በ1985 እና 1986 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔዊ ባንክና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኤርትራ ላይ የገንዘብ ጥያቄ አነሱ፡፡ ጉዳዩ በኤርትራ ባንኮች ውስጥ ቀልጦ የቀረውን የኢትዮጵያውያን ገንዘብ አካውንት የተመለከተና በኤርትራ ያሉ ፋብሪካዎች በደርግ ዘመን የተበደሩትን ብድር እንዲከፍሉ የሚጠይቅ ነበር፡፡ የነዚህን የኢትዮጵያ ተቋማት ጥያቄ ላነሱ የአመራር አባላት የተሰጣቸው መልስ “በዚህ በኤርትራ ጉዳይ ላይ የማይሆኑ ነገሮች እየጎረጎራችሁ የትምክህተኞች መሣሪያ እየሆናቸሁ ነው፤ ተጠንቀቁ!” የሚል ነበር፡፡ ኤርትራን በተመለከተ ሌሎች ጥቃቅን ጉዳዮችም እየተነሱ ልዩነት የፈጠሩ ሲሆን በሁሉ ጉዳዮች ላይ የሻዕብያን ፍላጎት በማስተናገድ ጥያቄ የሚያነሱትን በትምክህተኝነት ክስ በማስፈራራት ለሰባት ዓመታት ለቀጠለው የወያኔ ኢሕአዴግ ውድቅ ፖሊሲ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስና ቡድናቸው ተጠያቂ ነው፡፡”
“ወጥቼ አልወጣሁም” – ገጽ 101-102