ነው፤ ሁለቱ ድምጻውያን ግን ብዙ መንገድ ይቀራቸዋል።
መፍትሄው ሰጥቶ መቀበል ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ሁሉንም አስደስታ ለዘላለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic