1. አንዳርጋቸው በልጅነትና በጨዋታ እድሜያቸው የሀገራቸውን ፖለቲካ ለማዘመን ሲሉ የተሰዉ ለጋ ወጣት ጉዋደኞቹ ቃል ኪዳን በልቡ እንደታተመ ጨለማ ቤት እስከሚዘጋበት ድረስ ከፃፋቸውና ከተናገራቸው መገንዘብ ይቻላል።
2.አንዳርጋቸው መልካሙን በመመኘት ብቻ ለሀገራቸው ነፃነት ሲሉ በእሱ ትውልድ የነበሩ ወጣቶች የከፈሉት መስዋዕትነት ቢያስደንቀውም የሀገራቸውን ማህበራዊ ስነ ልቦናና የህብረተሰብ አደረጃጀት በውል ያልተገነዘበ መሆኑን አምኖ ባልተለመደ ሁኔታ በነፃነት ተችተዋል።
3. አንዳርጋቸው በመጀመሪያዎቹ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣባቸው ሁለት ዓመታት የሀገሩን ህዝብ የዴሞክራሲ ጥያቄ መልስ ለመስጠት በማሰብ ከኢህአዴግ ጋር አብሮ በሰራባቸው ጊዚያት ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች መንገዳቸው ሁሉ ከህዝብ ጥያቄ በእጅጉ የራቀ መሆኑን ስለተገነዘበ በራሱ ፈቃድ ድርጅቱንና ስራውን ለቁዋል። አብሮ በነበረባቸው ጊዚያት ለተሰሩ ጥፋቶች መፅሀፍ ፅፎ ህዝቡንና ሀገሩን በአደባባይ በይፋ ይቅርታ ጠይቁዋል።
4. አንዳርጋቸው የእውቀትን መሰረታዊ መርሆና ለሰው ልጅ መለወጥ አስፈላጊነትን በአፅንዖት የተረዳ ብሩህ አዕምሮ ያለው ሰው ቢሆንም ትምህርትን ለችግር መፍቻና ለማህበረሰብ አገልግሎት ለመጠቀም ብቻ ያዋለ ሲሆን ለራሱ ማህበራዊ ሽግሽግና ለግል ኑሮ ማደላደያነት የተጠቀመ ሰው አይደለም።
5. አንዳርጋቸው ሀገራችንን የወረረውን አደግዳጊነትን፣አድርባይነትን፣ አሙዋሙዋቂነትን ፣ጥራዝ ነጠቅነትን ለሀገራችን ጠንቅ መሆናቸውን ተገንዝቦ በፃፈው መፅሀፉ ውስጥ በሰፊው ያስተማረ ከመሆኑም በላይ እነዚህን ባህሪያት በመፀየፍ በተግባር አስተምሩዋል።
6.ስለ አንዳርጋቸው የግል ህይወት በቂ መረጃ ባይኖረኝም በማህበራዊ ሚዲያ ከማየው የልጆቹ የእድሜ ለጋነት የተረዳሁት አንዳርጋቸው ለግል ህይወቱ ብዙም ትኩረት ያልሰጠና ብዙውን ጊዜውን በሀገሩ ጉዳይ በማጥፋቱ ህይወቱ ብዙም የተደላደለ አይመስልም።
7.አንዳርጋቸው ለአመኑበት ነገር ዋጋ እንደሚያስከፍል እያወቁ ብዙ ርቀት መሄድና በአላማ መኖር ምን እንደሆነ በተግባር ያስተማረ ሰው ነው።
በአጠቃላይ አንዳርጋቸው በስብዕና ጉድፍ ፣ በዝርክርክነትና አባካኝነት ለሚዋዥቀው ለእኔ ትውልድ አስተማሪነቱና ዓርዓያነቱ በጣም ከፍተኛ ነው። እንደ አንዳርጋቸው አይነት በብዙ መልኩ የጠራ ስብዕና ያለውና ለትውልድ ምሳሌ የሆነ ሰው በመከራ ቤት ሆኖ ተገቢውን ትኩረት አለማግኘቱ የምንገኝበትን የሞራል ዝቅጠት የሚያሳይብን የተግባር ምሳሌ ነው። ገዥዎቻችንም ለአንዳርጋቸው አይነት ሰዎች እሾህ የሆነ አገዛዝ መስርተው ትውልድንና ሀገርን ስለመቀየር የሚያወሩት ሁሉ ከኢትዮጵያ እውነታ ጋር የራቀ መሆኑን በግልፅ ያሳያል። የአንዳርጋቸውን ዓርዓያነት ወደ ልባችን አስገብተን በቁም ነገር እንድንይዘው ለእኛ ለነፃነት እንታገላለን ለምንልና ስልጣን ላይ ላሉ ገዥዎች አምላክ ልቦና ይስጠን።