>

ኢ ት ዮ ጵ ያ ፡  አ ረ ን ጓ ዴ ! አረንጓዴ አፈር ...፣ አረንጓዴ ባንዲራ...፣ (አሰፋ ሀይሉ)

ኢ ት ዮ ጵ ያ  ፡  አ ረ ን ጓ ዴ  !

— አረንጓዴ አፈር …፣ አረንጓዴ ባንዲራ…፣ አረንጓዴ ፍቅር… ፣ አረንጓዴ ሰው…!  

አሰፋ ሀይሉ
“ጥቁር ሰው” በተሰኘው የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ አልበም ውስጥ ከተካተቱትን ዘፈኖች “ስለ ፍቅር” በተሰኘው ዜማ ውስጥ …
“አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ
ለምን ይሆን የራበው ሆዴ?”
የሚል ስንኝ ተቋጥሮ እናገኛለን። እና በወቅቱ ‹‹የቴዲ አፍሮ ‘ጥቁር ሰው’ እና ጥቂት የተዛቡ እውነቶች›› በሚል መሰል ርዕስ ትችታዊ መጣጥፍ ያቀረበ አንድ ጠያቂ፡- ‹‹ለመሆኑ ግን፣ የት አገር ነው አረንጓዴ አፈር ታይቶ የሚታወቀው?!›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ እርግጥ አባባሉ ከእውነት የራቀ ይመስላል፡፡
ግን ግን… እነዚህን የወሎ አፈር ማህፀን ውስጥ፣ የሸዋ ከርሰ-ምድር አብራክ ውስጥ ተሸሽገው… እንዲህ እንደ ባንዲራችን፣ እንደቀስተደመናችን፣ እንደ አንዳች አረንጓዴያዊ ልዩ ህብራችን… ከኢትዮጵያ አፈር ውስጥ እንዳሸለቡ… ከወሎ አፈር ሥር ሆነው… አረንጓዴ ብርሃናቸውን ለዓለም እየረጩ ሳለ… ግና … ‹‹የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው›› እንዲል ያገራችን ሰው… ሀገሩ ያለውን ሀብት ሳይጠቀምበት ቢራብ፣ ሀገሩ ወንዙ በፊቱ ሲወርድ እያየ ቢጠማ፣ ሀገሩ ባለጥበብ ሞልቶት ቢታረዝ፣ ሀገሩ በመሬት መራቆት፣ በእህል እጥረት፣ በኑሮ ፈተና ቢቸገር፣ የሀገራችን ህዝብ ከራሱ አልፎ በበረሃ ላይ ለተገነቡ የአረብ ሃገራት የሚበሉትን እያመረተ እየላከ እርሱ በጦም ቢያድር… ምንም እንደሌለው ህዝብ.. መሬቱ እንደተቃጠለበት ሀገር… በሌሎች ለሚበላው ስንዴ ቢረዳ፣ ዱቄት ቢመፀወት፣ ልብስ ቢዘከር… እውነት ጥፋቱ የማነው???
እና ታዲያ… እህ?! ምን እንበል?? አንገታችንን ወደላይ አቃንተን ቸሩን እዝጌራችንን… የሰጠኸን አፈር አረንጓዴ አልነበረም፣ አይደለም፣ አይሆንም… ብለን ልንሞግተው ይሆን … የቅድስቲቱን ምድራችንን አረንጓዴ አፈር ብቻ ሳይሆን አረንጓዴ ወርቅ አድርጎ የሰጠንን ታላቁን ድንቁን የኢትዮጵያችንን አምላክ…??!!! ወይስ … አንገታችንን ወደራሳችን ቀልሰን.. ራሳችንን ወቅሰን.. እንታረምና እንድንበትም.. እንነቃም ዘንድ ነው… ይህ ሁሉ አፈር አረንጓዴ ለብሶ… ዓይናችን ላይ የልምላሜ ብርሃናቱን የሚፈነጥቅ፣ የእኛኑ ጥበብ የሚጠባበቅ፣ እኛኑ የከበሩ ሀብታሞች የመሆናችንን ምስጢር ለዓለም ሊያውጅ.. በእዝጌሩ ኃይል የተቀመጠልን አንዳች አፈራዊ ተዓምራዊ ምስጢራት ይኖረው ይሆን ወይ?? ብለን እናስብ??!!
እንዴ! እነዚህ የከበሩ ክሪስታሎች እኮ.. ልክ በዓለማችን እንደከበሩት አብረቅራቂ የአልማዝ ማዕድናት… በቅዱስ መጽሐፉ እንደተጻፈ… እንዲሁ በእውን… እውነተኛ የግዮን ውብ ወርቆች መሆናችንን ለዓለም የሚመሰክሩ… ባለማችን እጅግ ብርቅዬ እና ተፈላጊ የሚባሉ… እጅግ ውድ ጌጣጌጦች የሚሠሩባቸው… ከአረንጓዴው አፈራችን ውስጥ ተዝቀው የሚወጡ… የከበሩ አረንጓዴያማ ኢትዮጵያዊ ብርሃናት ናቸው እኮ!!! ለዓለም ውበታችንን፣ ለገዛ ራሳችን ተስፋችንን የሰነቁ.. ያጎናፀፉ… በእዝጌሩ የተጻፉልን.. ውድ የአፈር ውስጥ ስጦታዎቻችን፣ ተፈጥሯዊ ውበታችንን ለህዋው ሁሉ በአረንጓዴ ብርሃናማ ቋንቋ እየፈነጠቁ እንዲናገሩ ከአምላካችን የተቸሩን… ውበታችንን ነጋሪ.. ድንቅ አረንጓዴ የተፈጥሮ ልሳኖቻችን ናቸው፡፡
እነዚህ በአረንጓዴው አፈራችን ውስጥ የሚገኙ .. ከወሎ አፈር ውስጥ እና ከሸዋ አፈር ውስጥ ተፈልቅቀው እየወጡ… ለዓለም ገበያ እየቀረቡ የዓለምን ባለፀጎች የሚያስጌጡ … ልዩ ተፈላጊነት ያላቸው…. የኢትዮጵያችን ድንቅ የኦፓል ማዕድናት… እንዲህ ተደርድረው ሲታዩ… አሁንስ…?? አሁንስ… እውነት እውነት… አፈራችን አረንጓዴ እንደሆነ… በቂ ምስክሮች አይሆኑም ይሆን??
እና ነገሩ ግና… እውነት ነውና… አርቲስቱ እንዲህ እያለ አረንጓዴያማውን የጥበብ ፋና  ይለኩስልናል..፡-
‹‹አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ
ለምን ይሆን የራበው ሆዴ?
ብራናው ይነበብ.. ተዘርግቶ በአትሮነሱ ላይ
የነ ፋሲለደስ.. የነ ተዋናይ
የት ጋር እንደሆን ይታይ.. የኛ ጥበብ መሰረቱ
የኋላው ከሌለ.. የለም የፊቱ
ሳይራመድ በታሪክ ምንጣፍ.. ሰው አይደርስም.. ከዛሬ ደጃፍ
አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ
ለምን ይሆን የራበው ሆዴ?››
በእርግጥ ይህ ሁሉ ሆኖ… ከልብ ካልተፋቀሩ.. ከልብ እጅ ለእጅ ካልተያያዙ… እነዚህ ሁሉ አረንጓዴ ብርሃኖቻችን… እንዲህ በጨለማ ውስጥ እንደምንመላለሰው እንዳሁኑ… ለዝንተ ዓለም ከዕይታችን ተሰውረው… ተስፋችንን አጨልመው እንደሚቀሩ.. ጥርጥር የለውም፡፡ መዳኛችን ፍቅር ነው፡፡ መድህናችን የወገን ፍቅር ነው፡፡ መነሻችን የሀገር ፍቅር ነው፡፡ መድረሻችን ኢትዮጵያዊ ፅናት ነው፣ ኢትዮጵያዊ ውበት ነው፣ ኢትዮጵያዊ ድንቅ የተፈጥሮ ሥጦታ ነው፡፡ እና በፍቅር የምንለኩሰው ለዚህ ነው…፡- ረዥሙን ጽልመታችንን ተገፍፎ…  የድነት ብርሃን፣ የድነት ጥበብ፣ የድነት ተስፋ… በሁላችን ላይ ይበራልን ዘንድ ነው፡፡ .. ያ በአፈራችን ውስጥ ያለንን.. የተጋረደብንን ትልቁን አረንጓዴያማ ህብራችንን ያበራልን፣ ያሳየን፣ ወደታላቅነታችንም ዋልታ ያመላክተን ዘንድ ነው፡፡ ያኔ ነው የብልጽግናችን እውነተኛ ጉዞ የሚጀምረው…፡፡ እውነተኛው የፍቅርና የብልጽግና ጉዞ – ወገንን ይዞ!!!
ታዲያ ቴዲ አፍሮ ‹‹ስለ ፍቅር›› በሚለው በዚሁ ዜማው.. በተካተቱት ስንኞች ውስጥ… እዚያው አረንጓዴ አፈር ይዘን እንዴት እንራብ? በሚል ከልብ በሚያነባ ዜማ የቀረበ ተጠየቅ ብቻ እኮ የማያበቃው ለዚሁ ይመስለኛል፡፡ ጥያቄውን ያጭርብንና… መፍትሄውን ግን ወደ ፍቅር ይመልሰዋል…፡፡ ወደራሱ..፣ ወደየራሳችን፣ ወደየ ሁላችን…. ሁላችንም እንዲሁ.. ወደየራሳችን.. የተጋረደብንን ፍቅራችንን… በትክክለኛ የልባችን ሥፍራ እንመልሰው ዘንድ… ያንኑ የፍቅር ጥያቄ እያነሳ.. እንዲህ ይለናል ደጋግሞ… ‹‹ስለ ፍቅር›› ዜማው ላይ፡-
‹‹ስለ ፍቅር ሲባል ስለ ፀብ ካወራን ተሳስተናል
አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል
አተናል እውነት ነው ተቸግረን ብዙ አይተናል
የመጣነው መንገድ ያሳዝናል
ፍቅር ይዞ እንዴት አይሄድም ሰው ወደፊት አይራመድም!
‹‹ቀስተደመና ነው የለኮስኩት ጥበብ የያዝኩት አርማ፣ 
አልጠላም ወድጄ የነፍሴ ላይ ፋኖስ እንዳይ ጨልማ…!
አንተ አብርሃም የኦሪት ስባት
የእነ እስማኤል የይሳቅ አባት
እንዳክሱም ራስ ቀርፀሀት ራሴን 
በፍቅር ጧፍ ለኩሳት ነፍሴን!
በል አትዛል ቀና ሁን ልቤ
የህልሜን ከንዓን እንዳይ ቀርቤ!
‹‹ሰው ለመውደድ.. ካልኩኝ ደከመኝ
ያኔ ገና.. ውስጤን አመመኝ!
አመመኝ አመመኝ.. እኔን አመመኝ!
ዛሬ ገና.. ውስጤን አመመኝ!
ያኔ ገና.. እኔን አመመኝ!›› 
እና ደግሞ… የከበረ ድንጋያችን ብቻ እኮ አይደለም አረንጓዴ፡፡ ትንሽ ዝናብ ካካፋ አረንጓዴ ሣር የለበሰ ትልቅ የእግር ኳስ ሜዳ የሚመስለው ያገራችን መስክስ…?? እሱስ… መሬቱ፣ አፈሩ፣ ሳር ቅጠሉ ሁሉ… አረንጓዴ ካልተባለ.. ምን ሊባል ነው? አረንጓዴ ቢባልስ.. ምኑ ነው ከእውነታው የራቀው? እኛስ ብንሆን አርቲስቱ እንደሚለው.. ተለያይተን፣ ደክመን፣ ፍቅር አጥተን እንጂ… እውነት መሬታችን አረንጓዴ፣ አፈራችን ለም ሳይሆን ቀርቶ መች ሆነና እንዲህ ገርጥተን በዓለም ፊት እንዲህ ለባህር ስደት ተጥፈን… ሀገር እንደሌለው ከሀገራችን ኮብልለን ወጥተን የቀረነው??! የሚል ሞጋች እውነት መልሶ ወደ ራሳችን ያፈጥብናል፡፡
እኛኮ ብዙ ጊዜ አረንጓዴ አብዮት እናስነሳለን ብለን አልመን.. የጠብመንጃ አብዮት አስነስተን ወዳልተፈለገና ወዳላሰብነው የታሪክ መንገድ አልፈን በሞት ሸለቆ የተማገድን አሳዛኝ አረንጓዴ ህዝቦች ነን፡፡ ‹‹አረንጓዴው ወርቅ!›› ከሚባለው ቡናችን.. ‹‹አረንጓዴው ወርቅ›› እስከሆነው አፈራችን.. ሀገራችን ለምለም፣ ምድራችን አረንጓዴ ናት፡፡ እኛ ልጆቿ አላውቅበት አልንና.. የረሃብ አውድማ… የስደት መነሻ አደረግናት እንጂ – አ ይ  ፡   ሀ ገ ር !?  እስቲ ልብ ይስጠን ማለት ነው… እንጂ ሁን ያለው ሁሉ መች ከመሆን ይቀራል?? አንድዬ የፍቅር ልብ፣ የጥበብ ልቦና፣ የማያረጅ ሁሉን የሚያሳይ ብርሃኑን ይስጠን እንጂ… ምድሪቱማ.. አረንጓዴ ነች፡፡ አ ረ ን ጓ ዴ  ፡  ነ ች   ፡  ኢ ት ዮ ጵ ያ ዬ ! ! !
በመጨረሻ አረንጓዴ አፈር ስለቀሰቀሰብኝ የቆየ አረንጓዴ ትውስታ አንስተን ብንሰነባበትስ?? በነገራችን ላይ በሐረር ከተማ ያደገ ሁሉ የሚያውቀው፣ ያለፈበትም ይመስለኛል ይህን ትውስታ፡፡ ሐረር.. ‹‹አራተኛ›› ተብሎ በሚታወቀው ሠፈር አካባቢ ባለ ገደል ዙሪያ… ወይም ከ‹‹ጁንየር›› ሃይስኩል አጥር በአንደኛው ገደላማ አቅጣጫ፣ አሊያም በ‹‹ቀይ መስቀል›› አጠገብ በሚያልፈው ወንዝ ዙሪያ ሁሉ…. የሚገኝ አረንጓዴ አፈር ነበር፡፡ እንዲያውም እርጉዝ ሴቶች ሁሉ ‹‹አረንጓዴው የሚያብርቀርቀው አፈር አማረን›› እያሉ ባሎቻቸውን መከራ አስበልተው እያስቆፈሩ በልዩ አምሮት የሚቀምሱት… አረንጓዴ አፈር ነው – ያ አፈር፡፡ ሲያዩት ያምራል፡፡ በቀላሉ ይላቁጣል፡፡ ፀሐይ ሲያብረቀርቅበት… በውስጡ የደቀቀ ወርቅ የተበተነበት አረንጓዴ ዱቄት ይመስላል፡፡ ጓሉ ደግሞ አቤት ሲያምር… !!! እና በቃ ተደሰቱ ያላቸው ልጆች ሁሉ… በቃ… ዕቃ-ዕቃ ይጫወቱበታል፤ ባለ ከለር (ባለ አረንጓዴ ዩኒፎርም) የጭቃ ሰው እየሠሩ፡፡
እኚያ ህጻናት ትውስ ሲሉህ… እኛን ከጭቃ ጠፍጥፎ ሠርቶ በለምለም ምድር ላይ ያሰፈረን የእዝጌሩ ጥበብ እየመራቸው ይሆን እኮ ነው የሚያሰኙህ፡፡ ህጻናቱ ኮስተር ብለው በፈጠራ ሥራቸው ላይ ተመስጠው ታያቸዋለህ… ፡- በአረንጓዴ ጭቃ አቡክተው… እጅ፣ እግር፣ ሆድ፣ አንገት ጭንቅላት ያለው የሰው አሻንጉሊት ይሰራሉ… እና.. ያልበሰሉ ሁለት አረንጓዴ የወፍ ቆሎዎችን ደግሞ… በየዓይኖቹ አቅጣጫ ይለጥፉበታል፡፡ እና ምን ዓይነት ሰው እንደሚመስል… እግዚአብሔር አያሳይህ ማለት ነው፡ አረንጓዴ ዓይኖች ያሉት፣ አከላተ አረንጓዴ ሰው፣ በአረንጓዴ አፈር ላይ… ሠርተው የሚቦርቁ.. ልምላሜ የታያቸው… ሕልመኛ ህጻናት!!! እንደህጻናቱ ያደርገን ዘንድ ተመኘሁ፡፡ እና ተሰናበትኩ፡፡ በፍቅር፡፡
አምላክ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በያሉበት ይባርክ፡፡ አረንጓዴይቱን ምድራችንን በጥበበ ብርሃን ይሙላልን፡፡ ኢትዮጵያችን ለዘለዓለም ትኑር፡፡ አሜን፡፡
የኢትዮጵያን የታወቁ የኦፓል ማዕድናት የያዙት ፎቶግራፎች (ለየባለቤቶቹ እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
1) በዓለም ገበያ ከታወቁ ቁጥራቸው ከ40 ከሚበልጡ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ የኦፓል ክሪስታል ዓይነቶች በጥቂቱ (‹‹Harvest Heart — odditiesoflife — The Strange Magnificent Beauty… — Jesss Falcioni saved to Spirituality››);
2) የወሎ ያልተቦረሸ ተፈጥሮአዊ ኦፓል ከነአፈሩ #1 (‹‹This is a natural opal geode specimen. This is a natural opal specimen from Welo, Ethiopia from Welo, Ethiopia Credit to Opalauctions.com – Katie Quinteros saved to Trippin’››);
3) የወሎ ተፈጥሮአዊ ኦፓል (አረንጓዴ ክሪስታል) ከነቅርፊቱ #2 (‹‹Opal (var. Crystal Fire Opal) from 570 km north of Addis Ababa, Wello (Wollo), Dalanta Plateau, Ethiopia – Carrie Garrot saved to Fossils, rocks and minerals››); እና
4) የሸዋ (የመዘዞ) ተፈጥሮአዊ ልዩ ባለህብር የኦፓል ማዕድን #3 (‹‹There are two type of Ethiopian opals one is the Chocolate type called Mezezo and the other is Welo, smaller rough has unlike Mezezo (Shewa) little or no matirix – Famous Mezezo rough cut by J.P. Gier – J.››)፡፡
Filed in: Amharic