>

የኦቦ በቀለ ገርባ ጉዳይ እና እነ "ያዙኝ-ልቀቁኝ" (ስዩም ተሾመ)

እኔን ጨምሮ በፍቃዱ ሃይሉ፣ አጥናፍ፣ ዳንኤል… ወዘተ በቀለ ገርባ ሲታሰር ጮኸናል፣ እንዲፈታ የተቻለንን ሁሉ አድርገናል፣ ፅፈናል፥ ተችተናል፥ ተሟግተናል፥… በእርግጥ የተለየ ላይሆን ይችላል፣ ነገር ግን፣ ብዙዎች በፍርሃት ቆፈን ተለጉመው በነበረበት ወቅት፣ ኦቦ በቀለን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጥረት አድርገናል፡፡ የሁላችንም ጥረት ተደምሮ የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱ፡፡ በተለይ በቀለ የተፈታ እለት በደስታ አቅሌን ስቼ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም ማዕከላዊ በነበርኩበት ወቅት ኦቦ በቀለ “እንግዳ ስለሚበዛበት መምጣት እንዳልቻለ ጠቅሶ” ልጁን #ቦንቱ_በቀለን ልኮ ጠይቆኛል፡፡ በእውነቱ ይሄ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም አቦ በቀለ ለእኔ ብቻ ሳይሆን በብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል በኣረዓያነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከልዩነት ይልቅ በአንድነት የሚያምን፣ ለብዙሃኑ መብትና ነፃነት የሚታገል፣ ከቀብሪዳህር እስከ ጎንደር ያሉ ሰዎች ከአንደበቱ የተስፋ ቃላትን የሚጠብቁ፣ ሥራና ምግባሩን ሚሊዮኖች በአንክሮ የሚከታተሉት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ስብዕና ያለው ግለሰብ በቴሌቪዥን ቀርቦ #እኛ_እና_እነሱ እያለ መናገር አይጠበቅበትም፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ በቀለን “ተሳስተሃል” ለማለት ከማንም የተሻለ ሞራል አለኝ፥ አለን፡፡ “በቄ አይ… የተናገርኩትን በተሳሳተ መንገድ ተርጉማችሁታል” ሲልም “እሺ ይሁን!” ብለን ተቀብለናል፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን፣ በቀለ ሲታሰር ጭራውን ቆልፎ ሲርመጠመጥ የነበረ፣ ከእስር ሲፈታ “እንኳን ለቤትህ አበቃህ” ለማለት ሲፈራ የነበረ ሁሉ ዛሬ ደርሶ “ያዙኝ ልቀቁኝ” ሲል ማየት ያስቃል፥ ያሳቅቃል፥ ያሳፍራል! ሰውዬው “አንተ ውለታ ቆጣሪ!” ቢለው ሌለኛው “አንተ ውለታ አስቆጣሪ!” አለው አሉ፡፡
Filed in: Amharic