>

እስክንድር ነጋ አውሮፕላን ውስጥ የገጠመው አስገራሚ ክስተት (ክንፉ አሰፋ)

እስክንድርን የያዘው አውሮፕላን ከፍራንክፈርት ተነስቶ፣ ልክ በ7.15 ዲሲ፤ ዳላስ አውሮፕላን ማረፍያ ላይ ሲያርፍ አዲስ ክስተት ተፈጥሮ ነበር። ተሳፋሪዎችን የስደነገጠ ክስተት።

እንዲህ ነው የሆነው። አውሮፕላኑ እንዳረፈ ፖሊሶች ወደ ውስጥ ይገቡና እስክንድር ነጋ ብለው ይጣራሉ። እስክንድር ከተቀመጠበት ተነስቶ እኔ ነኝ ይላቸዋል።

ወደ ፊት ብቅ እንዲል ይጠይቁትና ሲወጣ አጅበው ይወስዱታል። ግን ይህ ለምን ሆነ? ነገሩ ለእስክንድርም ሆነ ለተሳፋሪዎች እንግዳ ነበር። ሁሉም ግራ ተጋባ!

በዚያች ቅጽበት በእስክንድር እምሮ ውስጥ የሚመላለስ ነገር እንደሚኖር ለመገመት አያስቸግርም። በፈጠራ የሽብርተኝነት ወንጀል ተከስሶ፣ በሃሰት ተፈርዶበት የነበረ ጋዜጠኛ ነው። የፈጠራው ፋይል ግን አሜሪካ ግዛት ድረስ ተጉዞ ይደርሳል ብሎ ለመገመት ይከብደዋል ።

ሌላ ነገር በአእምሮው መጣ። አውሮፕላን ውስጥ እያለ በጉዞ ላይ የተፈጠረው ነገር ታወሰው። እስክንድር አውሮፕላን ውስጥ አንዲት ሙስሊም ሴትዮን በትርጉም እና በሃሳብ እየረዳት ነበር። ይህች ሴት በአሸባሪነት ትጠረጠር ይሆን? የሚል ነገር ቢመጣበት አያስደንቅም።

በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ፈረንጆችም የገመቱት ይህንኑ ሳይሆን አይቀርም።

እስክንድር ነጋ በፖሊሶቹ ታጅቦ እየሄደ ነው። እየተጓዘ ያለው በመደበናው መሄጃ መንገድ ሳይሆን፣ በልዩ የቪ.አይ.ፒ. መውጫ በኩል ነው። እምደማንኛውም መንገደኛ ፓስፖርቱን ለማስፈተሽ አልተሰለፈም። በጉምሩክ በኩልም አላለፈም። ፖሊሶቹ ሁሉን ነገር እያሳለፉ ይዘውት በፍጥነት ይጓዛሉ።

ውጭ ስላለው ነገር እስክንድር የሚያውቀው ነገር የለም። ፖሊሶቹ ግን አንድ ነገር አይተዋል። ስለዚህም ነገሩን ማጣደፍ ግድ ይላል።

አንድ ክፍል ውስጥ አስገብተው ፓስፖርቱ ላይ ማህተም አሳረፉ። በተለምዶ የሚመታው የይለፍ ማህተም የሶስት ወር ብቻ ነው። የእስክንድር ፓስፖርት ላይ ግን የ8 ወር ነው የተመታው።

ለእስክንድር ነጋ ዋሽንግተን ዳላስ ኤርፖርት ላይ አቀባበል እንደሚደረግ አስቀድሞ ለፖሊስ ተነግሯል። በስፍራው ተመድቦ የነበረው የፖሊስ ሃይል የገጠመው ነገር ከተጠበቀው በላይ መሆኑ በእጅጉ አስጨንቋቸዋል። ግልብጥ ብሎ የወጣው የዲሲ ሕዝብ የአውሮፕላን ማረፍያውን አጨኛንቆታል። መንገድ ተዘግቷል።

መንገደኞች ያለችግር ይተላለፉ ዘንድ የእስክንድር ጉዳይ በአፋጣኝ ማለቅ ነበረበት።

እስክንድር በዚያ መንገድ ወጥቶ ባንዲራዋን ይዞ የሚጠብቀው ወገን ጋር ተቀላቀለ። የፖሊሶቹ ስጋት ግን አሁንም አልቀረም። ከብዙ ጭንቅንቅ በኋላ በተዘጋጀለት ሊሞዚን ወጥቶ በአጀብ ወደ ማርቲን ሉተር መታሰብያ ፓርክ ሄደ።  አዳልስ ኤርፖርት እስከ ፓርኩ ድረስ በፖሊስ ታጅቦ አመራ። መንገዱ በመኪና ተሞልቶ የትራፊክ ጭንቅንቁ አይጣል ነበር። በኢትዮጵያን ባንዲራ የሚያውለበልብ በመቶዎች የሚቆጠር መኪና በፖሊስ ታጅቦ ሲሄድ ልዩ ነበር።

ከ24 ዓመታት በፊት አሜሪካን ሃገር ሲኖር ጥዋት እየተነሳ የሚሮጥበት ፓርክ፣  አሁን የማርቲን ሉተር ሃውልት ሰፍሮበታል። እስክንድር ያንን ግዜ እያስታወሰ ደስታውን በእጥፍ ሞላው።

እኛም እንኳን ከልጅህ እና ከባለቤትህ ጋር በሰላም አገናኘህ እንላለን፡

ድል ለዲሞክራሲ

ክንፉ አሰፋ

Filed in: Amharic