ምልከታ 1
ኦህዴድ በግፍ ያባረራቸውን የኦ.ዲ.ኤፍ አመራሮች በእቅፍ ተቀበላቸው!?!
ስዩም ተሾመ
እንግዲህ የቀድሞ #የኦነግ መሪ የሆነው ሌንጮ ለታ ወደ ሀገር ቤት ሲገባ አቀባበል ሊያደርግለት የተገኘው #አባዱላ ገመዳ ነው። ይሄ ምን ትርጉም አለው? በመጀመሪያ ደረጃ የህወሓትን የስልጣን ጥማትና የኢኮኖሚ ዘረፋ ለማሳካት በሚል የአባዱላ ኦህዴድ የኦነግን ሌንጮ ለታ ከሀገር አስወጣው። ውሎ-ሲያድር የህወሓት ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ ለአባዱላና ኦህዴድ ተገለጠላቸው። በመቀጠል አባዱላና ኦህዴድ ከቄሮዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር የህወሓትን የስልጣን ጥማትና የበላይነት በማኮላሸት የመሪነት ስልጣኑን በእጃቸው አስገቡ። በመጨረሻም በግፍ ከሀገር ያባረሯቸውን የቀድሞ የኦነግ፣ አሁን ደግሞ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ODF) አመራሮች ወደ ሀገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቀረቡላቸው። የODF አመራሮች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ከሀገር እንዲወጡ ያደረጋቸው የኦህዴድ መሪ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በመሄድ አቅፎ እየሳመ ተቀበላቸው። በህወሓት የስልጣን ጥማትና የበላይነት ምክንያት የተጣሉ የኦሮሞ ልጆች “እንኳን ደህና መጣህ?” እና “እንኳን ደህና ቆየህኝ” ተባብለው “ይቅር” ተባባሉ። ይህ ክስተት “ታሪካዊ” ካልተባለ “ታሪካዊ” የሚባል ነገር የለም!
ምልከታ 2
ዛሬ የሴት ጡት አስቆራጩና የሰው ጭን ስጋ ለምሳ የሚጋብዘው Sadist ሰው አዲስ አበባ ገብቷል
ቬሮኒካ መላኩ
የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሌንጮ ለታና የሚመራው ኦነግ የተባለው ቦቅቧቃ ድርጅት በተሳተፈበት የአጭር ጊዜ የፖለቲካ አረንቋ የሰራውን ነውር በመፅሃፋቸው እንደሚከተለው ገልፀውታል ።
………
<<…… እነ ሌንጮና ኦነግ የሚሰሩት ስራ እኮ መስመሩን የሳተ ነበር። የኦህዴድ ሴት ታጋዮች በኦነግ ጡታቸው ይቆረጥ ነበር። ወንዶች ደግሞ የጭናቸው ስጋ እየተቆረጠ ብሉት ይባሉ ነበር። በበደኖ በርካታ ሰዎች ከእነህይወታቸው በገደል እየተወረወሩ ተገድለዋል። ይሄ የተፈፀመው በኦነግ ወታደሮች መሆኑን የኦነግ አመራር አባቢያ አባ ጀበል ፓርላማ ቀርቦ አምኖ ነበር። ይሄ የተመዘገበ ታሪክ ነው……።>>
ዳንዲ የነጋሶ መንገድ
ገፅ 150 ።
…
እኛ ስለኦነግ ጡት ቆራጭነት ፣ የሰው ጭን ስጋ አስበሊነት ማስረጃ የምናቀርበው እንደ እናንተ ያላየውን ከሚፅፈው ፈረንጅ ሳይሆን በአይኑ በብረቱ ከተመለከተው ከራሳችሁ ሰው ነው።
ዛሬ የሴት ጡት አስቆራጩና የሰው ጭን ስጋ ለምሳ የሚጋብዘው Sadist ሰው አዲስ አበባ ገብቷል።
ምልከታ 3
የሰቆቃ ታሪክ እያሰብኩ የነገን ተስፋ ማጨለም አልሻም!
ስዩም ተሾመ
የእነ ሌንጮ ለታ እና የኦነግ ጉዳይ ሲነሳ ቁስል ማከክ ከተጀመረ ሁሉም የራሱ ቁስል አለበት። በተለይ የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን ወደኋላ ተመልሰው አስከፊውን የታሪክ ገፅታ ማጉላት ከፈለጉ በጣም ብዙ መረጃና ማስረጃ እየጠቀሱ መጨቃጨቅ ይቻላል። ዛሬ ባወጣሁት ፅሁፍ ዙሪያ አንዳንድ የአማራ ልሂቃን በተለይ በአርሲና በሐረርጌ አከባቢዎች የኦነግ ታጣቂዎች በአማራዎች ላይ የፈፀሙትን ጭፍጨፋ በመጥቀስ የቀድሞ የኦነግ አመራሮች ለፍርድ ይቅረቡ እያሉ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አቶ ሌንጮ ለታ የህወሓት/ኢህአዴግ ሊቀመንበር ከነበረው መለስ ዜናዊ ጋር በአማራ ሕዝብ ላይ ያሴሩ ነበር በማለት ይጠቅሳሉ።
መልካም፣ በዚህ መልኩ ቁስል ማከክ ከተጀመረ፣ የኦሮሞ ልሂቃን ደግሞ የአፄ ሚኒሊክ ጦር በተመሳሳይ በአርሲና በሐረርጌ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በማንሳት የራሳቸውን ቁስል ማከክ ይጀምራሉ። ልክ እንደ ሌንጮ ለታ ሁሉ የግንቦት7 መሪው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከመለስ ዜናዊ ጋር ሲሞዳሞድ እንደነበር ያወሳሉ። እንዲህ እያለ የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን ቁስል ማከክ እና ማቆሚያ የሌለው አተካራ ይቀጥላል።
በ19980ዎቹ ልጅም ብሆን በአርሲ አርባ-ጉጉ ምን እንደተፈጠረ አስታውሳለሁ። የራሴ የስጋ ዘመዶች አርባ-ጉጉ ውስጥ በኦነግ ታጣቂዎች በጥይት ተገድለዋል፣ የተቀሩት ደግሞ በትልቅ ገደል ውስጥ ከነነፍሳቸው ተወርውረዋል። በተመሳሳይ የራሴው ስጋ ዘመድ አራባ የሚሆኑ ኦሮሞችን ገድሎ ከእኛ ቤት ተደብቆ እንደነበር አስታውሳለሁ።
እኔ ከቀድሞ የኢትዮጲያ ታሪክ ጥሩን እያወሳሁ፣ አስከፊውን የታሪክ ገፅታ መዘንጋት እመርጣለሁ። የትላንቱን ቁስል እያከኩ ለነገ ቂምና ጥላቻ ስደግስ አልገኝም። ከዚያ ይልቅ፣ ትላንትን በይቅርታ አልፌ ነገን በተስፋ መኖር እሻለሁ። አዎ…የትላንቱን የሰቆቃ ታሪክ እያሰብኩ የነገን ተስፋ ማጨለም አልሻም። የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች በአንድነትና በአብሮነት በሰላም የሚኖሩበት ግዜ እንዲመጣ የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።