>

ነፃነትን የሚያውቅ ነፃ አውጪ! (ዳንኤል ሺበሺ)

  እኔ የእነ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፓርቲ አባል አይደለሁም፡፡ ግን የሰብዓዊነት ጉዳይ ሁሌም እንቅልፍ ይነሳኛል፡፡ የትግል ስልቱን ባልደግፍም በዓላማው/በግቡ ብዙም የምንራራቅ አይመስለኝም፡፡ ግባችን ፍትህ ማስፈን፣ ዴሞክራሲና ነፃነትን ማረጋገጥ እስከሆነ ድረስ፡፡
ወንድሜ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲሸፍት የአገዛዙ ሚና የአንበሳ ድርሻ መሆኑን የአገዛዙ ሊህቃን በአንደበታቸው ከጠየቁት ይቅርታ ማረጋገጥ ይቻላል፤ አገዛዙ እሱን በማሰሩ ምክንያት ያተረፈው ትርፍ የለም፡፡ ካሌም ጠላፊዎቹ ራሳቸው ብቻ ያውቁታል፡፡ ለእኛ እንደገባን  ከሆነ  ከዓለሙ አቀፍ ማኀ/ብ ውግዘትን፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቅራኔን፤ ሀገራችን በዶላር ድርቅ እንዲትመታ በማደረግ ለፖለቲ ካውና ለኢኮኖሚ ቀውስ አንዱ መንሥዔ ከመሆኑ ውጪ የተተረፈረፈና ለሀገር የሚፈይድ ነገር ያፈሱት አይመሰለኝም፤ በእርሳቸው መጠለፍ ምክንያት የለዘበ ጥያቄም ሆነ ትግል የለም፡፡ እርሳቸውንም ማስረሳት/መርሳት አልተቻለም፡፡በታሪካችን ታይተው ወደማይታወቅ አዘቅት ውስጥ ከተውናል፡፡ ከፈተናዎቹ ሲንዝር እንኳ ፈቅ ማለት ተስኗቸው በችግሩ ግዝፈትና ግፍት መሪያቸውን እስከመቀየር አድርሷል፡፡ ይህ ማለት እርሳቸው ይዘውት የተነሱት ዓላማ ትክክል መሆኑን ያሳብቃል ማለት ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአንዳርጋቸውና በአርበኞች-ግ7 ስም የተከሰሱት በሙሉ እንዲለቀቁ 4ቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ሊቃነመነበራት ማዘዛቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ እየተፈቱ መሆኑን እያየን ነው፡፡ ይህንን በንጽጽር ስናይ፦ ቄሮን እያመሰገኑ በቄሮ ስም የታሰሩትን እንደመራገም ነውና፡፡ ሌሎች ተከሳሾችንና ፍርደኞችን የአርበ-ግ7 አባል ቢሆኑም ይፈቱ ብሎ የፈታው አካል ክቡር አቶ አንዳርጋቸውንም በተመሳሳይ ምክንያት መፍታት ይገባል፡፡
ለብዙዎቻችን የቀለም፣ የዕውቄትና የጽናት ተምሳሌትና አባት የሆነው ወገናችን በዚህ በአንድና በሁለት ቀናት ውስጥ፤ ቢዘግይ እንኳ በአንድና በሁለት ሣምንታት ውስጥ ተፈትቶ ማዬት እንሻለን፡፡ ካልሆነ ግን የዘገየ ፍትህ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የዘገየ ፍትህ፤ እንደመንፈግ ይቆጠራል፡፡
እኛም ከህዝባችን ጋር ሆነን በተቻለ አቅም፤ ሁሉም የተቀሩ እስረኞች እንዲፈቱ፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ … እስኪረጋገጥ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥልበታለን፡፡ ሰላም ፣ ፍትህና ነፃነት ለአንዳርጋቸው ጽጌ! ሰላም ፍትህ … ለአንዳርጋቸው ቤተሰቦች፣ ለባለቤቱ፣ ለልጆቹ እና ለወላጆቹ!!!  ሰላም!!
Filed in: Amharic