>

የዶክተር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ የ62 ተካሳሾች ክስ እንዲነሳ ተወሰነ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የዶክተር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ የ62 ተከሳሾችን የክስ ሂደት ማንሳቱን አስታወቀ።
ተከሳሾቹ የወንጀለኛ መቅጫ ህግን አንቀጽ 464 እና 494 በመተላለፍ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያለና እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው ናቸው።
ኢዜአ ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባገኘው መረጃ መሰረት በእነ አበበ የኋላ የክስ መዝገብ የተጠቀሰውን አንቀጽ በመተላለፍ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ 18 ተከሳሾች ክስ እንዲነሳ ተወስኗል።
በእነ ማስረሻ ሰጠኝ መዝገብ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ችሎት ጉዳያቸው ሲታይ ከነበሩት 38 ተከሳሾች መካከል፥ አራቱ በሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው እንዲከላከሉ ብይን ተሰቶባቸዋል።
ስምንቱ ደግሞ በነጻ መሰናበታቸው ይታወሳል።
በተጠቀሰው መዝገብ የወንጀለኛ ህጉን አንቀጽ 464 እና 494 በመተላለፍ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠባቸውን ቀሪ 26 ተከሳሾች ክስ ደግሞ እንዲነሳ ተወስኗል።
በሰው መግደል ወንጀል እንዲከላከሉ የተበየነባቸው የአራቱ ተከሳሾች የፍርድ ሂደት ግን ባለበት ይቀጥላል ተብሏል።
በተመሳሳይ በእነ ቴዎድሮስ ዳንኤል መዝገብ የወንጀለኛ ህጉን አንቀጽ 464 እና 494 በመተላለፍ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያለ የ18 ተከሳሾች ክስ እንዲነሳ መወሰኑንም የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ
Filed in: Amharic