>
5:31 pm - Tuesday November 13, 3945

ወያኔ ታላላቅ የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ኤፈርት ለማዞር ደባ ሸረበ! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ወያኔ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ እስከዛሬ “ፈጽሞ ወደግል ይዞታ አይዛወሩም!” ብሎ ከዓለም ባንክ (ቤተ ንዋይ) ጋር ሲወዛገብባቸው የነበሩ እንደ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኮሽን (ርሑቀ ግንኙነት) ፣ የመብራት ኃይል ተቋም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ የባሕር መጓጓዝ አገልግሎት ድርጅቶችን ከፊል ድርሻ እንዲሁም የባቡር (የሰደዴ)፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ (የመካነ ምግንባብ) የሆቴል (የቤተ እንግዳ) እና የተለያዩ ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን (በጋራ ድርሻ) ሽያጭ ወደ ግል ይዞታ እንዲተላለፉ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
 
እንደምገምተው የዚህ ሽያሽ ዓላማ፦
 
1ኛ. አገዛዙ የገጠመውን የውጭ ምንዛሬ ድርቅ ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ያስችለኛል ብሎ በማመኑ፡፡
 
2ኛ. ዋነኛው ዓላማ ይሄኛው ነው፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ማለትም ከዚህ ቀደም ከመንግሥት ይዞታነት ወደግል ይዞታነት እንዲተላለፉ የተደረጉ የመንግሥት ድርጅቶች ወደግል ይዞታነት በማስተላለፍ ስም በኤፈርት የወያኔ ሕገወጥ የንግድ ድርጅትና በወያኔ ሙሰኛ ባለሥልጣናት ባለቤትነት እንዲዛወሩ ወይም እንዲወሰዱ እንደተደረገው ሁሉ አሁንም ወደግል ይዞታነት ይተላለፋሉ የተባሉት ድርጅቶችንም ግዙፉ የወያኔ ሕገወጥ የንግድ ተቋም እና በሙስና የናጠጡ የወያኔ ባለሥልጣናት ባለቤትነት እንዲገቡ ለማድረግ ነው፡፡
 
ለነገሩ የማዛወሩ ሒደት ነጻና ፍትሐዊ ቢሆንም እንኳ የኤፈርትንና የሙሰኛ የወያኔ ባለሥልጣናትን ያህል አቅም ያለውና መፎካከር የሚችል ማንም የሀገር ውስጥ ባለሀብት ስለማይኖር ዞሮ ዞሮ ከነሱ አይወጣም፡፡ ወያኔ የእነኝህን ድርጅቶች ሽያጭ እስከዛሬ ያቆየውም ወደራሱ ለማዛወር እንዲችል አቅም እስኪገለባ ለመጠበቅ ነበር፡፡ አሁን የሚፈልገውን አቅም የገነባበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የሱን ያህል አቅም የገነባና ያለው ምንም ዓይነት ሀገር በቀል ድርጅትም ፈጽሞ የለም፡፡ ስለዚህ ለገበያ አቀረባቸው፡፡
 
ሊፎካከሩት ይችሉ የነበሩት የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ነበሩ ነገር ግን መፎካከር እንዳይችሉ ቅድሚያ ለሀገር ውስጥ ባለሀብት ብሎ ዘግቶባቸዋል፡፡ ቀጥሎ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ (ግዩራን) ነው ብሏል፡፡ ከሁለቱ የተረፈውን ነው የውጭ የመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች የሚፈቀደው ብሎ ሽያጩ ከሱ እንዳይወጣ ለማድረግም አመቻችቶታል፡፡ ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ አለ! ወያኔ እንዲህ የዋዛ መስሎሻል ምድረ ቂል ሁላ፡፡
 
የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄንን ዓይን ያወጣ ተወዳዳሪ የሌለው ዝርፊያ መከላከል የሚችለው ወያኔን ጠራርጎ ያስወገደ እንደሆነ ብቻና ብቻ ነው እንጅ ከዚህ ውጭ የወያኔ ሕገወጥ የንግድ ድርጅቶች በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ይሄ የቀደመውን ኢፍትሐዊ አሠራር ያስቀጠለው የዐቢይ የውሸቱ የለውጥ አሥተዳደር እስካለ ወይም እስከቀጠለ ጊዜ ድረስ ፈጽሞ ይሄንን ተወዳዳሪ የማይገኝለትን ዝርፊያ መከላከልና ማስቆም አይቻልም፡፡ 
 
ወያኔ ሥልጣን ለቀቀ ቢባል እንኳ በእነኝህ ሕገወጥ የንግድ ድርጅቶቹ በሕገወጥና ኢፍትሐዊ መንገድ ያካበተውን ሀብት ይዞ መውጣት እስከቻለና እነኝህን ሕገወጥ የንግድ ድርጅቶችም ማንቀሳቀስ እስከቻለ ጊዜ ድረስ ገዥ ሆኖ የሚቀጥለው እሱው ራሱ ነው፡፡ የትኛውም የዓለማችን ክፍል እንደምንመለከተው ሥልጣን ያለው ኢኮኖሚውን (ምጣኔ ሀብቱን) በተቆጣጠረው አካል እጅ ነው፡፡ ስለሆነም ወያኔ ኢኮኖሚውን ተቆጣጥሮ መቀጠል እስከቻለ ጊዜ ድረስ በእጅ አዙር የሚገዛው እሱ ራሱ ነው የሚሆነው፡፡ 
 
በመሆኑም ኢኮኖሚውን ሊበራላይዝድ (ምጣኔ ሀብቱን ነጻ) ከማድረግ በፊት ፖለቲካው ሊበራላይዝድ (እምነተ አሥተዳደሩ ነጻ) እና ተጠያቂነት የሰፈነበት ማድረጉ መቅደም አለበት፡፡ ይሄ መሆን ካልቻለ ወያኔ እንደቀለደብን ይኖራል እንጅ አንድም የሚለወጥ ነገር አይኖርም!!! ስለሆነም ከምንም ነገር መቅደም ያለበት ነገር እነኝህ በሕገወጥና ኢፍትሐዊ መንገድ በዝርፊያ ሀብት ሲያካብቱ የኖሩ ሕገወጥ የንግድ ድርጅቶች እንደ ሕገወጥነታቸው መወረስ ይኖርባቸዋል እንጅ በምንም ተአምር ቢሆን ነጻ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊፈቅድና ሊደራደር አይገባም፡፡
 
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic