>

150ኛ ዓመት የእቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ አሳዛኝ ሕይወትና አሟሟት (አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል)

‹‹እኔ ለመከራ የተፈጠርኩ ሰው ነኝ፤ የልጄን ነገር አደራ›› … እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ ኃ/ማርያም (ግንቦት 1860 ዓ.ም) 
የእቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ አሳዛኝ ሕይወትና አሟሟት (150ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያቸውን ምክንያት በማድረግ የተፃፈ) 
ከ አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል
[ፎቶው የእቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ ኃ/ማርያም አስክሬን ወደ ሸለቆት ሥላሴ ገዳም ሲወሰድ የሚያሳይ ነው]
እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ሕጋዊ ሚስት ነበሩ፡፡ ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ የመጀመሪያ ባለቤታቸው እቴጌ ተዋበች አሊ አሉላ ከሞቱ በኋላ በሕግ ያገቡት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤን ነው፡፡ እቴጌ ጥሩወርቅ የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም በደጃዝማች ካሣ ኃይሉ (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ) ደረስጌ ላይ የተሸነፉት የደጃዝማች ወቤ ኃይለማርያም ልጅ ናቸው፡፡
ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም መቅደላ ላይ ከሞቱ በኋላ የእንግሊዝ ጦር መቅደላ አምባንና አካባቢውን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ የታሰሩትን ፈትቶ (ምርኮኛና እስረኛ የነበሩትን ኢትዮጵያውያንን) ወደእንግሊዝ ለመውሰድ የሚጭነውን ሀብት ካዘጋጀ በኋላ ሚያዚያ 14 ቀን 1860 ዓ.ም የመልስ ጉዞ ጀመረ፡፡
በጉዞው ላይም የንጉሰ ነገሥቱ ባለቤት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ እና ልጃቸው ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ነበሩ፡፡
ይሁን እንጂ  እቴጌዋ ከመቅደላ ጀምሮ ጤንነት አልነበራቸውም፡፡ የእንግሊዝ ጦር መሪ ጀኔራል ሮበርት ናፒዬርም ጉዳዩን አውቆ ሐኪም መድቦላቸው ቢታከሙም ሊሻላቸው አልቻለም፡፡ ወቅቱ የበልግ ዝናብ የሚዘንብበት ጊዜ በመሆኑ ከላይ ዝናቡ ከታች ጭቃው በህመማቸው ላይ ተጨምሮ ስቃያቸውን ስላባባሰባቸው ጉዟቸውን በቃሬዛ ላይ ሆነው ለማድረግ ተገደው ነበር፡፡
ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ ከንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ጋር ወዳጅነት የነበረው እንግሊዛዊው ተጓዥና መልዕክተኛ ሆርሙዝ ራሳም እቴጌዋን ለማበርታት ‹‹አይዞዎት፣ ይበርቱ፣ ይድናሉ›› ሲላቸው … ‹‹አዬ ለመሞት ቀኔ የተወሰነ ነው፤ብሞትም አላዝንም፤ ጥንትም ስፈጠር ከልጅነቴ ጀምሮ ለመከራ የተመደብሁ ነኝ፡፡ አሁን መድኃኔዓለም ተስፋ ወደሰጠው ዓለም (መንግሥተ ሰማያት) ለመድረስ ብቻ ነው ምኞቴ፤ የልጄን ነገር አደራ›› ብለው እንደመለሱለት ጽፏል፡፡
እቴጌ ጥሩወርቅ ‹‹ጥንትም ስፈጠር ከልጅነቴ ጀምሮ ለመከራ የተመደብሁ ነኝ›› ያስባላቸው የወቅቱ ሕመማቸው ብቻ አልነበረም፡፡
አባታቸው ደጃዝማች ወቤ ኃይለማርያም ለመንገስ እየተዘጋጁ ሳለ በባለቤታቸው በደጃዝማች ካሣ ኃይሉ (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ) በጦር ሲሸነፉ እስራትና መጉላላት ደርሶባቸው ነበር፡፡ ደጃች ውቤ በወቅቱም ‹‹እኔን እንደዚህ ከማጉላላት ለኔ አንድ ጥይት አነሰኝ?!›› ብለው በምሬት ተናግረዋል፡፡ እቴጌዋም በአባታቸው እስራትና ሞት ብርቱ ሀዘን ወድቆባቸው ነበር፡፡
የአክስታቸው ልጆች የሆኑት ደጃዝማች ንጉሤና ደጃዝማች ተሰማ በ1852 ዓ.ም በንጉሰ ነገሥቱ ተሸንፈው ተማርከው በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ ያጋጠማቸው ሃዘንም የበረታ ነበር፡፡ ይህም አልበቃ ብሏቸው እርሳቸውም በአካባቢው ስለነበሩ ገና በወጣትነታቸው ንጉሰ ነገሥቱን ለማግባት ተገደዱ፡፡
ወንድሞቻቻው ደጃዝማች ጓንጉልና ደጃዝማች ካሣ በንጉሰ ነገሥቱ ተማርከው ታስረው ነበር፡፡ ከእስራት የተፈቱትም ከመቅደላ ጦርነት በኋላ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ሚስት ሆነው ሳለ ንጉሰ ነገሥቱ የየጁዋን መልከመልካመም ሴት ወይዘሮ የተመኙን ቅምጥ አድርገው እቴጌ ጥሩወርቅን ያስቀኗቸው ነበር፡፡
በሌላ በኩል ንጉሰ ነገሥቱ መቅደላ ላይ ራሳቸውን ካጠፉ በኋላም “በንጉሰ ነገሥቱ ተበድለናል” ያለው ሰው ሁሉ እቴጌዋን ለመጉዳት ይጋበዝ/ይዘጋጅ ነበር፡፡
ታዲያ ዳዊት ከመድገም ውጭ ሌላ ነገር ያልለመዱት ቆንጆዋና ለስላሳዋ እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ ይህን ሁሉ መከራና ስቃይ ተሸክመው ሊዘልቁ አልቻሉም፡፡ የአባታቸው እስራትና ሞት፣ የወንድሞቻቸው እስራት፣ የአክስታቸው ልጆች አሰቃቂ ሞት፣ በባለቤታቸው ዘንድ እንደንበኛ ሚስት አለመታየት … ይህ ሁሉ መከራ ከበሽታ ጋር ተደምሮ የእቴጌዋን ሕይወት አሳጠረው፡፡ ከዛሬ 150 ዓመታት በፊት (ግንቦት 7 ቀን 1860 ዓ.ም/ባለቤታቸው ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ከሞቱ ከሦስት ወራት በኋላ) አረፉ፡፡ ስርዓተ ቀብራቸውም በሸለቆት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን ተፈፀመ፡፡ ከራስ ወልደሥላሴ ጎን ተቀበሩ፡፡
[መረጃው ‹‹አጤ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት›› ከሚለው የክቡር አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ መጽሐፍ እና ከሌሎች መዛግብት የተገኘ ሲሆን አንዳንዱ ትረካ ቃል በቃል የተወሰደ ሳይሆን መጻሕፍቱን ሳገላብጥ ያየሁትን አዛምጄ ጽፌዋለሁ]
ነፍስ ይማር!
Filed in: Amharic