>

አቶ አዲሱ ለገሰ- ወደር አልባ የጸረ አማራ ፊታውራሪ፤ (ውብሸት ሙላት)

አቶ አዲሱ ለገሰ የአማረ ክልል አሁን ያለውን ድንበር ሲይዝ የክልል ርዕሰ መስተዳደር ነበሩ፡፡ እናም የክልሉ ድንበር የአሁኑ ሆነ፡፡ ከክልሉ ውጪ ይኖሩ የነበሩ አማራዎችን ዕልቂትና ሞት አለቃቸው አቶ ታምራት ላይኔ አጋፍረዋ፡፡ እኒህ ሰው አማራ አለመሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
አቶ አዲሱ ለገሰ ደግሞ በክልሉ ውስጥ የሚኖረውን ሰው በብዙ መንገድ ለስቃይና ለውርደት የዳረጉ ናቸው፡፡ አይደለም የሕዝቡን ጥቅም ሊያስከብሩ ይቅርና መሬቱን ሁሉ በሽልማት ለሌላ የሰጡ ሊባሉ የሚችሉ ሰው ናቸው፡፡ አማራ ክልል ውስጥ ኖረው ያማያውቁ ሰዎችን ለየዞኑ አስተዳዳሪ አድርገው በመሾም ክልሉን ባልተወለደ አንጅት ገዝተዋል፡፡
አቶ አዲሱ ለገሰ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር  እንዲሁም የብአዴን ሊቀ መንበር በነበሩበት ወቅት እንደው ከየቦታው ስለሚፈናቀለው ስለሚገደለው ስለሚባረረው አማራ ትንፍሽ ሲሉ ተሰምተው አያውቁም፡፡ በአማራ ስም አማራን እመራለሁ በማለት እንደዚህ ሰው የበደለን የለም፡፡ አሁን ላይ የክልሉ ሕዝብ ለሚያነሳቸው የድንበር ጥያቄዎች የአማራው ወኪል ሆነው በዚህ ሁኔታ እንዲቀመጡ ያደረጉት እኒሁ ሰው ናቸው፡፡
አቶ አዲሱ ለገሰ የቀድሞው  በደላቸው አልበቃቸው ብሎ አሁንም ከአማራ ጠል እና ጸረ አማራ ጓዶቻቸው ጋር ወደ ባህር ዳር በመዝመት ጸረ አማራዊ ትግላቸውን አጧጡፈውት ከርመዋል፡፡ እንግዲህ አራሳቸው ነፍጠኛ ሲሉን ትምክህተኛ ሲሉን እና ሲያስብሉን ኖሩ፡፡ በአባባነት ዕድሜያቸውም አልተወን አሉ፡፡ ያኔ የበደሉንን ብቻ ይዘው አማራን በመበደል ባለሃብት ሆነው ምናለ አርፈው ከአማራ ላይ በመውረድ ቢኖሩ?
እባክዎት አማራ ጠልና ጸረ አማራ የሆኑት ጓዶችዎች ይዘው ገለል ይበሉልን አቶ አዲሱ ለገሰ፡፡ የበደላችሁን ይበቃል! አቦ አዲሱ ለገሰ እባክዎትን ከአማራ ራስ ላይ ይውረዱ! ይብቃወት….ከፓርቲውም ጡረታ ይውጡ!

በተያያዘ:- አገር ያጠፋው አማራም የጠፋበት  Under  Invoice እና አገር አጥፊዎቹ፤ 

ውብሸት ሙላት

የዚችን አገር ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ካወሳሰቡት ኢፍትሐዊ የሀብት ሥርጭትና ክፍፍል፣ ዝቅተኛ ግብር ወዘተ እንዲኖር ከፍተኘውን ድርሻ የሚይዙት አስመጪዎች ናቸው፡፡
አገሪቱን በሚያምሳት የዶላር እጥረት መነሻነት ከውጭ የሚገዙ ዕቃዎችን (ሸቀጦችን) ከተገዙበት ዋጋ ዝቅ አድርጎ ሪፖርት ማድረግ የዘወትር ተግባር ሆኗል፡፡ ዝቅ ብሎ ለሚቀርብ ደረሰኝ ዶላር በሰቀቀን ለሚገኝባት አገር ብዙም ትኩረት አይደረግበትም፡፡
ዝቅ አድርጎ ሪፖርት በማድረግ ዝቅተኛ የጉምሩክ፣የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ኤክሳይዝ ታክስ ወዘተ ይከፈላል፡፡ ሲያስፈልግ ዓለማቀፋዊ ሙስና ሲያስፈልግ ፎርጅድ ሰነድ መጠቀም ተለምዷል፡፡
አገር ውስጥ የገቡ ብዙ ሸቀጦችም ሆኑ ዕቃዎች ያለደረሰኝ ይከፋፈላሉ፡፡ ደረሰኝ ለሚጠይቅ ነጋዴ አይሸጥለትም፡፡ ከዚያ አስመጨውም አሁንም Under Invoice አዘጋጅቶ ገቢውን ለገቢዎችና ጉምሩክ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ቴሌቪዥን በዶላር የተገዛበት ዋጋ ወደ ብር ሲቀየር 2000 ብር እንደሆነ አስመጭው ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ይህንን መሠረት አድርጎ ግብርና ታክስ ይከፍላል፡፡ ከዚያም ለአከፋፋዮችና ለሌሎች ነጋዴዎች በ10000 ብር ያለደረሰኝ ይሸጣል፡፡ ለገቢዎችና ጉምሩክ ግን 5000 ብር እንደሆነ አሁንም በፎርጅድ ሰነድ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ነጋዴውም 10000 ብር ለገዛው የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ደረሰኝ አይኖረውም፡፡ ሲሸጥም በተቻለ መጠን ያለደረሰኝ ነው፡፡ ምክንያቱም በተቀናናሽ እንዲያዝለት የሚያስችል ሰነድ የለውምና፡፡ ደረሰኝ ከሰጠ ደግሞ ፎርጅድ source documents ያዘጋጃል፡፡ በዚህ መንገድ አስመጭው ዝቅተኛ ግብር ይከፍላል፡፡ ነጋዴዎቹም ሳይወዱ በግዳቸው የተጭበረበረ ሰነድ ያዘጋጃሉ፡፡ ግብርም ለማጭበርበር ይገደዳሉ፡፡
ችግሩ የበለጠ የሚከፋውና የሚወሳሰበው አስመጭዎቹ የአንድ ሰፈር፣ብሔርና ዘመዳዝማዶች ሲሆኑ ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት የፈለገ የኤሌክትሮኒክስ ንግዱን ብቻ ወደ መርካቶ ጎራ በማለት መመልከት ነው፡፡ አስመጭዎቹ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ማንነታቸው የታወቀ እና አይነኬ-ዘመዳዝማዶች ወይም በአንድ ብሔርነት የተሣሠሩ፡፡ አሠራራቸው ወጥ ነው፡፡  እንዴት እንደሚሸጡ በአንድ ቀን ይገባችኋል፡፡ በዚህም አገር ይጎዳል፡፡ ከአስመጭዎቹ ክልል በስተቀር (በመጨረሻ እዚያው ኢንቨስት ማድረግ ስለተመለደ) ጉዳቱ የትየለሌ ነው፡፡
ነጋዴዎቹም ወደ አዲስ አበባ መሰደድ ዕጣ ፋንታቸው ነው፡፡ አዲስ አበባ ባህር ናታ፡፡ ብታጭበረብርም ቢያንስ ዐይን ውስጥ አትገባም፡፡  የክልል ገቢ ይቀንሳል፡፡ ነጋዴም ይሰደዳል፡፡ በተለይ የአማራ ክልል ነጋዴዎች ወደ አዲስ አበባ መሰደድ እጅግ በጣም የተለመደ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የኮምቦልቻ ጉምሩክ እና ደረቅ ወደብ ስለምን አፉን ከፍቶ ይውላል? ምክንያቱም የዚያ አካባቢ ተወላጅ አማራዎች አስመጭ ስለሌሉ ነው፡፡ የምሥራቅ አማራ ነጋዴዎች በብዛት ብረታ ብረትም ሆነ ኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚያስመጡት ከአዲስ አበባ እና ከመቀሌ ነው፡፡
አማራ ከኢኮኖሚው ተገፍቷል፡፡ ይቺ አንዷ ማሳያ ናት፡፡ እስኪ የብረት እና የኤሌክትሮኒክስ አስመጪ የሆኑ ስንት አማራዎች አሉ የምታውቁ ወዲህ በሉ፡፡
በነገራችን ላይ ባለፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ እራት ግብዣ ላይ የአማራን ከኢኮኖሚው እንዴት እደተገፋ ለማሳየት የቀረበው አንዱ ምሳሌ እንደው ስሙ የሚታወቅ አማራ ኮንትራክተር አለ ወይ በሚል ጥያቄያዊ አስተያየት ነበር፡፡
Filed in: Amharic