>

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ወሰነ   

ፋና ብሮድካስቲንግ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዛሬ መደበኛ ስብሰባውን ያደረገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ወሰነ።
ምክር ቤቱ በስብሰባው የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ ገምግሟል።
አሁን ላይም በሀገሪቱ ስርዓት ሰፍኖ ሰላምና መረጋጋት በመመለሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ አስታውቀዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ እንዲፀድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኳል።
ረቂቅ የውሳኔ ሀሳቡ በምክር ቤቱ ሲፀድቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 23 2010 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት ለስድስት ወራት ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማፅደቁ ይታወሳል።
ምክር ቤቱ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሀ) መሰረት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ በምክር ቤቱ ያፀደቀው።
በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የተጋረጠውን ይህን አደጋ በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለመጠበቅ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት በማስፈለጉ ነበር የታወጀው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባው የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ አሁን ላይ በሀገሪቱ ስርዓት ሰፍኖ ሰላምና መረጋጋት በመመለሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ወስኗል።
Filed in: Amharic