>

መፈራረጅ፣ መጠላላት፣ መጠቃቃት፣ መጠፋፋት በዚያ…ትውልድ ይብቃን!!! (ውብሸት ሙላት)

ሰሞኑን የተወሰኑ በጣት የሚቆጠሩ የአማራ አክቲቪስቶች ሌሎች አክቲቪስቶችን፣ ጋዜጠኞችን እና ፖለቲከኞችን ማብጠልጠል እና ማሳጣት ጀምረዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በጭራሽ መቀጠል የለበትም፡፡ በብዙ ምክንያቶች፡፡ 
እርስ በእርስ መዘላለፍና መጣላት መጠላላት የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደልና ግፍ ከማራዘም ውጭ ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም፡፡ መጠላላትና መከፋፈል ለአጥቂዎችና ለበዳዮች ምቹ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ለጠላት ምቹ መሆን ሆኖ መገኘት ደግሞ ጀግንነትም ፣ብልህነትም አይደለም፡፡
የአማራን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚደረገው ትግልና ጥረት መንገዱ ወይም ስልቱ አንድ ብቻ አይደለም፤ሊሆንም አይችልም፤መሆንም የለበትም፡፡ በአንዲት መንገድ ብቻ መጓዝ ለበዳዮች መመቻቸት ነው፡፡ ያችን መንገድ መዝጋት ወይም ማደናቀፊያ መፍጠር ብቻውን የአማራን ሕዝብ በደል ማረዘም ነው፡፡ የመታገያ ስልቶቹ ብዙ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስሆነም በተለያዬ መንገድ ነገር ግን ለአማራ ሕዝብ ጥቅም እና መብት እስከታገሉ ድረስ አንዱ ሌላውን መቃወም የለበትም፡፡ መደገፍ ላይጠበቅበት ይችላል፡፡ መታየት ያለበት ግን ግቡ ነው፡፡ ስለ አማራ  የተለያየ ስልት በመከተል የሚሠራን ሰው ማደናቀፍ ትርፉ አማራን መጉዳት ነው የሚሆነው፡፡
ስለ አማራ ሕዝብ ጥቅም እና መብት ጉዳይ የተለያዩ ስልቶችን መከተል ተገቢ ነው፡፡  እየተደረገም ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የሚከተሉትን እንጥቀስ፡፡
ሀ. ኦሮማራ… 
ኦሮማራ ሐሳብ እንጂ እሱን ብቻ የሚከተል ቡድን የለም፡፡ ግን ፋይዳው የሚናቅ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው በሚሊዮን የሚቆጠር አማራ በኦሮሚያና በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ይኖራል፡፡ በእነዚህ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩትን አማራዎች ቢያንስ ለጊዜውና በአሁኑ ወቅት ከጥቃት ለመታደግ የሚያስችል አደረጃጀት የለንም፡፡
ስለሆነም በዋናነት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ከሌሎች ብሔሮች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት በጎ መሆን አለበት፡፡ ለአብነት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲፋናቀሉ፣ የአበጠር ወርቁ ብልት ሲቆረጥ መከላከል የሚያስችል አደረጃጀትም አወቃቀርም ስለሌለን ጉዳት ከደረስ በኋላ እግዛና እርዳታ ከማድረግ ያለፈ ድርሻ ሊኖረን አልቻለም፡፡
ስለሆነም፣በኦሮማራና በመሳሰሉት ፕሮግራሞች ውስጥም የሚሳተፉ ሰዎች ከክልሉ ውጭ የሚኖረውን አማራ ከጥቃት ለመከላከል ድርሻ አላቸውና እነሱን መኮነን፣ማብጠልጠል ቢያንስ ለጊዜው ጉዳቱ አማራ ላይ ነው፡፡ ቢያንስ አማራ ላይ የሚደርስን ጥቃት ለመቀነስ ይረዳል፡፡  ስለዚህ ሊበረታቱ እና ሊደገፉ ይገባቸዋል፡፡
ለ. በውጭ ያሉ የአማራ አክቲቪስቶች፤
በአገር ውስጥ ሆኖ መሥራት የማይቻልን፣ መዘገብም ማስተጋባትም የማይቻልን ብዙ ጉዳይ በተለያዩ ሚዲያዎች በማቅረብ፣ በማጋለጥ ወዘተ በርካታ በጎ ነገሮችን እያደረጉ ነው፡፡ ወገኖቻችን ሲጎዱም ገንዘብ በማሰባሰብ፣ በተለያዩ የውጭ ተቋማትና መንግሥታት ዘንድ በቅርብ ጫና በመፍጠር እየታገሉ ነው፡፡ የኤች አር መጽደቅ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ ስለሆነም እነሱም ለአማራ ሕዝብ እየሰሩና እየተጋሉ ነውና ሊበረታቱ ይገባቸዋል፡፡
ሐ. በአገር ውስጥ ያሉ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች፤
የደኅንነቱንና የፖሊሱን አፈና፣ እስር፣ እንግልት፣ ድብደባ፣ ወዘተ ተቋቁመው ቤተሰብ መመሥረት፣ ሐብትና ንብረት ማፍራት ሳያምራቸው መሳቀቅንና መፍራትን ከውስጣቸው አውጥተው ጥለው  የወገናቸው ሰቆቃ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ የሚታገሉትን ማበረታታት እንጂ መንቀፍ አይገባም፡፡ እነሱም ቢሆኑ ለአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ የመብትና ጥቅም መከበር እየታገሉ ነውና!
መ.  አዲሱ የሚመሠረተው የአማራ ፓርቲ፤
ይህ ፓርቲ ከፍተኛ ተስፋን ሰንቆ የተለያዩ ፈተናዎችን በመጋፈጥ የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር በመቋቋም ላይ ነው፡፡ ፈተናው ገና ለማደረጃት የመጀመሪያውን ስብሰባ ለማድረግ ሲሞከር እንኳን የተከሰተው ነገር ድብደባ እና እስራት ነው፡፡ ይሁን ፈተናዎቹና ተግዳሮቶቹ ምንም ይሁኑ ምን አባላቱም የግላቸውንና  የቤተሰባቸውን ጉዳይ ከአማራ ሕዝብ በታች በማድረግ ለአማራ ሕዝብ መብትና ጥቅም ለመስራት በመታገል ላይ ናቸውና ሁለንተናዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡  ብአዴን ሊያደናቅፋቸውና እንቅፋት ሊሆንባቸው አይገባም፡፡
ሠ. ብአዴን
 ብአዴን የአማራን  ሕዝብ ሳይወክል፣ የመወከል ፍላጎት ሳይሆን አማራን የማጥቃትና የማስጠቃት ሚና ወስዶ ኖሯል፡፡ በተለይም በብሔራቸው አማራ ያልሆኑ ጸረ አማራ እና አማራ ጠል የሆኑ ሰዎች የተሰባሰቡት፣ከአናቱ ላይ ቁጭ ብለው ሲዘውሩት ኖረዋል፡፡ አሁንም ከአናቱ ላይ ገና አልወረዱም፡፡
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከፓርቲው ከፍተኛ አመራር ጀምሮ እስከታች ድረስ የሚገኙ የተወሰኑ የብአዴን አባላት የአማራን ጥቅምና መብት ለማስከበር እየጣሩና እየተጋሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ብአዴን ቢያንስ አማራን የሚጠሉትን  ከአማራ ብሔር  ውጭ የሆኑ አባላቱን (አገው አዊ፣ኽምራ፣ቅማንት፣አርጎባና የከሚሴ አካባቢ አሮሞን አይጨምርም) እንዲሁም  አማራም ሆነው ባንዳ የሆኑትን ከፓርቲው ሊያባርር ይገባል፡፡  በዚህ ረገድ ለአማራ ሕዝብ ጥቅምና መብት ከመቆምና ከመሥራት በተቃራኒው እያጠቁም እያስጠቁም ያሉትን ለሕዝብ ይፋ እያደረጉ ማሸማቀቅ (Naming and Shaming) ያስፈልጋል፡፡
ብአዴን ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጋ አባላት አሉት፡፡ እነዚህ አባላት ስለ አማራ እንዲቆረቆሩ፣ እንዲያስቡ፣ እንዲከራከሩ ማድረግ እንጂ መጣላትና ግጭት ውስጥ መግባት አሁንም ቢሆን ለአማራ ሕዝብ አይጠቅምም፡፡ እነዚህ ጋር መጣላትና አተካራ ውስጥ ለበዳዩ መመቸት ነው፡፡ የፈለጉትን መንገድ ይከተሉ ነገር ግን ስለ አማራ እንዲሰሩ.እንዲያስቡ እንዲታገሉ እንዲቆረቆሩ ማድረግ ይጠቅማል፡፡ በዴሞክራሲያዊ አካሔድ እንዲያምኑ ማድረግ ነው፡፡ ካልሆነ አዲሱ ፓርቲም የመጀመሪያና ዋና ትግሉ ከብአዴን ጋር ብቻ ሆኖ እርስ በራሳችን በመጣላት ታጥረን የታላቁን የአማራን ሕዝብ ጉዳትና የሕልውና ጥያቄ እንረሳዋለን፡፡
በተጨማሪም አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ የአማራ ሕዝብን ለማግኘትና ለመድረስ (ከክልሉ ውጭ የሚኖሩትንም ጨምሮ)  ከብአዴን የተሻለ አደረጃጀት ገና አልተፈጠረም፡፡  ቢያንስ አዲሱ ፓርቲ ተፈጥሮ ብአዴንን መተካት እስከሚችል ድረስ የብአዴን ሰዎችን አማራዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ማድረግ ይጠቅማል፡፡ አዲስ ሐሳብ  ባያመጡም፣ አቅም ባይኖራቸውም ወደ ሚሊየን የሚጠጋ የብአዴን አባል ሁሉ መልሶ አማራን መበደል እና ማስበደል ውስጥ መግባት የለበትም፡፡
ረ. ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድሙ የአንድነት ሰዎች፤
ዘመኑ የዴሞክራሲ ነው፡፡ አማራ በአማራነቱ ከሚደራጅ ይልቅ ኢትዮጵያነትን ቢያስቀድም ይሻላል የሚሉም ስላሉ ሐሳባቸውን ማክበር ይገባል፡፡ መሰባሰብና መደረጃት ያለብን እንደ አማራ እንጂ በኢትዮጵያዊነት ስም ሊሆን አይገባም የሚሉትን ማንቋሸሽና ማጣጣል መሳደብ ወዘተ መኖር የለበትም፡፡ ሁሉም ተከባብሮ እና ተደማምጦ መሥራት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከዚህ አንጻር የአማራ ብሔርተኝነት ፋሽስት አስመስሎ ማቅረብ ከአማራ ዋና ጠላት ከሕወሃትም የበለጠ ጠላት መሆን ነው፡፡ አንዱ ሌላውን የማደናቀፍ ተግባር ፈጽሞ መኖር የለበትም፡፡
በዚያ ላይ ኢትዮጵያዊነት ላይ ተመስርተው የሚሰሩ አማራ የሆኑ ሰዎችም በዚሁ አሰላለፋቸው ከሌሎች ሰዎች ጋር ተባብረው እንደዚህ ዓይነት ድርጂቶች ውስጥ አማራን ይወክላሉ ማለት ነው፡፡ አማራ ለአማራነት እስከቆመ ድረስ በተለያዩ አደረጃጀቶች ቢሳተፍ ጉዳት የለውም፡፡ ይጠቅማል እንጂ፡፡ ቁምነገሩ አንዱ ለአንዱ እንቅፋት አለመሆን ነው፡፡
እንዲህ እንዲህ እያሉ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ዋናው መለኪያ ግን አማራነት የሕልውና ጉዳይ ነውና ለአማራ መብትና ጥቅም መቆማቸው ወይንም አለማደናቀፋቸውን ነው፡፡ ካላደናቀፉ ማንም የመሰለውን ማራመድ መብቱ ስለሆነ መታገስ እና የሐሳብ ፍልሚያ ማድረግ ነው፡፡
በአጭሩ የአማራ የትግል ጉዞ የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን የሕልውና ጥያቄ አንግቦ ለአንድ አማራ ጥቅምና መብት መከበር የሚሰራን ማንንም ሰው ሌላው ሊያደናቅፈው ብሎም ንትርክና ጥል ውስጥ ሊገባ አይገባም፡፡
በግንቦት ሰባት ስምም ይሁን በሌላ ምክንያት የታሠሩ አማራዎች ዞሮ ዞሮ ለሕዝባቸው ሲሉ ሕይታቸውን ሁሉ ሳይቀር ለመገበር ዝግጁ ነበሩና ከእስራት ሊፈቱ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር አንዳርጋቸው ጽጌም ሆነ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ በግንቦት ሰባት ሰበብ የታሰሩ አማራዎች ሊፈቱ ይገባቸዋል፡፡ አንዳርጋቸው አይፈታ ማለት ተገቢነት የለውም፡፡ የታሰረው አማራ በመሆኑ ነው፡፡ በሕወሃት ዘንድ ሌሎቹን አመራሮች ማሰርም መያዝም አልተፈለገም፡፡ ምክንያቱም የግንቦት ሰባት መኖር ወይም አለመፍረስ ለሕወሃት ይጠቅማልና፡፡ አማራን ለማሸማቀቅና ለማሰር ጥሩ ስልታቸው ነውና፡፡
የግቦት ሰባቱ አንዳርጋቸውም ይፈታ፡፡  የብአዴኑ መላኩ ፈንታም ይፈታ፡፡ እነ ሊዲያም፣ ምስጋናው አንዷለምም፣መሳፍንት ታምራትም፣ ሔኖክ የሺጥላም፣ሚኪ አማራም፣ጌታቸው ሽፈራውም፣ አዲሱ የአማራ ፓርቲም፣ብአዴንም (ከላይ የገለጽኩት ሳይረሳ)…..ወዘተ ለአማራ ሕዝብ ያስፈልጋሉ፡፡ ትግሉ በየአቅጣጫው ነው መሆን ያለበት፡፡ ግቡም የአማራ ሕዝብን መብትና ጥቅም በላቀ ሁኔታ ማስከበር ነው፡፡ መፈራረጅ፣ መጠላላት፣ መጠቃቃት፣ መጠፋፋት በዚያ….ትውልድ ይብቃን፡፡ አማራ አማራን ማጥቃቱም፣ ማሰደቡም፣ መስደቡም ይብቃ! ማበረታታትና መደናነቅ መወዳደስ ባይኖር እንኳን መሰዳደብ መዘላለፍ አማራዊ ባህርይ አይደለም፡፡ ጸረ አማራና አማራ ጠል  የሚሆኑትን ግን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ነው፡፡
አማራ ዳግም ታሪኩን ያድሳል፡፡  አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንዱ አማራ፡፡ 
መክት!!!!!
Filed in: Amharic