>

ኦሮማራ በእስርቤት “ገርባነት”፡  ስቲቭ “ወልቃይቴው” (ውብሸት ሙላት)

መቼስ ኦሮሞ በኦነግነት እና አማራ ደግሞ በግንቦት ሰባትነት በአሸባሪነት ክስ ብዙ እስር ቤቶችን አጥለቅልቆታል፡፡ በታወቁትም በማይታወቁትም እስር ቤቶች አብረው ናቸው፡፡ በተለይ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአሸባሪነት የሚከሰሰው አማራ ቁጥሩ በብዙ እጥፍ ጨምሯል፡፡ “ሳይደግስ አይጣላም” እንዲሉ ይህ መጥፎ አጋጣሚ ግን በውሸት የተገነባውን የጥል ግድግዳ ውሸትነቱ ታውቆ ፍቅርና አንድነትን አምጥቷል፡፡
ይህ እንዴት እንደሆነ ወይም እንደመጣ ለማስረዳት በቅርቡ ከእስር ከተፈታ በኋላ የተዋወቅኩት ሰው ያጫወተኝ ላካፍላችሁ፡፡
#ሁለቱ_ታራሚዎች
“ሁለቱ ታራሚዎች”  የሚለውን ስያሜ ያወጣው ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ነው፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት ኦሮሞና አማራ የጠባይ ማረሚያ ቤት ውስጥ ገብተዋል ነው ዋና መልእክቱ፡፡  ይህ እውነት ነው፡፡  በየማረሚያ ቤቱ ሂዱ እውነትነቱን ታውቃላችሁ፡፡
በዚህ ዓመት ብቻ እንኳን ከእስር በየጊዜው ቢፈቱ ቢፈቲ ማለቂያ ያጣው ኦሮሞና አማራ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚሳዩት ገና ወደ 30 ሺህ የሚገመት የኦሮሞ እስረኛ ገና የት የት እንዳለ አልታወቀም፡፡ 40ሺ የሚጠጋ ኦሮሞ በዚህ ዓመት ተፈቷል፡፡
የአቶ ለማ መገርሳ መንግሥት አሮሚያ ክልል ውስጥ ድብቅ እስር ቤት ይኖር ይሆን እንደ በማለት ክልሉን አስፈትሸዋል ይባላል፡፡ ከሽብር ጋር በተገናኘ ከአስር ሺ በላይ አማራዎች በየማረሚያ ቤቶቹ ይገኛሉ፡፡ ምጥ ይግቡ ስምጥ የማይታወቁት ግን ቁጥራቸውንም ለመገመትም አስቸጋሪ ነው፡፡ አማራ ክልል ላይ የምሥጢር እስር ቤቶች ይኑሩ አይኑሩ ለጊዜው መረጃ የለኝም፡፡ በርካታ የአማራ እና የኦሮሞ እስረኞች ግን ሦስት ክልሎች እንዳሉ አንዳንድ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ትግራይ፣ኢትዮጵያ ሶማሌ እና አፋር፡፡
እስኪ በየቦታው የሚገኙትን እስረኞች ኦሮሞና አማራ  ስለመሆናቸው አገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ነው፡፡ ምስክር ካስፈለገ በኦሞ ስኳር ፕሮጀክት በሙስና  ወንጀል  የተከሰሰውን ‘ስቲቭ’ የተባለውን  ቻይናዊ ምስክርነት  እንካችሁ፡፡
#ስቲቭ_ወልቃይቴው_እና_ትዝብቱ
ስቲቭ ተይዞ የታሰረው ማእከላዊ ነበር፡፡ ሳይቤሪያ ስድስት ቁጥር፡፡ እሱ በታሰረበት ወቅት በዚች ክፍል ውስጥ ወደ 30 ገደማ አማራ እና ኦሮሞ እስረኞች ነበሩ፡፡ በዚች ክፍል ውስጥ የታሠሩት ሁሉም በሽብር ክስ የተጠረጠሩ ናቸው፡፡ ስቲቭ ግን በሙስና፡፡
ስቲቭ አማርኛ ይናገራል፡፡ እንደገባም “በቃ አማራ እና ኦሮሞ ብቻ ነው የሚታሰረው አይደል?” አለ በራሱ ማንም ይሄንን ሳይነግረው፡፡ ከየት ከየት አካባቢ ብዙ እንደሚታሰር ስለሚያውቅ “በሉ ያው እኔም እዚህ የመጣሁት ወልቃይቴ ስለሆንኩ ነው፤ ወልቃይቴ ነኝ”  አለ፡፡ ስቲቭ ወልቃይቴ ሆነ፡፡
ስቲቭ ትዝብት አለው ፡፡ ትዝበቱም በአጭሩ የሚከተለው ነው፡፡ አንድ መንግሥት ከገበሬ ጋር በርዕዮተ ዓለም ከተለያየ፣ ገበሬን አሳምኖ መምራት ካቃተው ያ መንግሥት እንደ መንግሥት መወሰድ የለበትም፡፡ ገበሬ አሸባሪ ሆነ ማለት የራሱን (የገበሬውን) ርዕዮተ ዓለም መንግሥት ላይ ለመጫን እየታገለ ነው ማለት ነው፡፡  አብሮት ስድስት ቁጥር የነበረው ታሳሪ የነገረኝ ነው፡፡
አሸባሪነት በዋናነት ፖለቲካ፣ ርእየተ ዓለም ወይም ሃይማኖትን በግዳጅ ሌላ ላይ መጨን ነው፡፡ የጸረ ሽብር አዋጁም ለሽብር የሰጠው ትርጉም ላይ ይሄው ሀሳብ ተካትቷል፡፡ እነዚህ የገበሬ አሸባሪዎች መንግሥት ላይ ፖለቲካ ወይም ርእዮተ ዓለም በግዳጅ የሚጭኑ ከሆነ መንግሥት ፖለቲካዊም ሆነ ርእዮተ ዓለማዊ ዕውቀቱ ከገበሬው ንቃተ ሕሊና ያነሰ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ እውነት ሊሆን ስለማይችል እውነታው “ሊበሏት ያሰቧት አሞራ ጅግራ ናት” ይሏታል ነው ነገሩ፡፡
#የአለማየሁ_ጉጆ_ምስክርት
አቶ አለማየሁ ጉጆ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ዲኤታ ነበሩ፡፡ ብሔራቸው ደግሞ ሲዳማ ነው፡፡ እሳቸው እና ሌሎች በሙስና የተከሰሱ ሰዎች በሽብር የተከሰሱ ሰዎች ጋር ይታሰራሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም ከፍርሃታቸው የተነሳ ለሦስት ቀናት ያህል ከእስረኞች ጋር ማውራትም አልቻሉም፡፡
ውሎ ሲያድር ግን ብዙዎቹ በታሳሪዎቹ ብስለት እና ጥበብ በጣም ተገረሙ፤ ተደመሙ፡፡ ደግሞ፣ ሽንት ቤት አጠገብ (ክፍሉና ሽንት ቤቱ ምንም በቅርበትም ሆነ በጥራት ልዩነት የለውም) በመታሰራቸው እየደረሰባቸው የነበረውን በደል አቶ አለማየሁ ለፍርድ ቤትም ተናግረዋል፡፡
ለታሳሪዎቹም ሐዘኔታቸውን፣ አድናቆታቸውን ገልጸው እሳቸው እንደ መንግሥት ባለሥልጣን ይህንን ዓይነቱን በደል እንደማያዉቁ ተናግረዋል፡፡ ከዚያም ለብዙ እስረኞች አልባሳትና ምግብ ያስመጡላቸው ነበር፡፡
አቶ አለማየሁን ተቀብሎ ቃለመጠይቅ ያደረገላቸው አንዱ በግንቦት ሰባት ስም የታሰረ ሰው ስለ ግንቦት ሰባት ሰምተው ያውቁ እንደሁ ይጠይቃቸዋል፡፡  እሳቸውም ትንሽ ትንሽ እንደሰሙ ይመልሳሉ፡፡ ከዚያም “አንዳርጋቸው ጽጌንስ ያውቁታል? ይላቸዋል እሳቸውም  “እንዴ አንተ ነህ እንዴ አንዳርጋቸው ጽጌ የምትባለው?” ብለው በድንጋጤ መለሱ፡፡ አቶ አለማየሁ ስለ ግንቦት ሰባት አለማወቃቸው ማረጋገጫው ዕድሜው ገና በሰላሳዎቹ አጋማሽ እንኳን የማይደርስን ልጅና አቶ አንዳርጋቸውን መለየት አለመቻላቸው ነው፡፡ ሚኒስትር ዲኤታው አንዳርጋቸውን በመልክ አያውቁትም እንኳንስ የኢትዮጵያን ፖለቲካ!
#የአሸባሪነት_ክብር
እስር ቤት ግባ፡፡ የተከሰስከው በአሸባሪነት ከሆነ ማንም ያከብርሃል፤ ከአሳሪዎቹ በስተቀር፡፡ “ዱርየዎች” ተብለው የሚታሰሩት ቀደም ሲል በአሳሪዎች እየተከፈላቸው በሽብር የተከሰሱ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደርሱ ነበር አሉ፡፡ ኋላ ኋላ ዱርየዎቹም እያከበሯቸው በሽብር የተከሰሱትም እራሳቸውን  ከመከላከል ወደ አጥቂነት በመቀየራቸው ይህ ዓይነቱ መንግሥታዊ ዱርዬነት እየቆመ ሔደ አሉ፡፡ በሙስና የተከሰሰ ብዙ ጊዜ አይወደድም፡፡ ሆን ብሎ መንግሥት ያጠቃቸው ከሆኑ ግን ይታዘንላቸዋል፡፡
በሽብር መከሰስ በእስረኞች ዘንድ የሚያስከብር ነው ብለናል፡፡ ሲሰርቁ፣ ሲዘርፉ ወዘተ ሳይሆን ስለመብት ሲታገሉ መያዝ እውነትም ቢያስከብር እንጂ የሚያዋርድ አይደለም፡፡ ታዲያ አንዱ ትንሽ የአእምሮ ሕመም ያለበት ሰው እናቱን ደብድቦ ይታሰራል፡፡ ከዚያ ይህ እስረኛ ለዓቃቤ ሕግና ለፍርድ ቤትም ሁል ጊዜ “ክሴን ወደ ሽብር ቀይሩልኝ፤ ዞሮ ዞሮ እኔም ያደረግኩት ከሌሎቹ አይለይም” ይል ነበር አሉ፡፡
#ኦሮማራነት_በእስር_ ቤት
ኦሮሞም ሁን አማራ በሽብር ከተከሰስክ ትዋደዳለህ፡፡ በእርግጥ ሌሎችም በሽብር ከተከሰሱ እንዲሁ የዚሁ አካል ናቸው፡፡ ማንኛውም ኦሮሞ እንደ ፖለቲካ አደረጃጀትና አተያይ በአማራነት መደራጀትን ይደግፋሉ፤ ያከብራሉ፡፡ በኦሮሞ ዘንድ የመገንጠል ነገር ፍጹም ተገቢ እንዳልሆነ፣ ከጭቆና ለመላቀቅም ኦሮሞና አማራ አብሮ መታገል እንዳለበት የዘወትር አጀንዳ ነው፤ በየእስር ቤቱ፡፡
እንግዲህ በሽብር የሚከሰሱት አማራ እና ኦሮሞ ናቸው ብለናል፡፡ አልፎ አልፎ ሌሎች ብሔሮች ቢኖሩም፡፡  አብረው የሚታሰሩትም እስር ቤቱንም የሞሉትም እነሱው ናቸው፡፡ በመሆኑም አብሮ በመኖር አንድ ሆነዋል፡፡ በተለይ ማእከላዊ፣ ቂሊንጦ ቃሊቲና ዝዋይ ለሚታሰሩት ምግብ የሚቀርበው በብዛት የሚመጣው ከኦሮሞ ነው፡፡ አብሮ መብላት መጠጣት ልማድ ነው፡፡ የኦሮሞም የአማራም አሳሪው አንድ ነው፡፡ ታሳሪዎቹም አንድ ናቸው፡፡
ይቅርታ መባባል፣ መገናዘብ መግባባት በሽብር በተከሰሱ ኦሮሞና አማራ ዘንድ የዘወትር እና ምንም ዝንፍ የማይል ባህርይም መለያም ነው፡፡ በድንገት ይህንን የሚጥስ አጋጣሚ ከተከሰተም በፍጥነት እርምት ይወሰዳል፡፡ በዚህ መልኩ  እየተኖረ ከእስር ቤቶች በአንድኛው  ይህንን የሚጥስ አንድ ክስተት ተፈጸመ፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡
አንድ የኦሮሞ ታሳሪ “ኦሮሚያ መገንጠል አለባት” የሚል ሐሳብ አነሳ አሉ፡፡ ሐሳቡን ያነሳው ለአማራ ታሳሪዎች ነው፡፡ ከዚያ በፊት አማራም ይሁን ኦሮሞ በጭራሽ መገንጠል የለበትም የሚል ፍጹም ስምምነት አለ፡፡  “እጣፈንታችን ጽዋ ተርታችን በአንድ ላይ በአንድ አገር ነው” የሚል ስለነበር የመገንጠል ሐሳብን ከአንድ ታሳሪ የሰሙት አኮረፉት አሉ፡፡ ከዚያ ይህ ሁኔታ በሌሎች ኦሮሞዎች ዘንድ ተሰማ፡፡ ሌሎቹ ኦሮሞዎች ኮሚቴ አዋቅረው ይህንን አንዱን ኦሮሞ ታሳሪ ገስጸው በኮሚቴው አማካይነት ሁሉንም ታሳሪ አማራዎች ይቅርታ ጠየቁ፡፡ ሐሳቡን ያነሳው አንድ ሰው፣ የሰሙትም በጣት የሚቆጠሩ ሆነው ሳለ ሁሉም ኦሮሞ ሁሉንም አማራ ይቅርታ ጠየቀ፡፡ ይኽ የተፈጸመው እንግዲህ በእስር ቤት ነው፡፡
ኦሮሞና አማራ በአንድነት ይዘምራሉ፡፡ ሁለቱም ተመሳሳይ ግጥሞችና መዝሙሮችን በአማርኛም በኦሮምኛም ያጠናሉ፤ ይዘምራሉ፡፡ ተለያይቶ የሚዘመርም ሆነ የሚጻፍ  ምንም ነገር የለም፡፡ እነዚህን ምሳሌዎች እንካችሁ፡፡
“እኔ ተበደልኩኝ አማራ ስለሆንኩ፤
“እኔ ተበደልኩኝ ኦሮሞ ስለሆንኩ፡፡”
 እየተባለ በአማርኛም በኦሮምኛም እኩል ይዘመራል፡፡
የትም ይሂዱ ኦሮማራነት አብሮ ነው፡፡ መንፈስ ሆኗል፡፡ የመግባባት፣ የመዋደድ፣ አንድ የመሆን መንፈስ፡፡ ልደታ የእስረኞች ማረፊያ አግዳሚ ወንበርን ተመልከቱ፡፡ ከጀርባቸው:-
“መሪያችን ዳውድና ዶ/ር ብርሃኑ ናቸው፡፡”
“ABO  እና ግ7 አሸባሪ አይደሉም፡፡”
“WBO and AG7 will win TPLF.”
[ABO  (Adda Biliissummaa Oromoo)- የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ፖለቲካዊ ክፍሉን ሲወክል WBO (Waraana Bilissummaa Oromoo) ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ ወታደራዊ ክፍሉን ይወክላል፡፡]
አንተ ትብስ አንተ ትብስ መባባል ባህል ሆኗል፡፡ ምግብ ሲመጣ፣ልብስ ሲመጣ ከራስ ይልቅ ሌላን ማስቀደም ከመንፈሳዊ ትእዛዝም የሚልቅ አስገዳጅነት አለው-በሽብር ተከሳሽ አማራና ኦሮሞ ዘንድ፡፡ በወልቃይት የአማራ ማንነት ጉዳይ የታሰሩት ሰዎች ሲፈቱ እንዳጋጣሚ እስረኛን ለመቀበል መኪና ይዘው የመጡት የወልቃይት ኮሚቴዎችን የሚቀበሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ በዚያን ዕለት አብረው የተፈቱ ኦሮሞ እስረኞች ስለነበሩ ባለመኪናዎቹ አስቀድመው ወደ የቤታቸው እንዲያደርሱ የተደረገው ኦሮሞ እስረኞችን እንጂ አማራዎቹን አልነበረም፡፡
በነገራችን ላይ በየእስር ቤቱ ምግብ ለእስረኛ በአብዝኃኛው የሚያመጣው እና የሚጠይቀው (ኦሮሞዎቹንም አማራዎቹንም) በቄሮ አስተባባሪነት የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው፡፡
#ገርባነት
የኦሮማራነት ነገር ከላይ ከተገለጸውም የሚያልፍበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡  እንደሚታወቀው ብዙዎቹ ክሶች የሚታዩት በ19ኛ እና በ4ኛ ወንጀል ችሎቶች መሆኑ ይታወቃል፡፡  የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በችሎት መድፈር መቅጣትን ልማድ አድርጎት ነበር፡፡
ይህ ችሎት በሽብር በተከሰሱ እስረኞች ዘንድ የተናቀ፣ ገለልተኛ አይደለም የሚባል፣የፖለቲካ ውሳኔ የሚሰጥበት እንጂ ፍትሕ ሊሰፍንበት እንደሚችል የሚያስብ እስረኛ የለም፡፡ በዚህ በተናቀ ችሎት ንቀቱን ለማሳየት የማይደፍር እስረኛ የለም፡፡ ያው ንቀታቸውን ለማሳየት ሲደፍሩ ችሎቱም በችሎት መድፈር ይቀጣቸዋል፡፡
ያንን ችሎት መናቅና መድፈር በሽብር ለተከሰሱት ጀግንነት ነው፡፡ ጀግና ያሰኛል በሌሎች ዘንድ፡፡ እንደውም ማእረግ ያስሰጠዋል፡፡ የገርባነት ማእረግ፡፡ የገርባ ማእረግ ታሪካዊ አመጣጥ እንዲህ ነው፡፡
እንደሚታወሰው አቶ በቀለ ገርባ ከአንድም ሁለት ጊዜ በችሎት መድፈር ተቀጥተው ነበር፡፡ የመጀመሪያውን የችሎት መድፈር ቅጣት ከተወሰነባቸው በኋላ ብዙ እስረኛ በአንድነት መዝሙር ማሰማት፣አንዱ በችሎት መድፈር ሲቀጣ ሌላውም አጋርነቱን ማሳየት እንደዘወትር ተግባር ቀጠለ፡፡ ከዚያ በችሎት መድፈር የሚቀጣ ሁሉ “ገርባ”  ሆነ ይባል ጀመር፡፡
አቶ በቀለ ገርባን በማክበር፣ በማሰብና በመዘከር የእሳቸውን የአባት ስም የጀግንነት መለያ ማእረግ ተደረገ፡፡ በርካታ የአማራም የኦሮሞም ወጣቶች “ገርባ” ሆነዋል፡፡ የገርባነት ማእረግ ከተሰጣቸው ውስጥ የሚከተሉት ሦስት ወጣቶች ይገኙበታል፡፡  እድሜያቸው ገና ከ17 ዓመት አልዘለለም፡፡  የጎንደር ልጆች ናቸው፡፡ኤሊያስ አደም፣ኢብራሂም አሊ እና አዲሱ አህመድ ይባላሉ፡፡
እነዚህ ልጆች የተከሰሱት በሽብር ወንጀል ነው፡፡ መነሻው “የአንድ ብሔር (የትግሬ) የበላይነት አለ ወይስ የለም?”  የሚል ሲሆን ልጆቹ “አለ” ይላሉ፡፡ ከዚያ ነገሩ ተጎትቶ ተጎትቶ ወደ ሽብር ድርጊት እና አሸባሪዎች ጋር እንዲገናኝ ተደርጎ በሽብር ተከሰሱ፡፡  ከዚያም ከፍተኛ ድብደባ ደርሶባቸው አሁንም ቂሊንጦ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወጣቶችም የገርባት ማእረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሦስት ፣ሦስት ወራት በችሎት መድፈር ወንጀል ስለተቀጡ፡፡
እና ምን ለማለት ነው? ኦሮማራነት እንዲሁ በፌስቡክ የተፈጠረ ወይም የተወለደ አይደለም፡፡ ጎንደር ላይ በ2008 ዓ.ም. “በቀለ ገርባ ይፈታ፣ የኦሮሞ ደም የእኛም ደም ነው”  ሲል ከዚያም ቄሮ በኦሮሚያ ክልል በአሳሪዎቹ ተንኳሽነት ኦሮሞና አማራን ለማጫረስ የሚያደርገውን ተንኮልና ሴራ በማፍረስ ለአማራ የሚሠጠው ጥበቃ በፌስቡክ የተጀመረ አይደለም፡፡ በእርግጥ ተጠናክሯል፡፡
 በጥቅሉ ደምቢዶሎም አርማጭሆ፣አርማጭሆም ደምቢዶሎ  ነው፡፡ አንድ በሽብር ተከስሶ የነበርን ሰው አግኝታችሁ ጠይቁት፡፡ እውነታው እንዲህ ነው፡፡
የለውጡ ሞተር ገጠር ላይ እንደሆነ ያኔ ይገባናል፡፡ እጅ የጠመዘዘው ኃይል ያለው ገጠር ነው፡፡ ለውጡ የመጣው ከገጠር ወደ ከተማ ነው፡፡ ኦሮማራን መንካት፣ኦሮማራን ማንቋሸሽ ምን ያህል እንደሚያስከፋ አጋየ አግማስን ወይም በቀለ ገርባን ጠይቁ፡፡ ሌላ ሌላ በሽብር የተከሰሰን ሰው ጠይቁ፡፡
ኦሮማራ ይለምልም!!
ማስታወሻ፡-
ይህንን ሁሉ ታሪክ ያጫወተኝ፣ የተረከልኝ ድርሳን ብርሃኔ ነው፡፡ እኔ አገጣጥሜ ብቻ ጻፍኩት፡፡ ሌላው የድርሳን ነው፡፡ ድርሳን ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በላይ ማዕከላዊና ቂሊንጦ ታስሯል፡፡ ከዚያ ከተፈታ በኋላ ወዲያውኑ ባህር ዳር ላይ ከታሠሩት 19ኙ የአማራ ፓርቲ አደራጆች አንዱ ነው፡፡ ድርሳን የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም መጽሐፍ ማለት ነው፡፡ ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ እሱም መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቢሏችሁ አንድ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ካወቅኩት ሳምንት አይሞላኝም፡፡ ግን ከስምንት መጽሐፍ በላይ አነበብኩ-ድርሳንን፡፡ ይንንም ማረጋገጥ ካስፈለገ አብረውት ታስረው የነበሩት እና አሁንም አብረው እየሰሩ ያሉት የአማራ ፓርቲ አደራጆች ይመስክሩ፡፡
Filed in: Amharic