>

ለ24 አመት በትግራይ ድብቅ እስር ቤት የሚገኙት ሊቅ (ጌታቸው ሺፈራው)

መምህር እንደስራቸው አግማሴ ይባላሉ። እውቅ የዜማ እና የቅኔ ምሁር ናቸው። በኢትዮጵያ ብቸኛዋ የድጓ ምስክር ቅድስት ቤተ ልሔም (ታች ጋይንት) ገብተው ድጓ አስመስከረው የድጓ መምህር ሆነው አገልግለዋል። በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በደብረ ታቦር አሁን ድረስ የእንደስራቸው ዜማ እየተባለ በተክሌ ዝማሜ ውስጥ እንደሚገኝ ይገለፃል። የመምህር እንደስራቸው የተክሌ ዜማ በ9 ካሴት ቀርፆ ተቀምጧል።
ጎንደርም በነበሩበት ጊዜ የሐዋሪያ ጳውሎስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ስራ አስኪያጅ፣የካህናት የታሪክ፣የሂሳብና የዜማ መምህር በመሆን ሰፊ አገልግሎት እንደሰጡ ታሪካቸው ያስረዳል። በዓለማዊውም ሥራቸው ደግሞ የኪ.ቤ.አ.ድ/የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት/ ዋና የአስተዳዳር ክፍል ሆነው አገልግለዋል፡፡
በሐምሌ 12/ 1986ዓ/ም 11፡35 አካባቢ ሲሰሩበት ከነበረው ኪቢአድ ቢሮ ከስራ ቆይተው ሲመለሱ የሻዕቢና የህወሓት ደሕንነቶች እንደሆኑ በተነገረላቸውና በትግርኛ ተናጋሪ ታጣቂዎች ታፍነው ተወሰዱ፡፡ህወሓት በወቅቱ ከእርሳቸው ጋር ሌሎች የታፈኑ ሰዎች የነበሩ ሲሆን በበጎንደር ራስ ግንብ ተብሎ ከሚጠራበት ቦታ ስር በሚገኘው ማሰቃያ ቦታ ከሌሎች ታሳሪዎች ጋር ስቃይ ተፈፅሞባቸዋል። በእስር ቤት የገጠማቸውን በአንድ ወቅት ለቤተሰቦቻቸው በሚስጥር በወጣ ደብዳቤ አሳውቀዋል።
እኚህ ሊቅ የታሰሩበት ምክንያትም ‹‹በወቅቱ የቆሰለ የደርግ አመራር አሳክመሃል ›› የሚል እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ መምህሩ ‹‹ ታዲያ ማሳከም ምንድነው ጥፋቱ? ሰው ካጠፋ ለምን በሕግ አይጠየቅም?›› ብለው ቢከራከሩም ይህ ህጋዊ ክርክር ምድር ቤት ከሚገኝ ጨለማ ክፍል ከመታሰር ብሎም ለ24 አመት ደብዛቸው ከመጥፋት አላዳናቸውም።
እምነትን እንደመሳርያ የሚጠቀሙት ገዥዎቹ በወቅቱ ‹‹ሥልጣን እንስጥህ፣ ህዝቡም ካህናቱም ይቀበሉኋል›› የሚል መደለያ ቢቀርብላቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። እንዲያውም መምህሩ ‹‹ኢትዮጵያን ለሚከፋፍል ቡድን ህብረት የለኝም፣ብትፈልጉ ግደሉኝ› የሚል አቋም በመያዛቸው ብዙ ስቃይ እንደተፈፀመባቸው ቤተሰቦቻቸው ይገልፃሉ
የሚያውቋቸው የእስር ቤቱ ሰዎች ማታ ማታ የታሰሩበትን ሰንሰለት እያላሉላቸው ለቤተሰብም በሚስጥር መረጃ ማድረስ ችለው ስለነበር ከታሰሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ሲገደሉ፣ ተራው መምህሩ ጋር ሲደርስ እንደቆመ ለቤተሰቦቻቸው አሳውቀው ነበር።
በወቅቱም ባለቤታቸውና ልጃቸው ለማስፈታት ጥረትም ቢያደርጉ ሳይሳካላቸው እንደቀረ ይነገራል። ጎንደር የሚገኝ ድብቅ እስር ቤት ውስጥ የተወሰነ እንደታሰሩ ለቤተሰብ የሚደርሰው መልዕክት ተቋረጠ። ከዛ ጊዜ በኋላ የት እንደገቡም ማወቅ አልተቻለም። ቤተሰቦቹ ባገኙት አጋጣሚ ጉዳዩን ቢያሳውቁም የሚሰማቸው የመንግስት አካል አላገኙም።
ሆኖም መምህሩ የት እንደገቡ ሳይታወቁ 24 አመት ካለፋቸው በኋላ በ2010 ዓም መጀመርያ ትግራይ ውስጥ የሚገኝ ድብቅ እስር ቤት ውስጥ በህይወት እንዳሉ ለቤተሰቦቻቸው መረጃ ደርሷቸዋል።
የመምህር እንደስራቸው ቤተሰቦች፣ በመምህርነትና ሊቅነታቸው የሚያውቋቸው ባለፉት 24 አመታት ጥያቄ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው አካል አላገኙም። በቅርቡ መምህሩ በህይወት መኖራቸው ሲሰማም ጥያቄያቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ጎንደር በሄዱበት ወቅት የመምህር እንደስራቸው ቤተሰቦች ጥያቄ ለማቅረብ ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን አጋጣሚውን ሳያገኙ ቀርተዋል።
መምህር እንደስራቸው ባለፉት 26 አመታት ስለ እውነት ስለቆሙ ብቻ ደብዛቸው ለጠፋው ንፁሃን ማሳያ፣ ለገዥዎቹ ወደር የለሽ ኢሰብአዊነት ደግሞ ምስክር ነው።
#FreeEndesrachewAgmasie 
#እንደስራቸውአድማሴይፈቱ
Filed in: Amharic