>

የአማራ ብሔርተኝነት ትግል ከዚህ አስተሳሰብ ውጭ ከሆነ የአማራነት ጠላት እንጅ የአማራ አይደለም!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

ማሳሰቢያ! በጠለቀ አስተውሎት ይነበብ!!! 
ወገኖቸ እንነጋገር! ሌላው ቢቀር እውነት ላለውና በአመክንዮ ለተደገፈ ልዕልና ላለው ሐሳብ ለመገዛት የሞራል (የቅስም) ግዴታ እንዳለበት የማያምንና የማይቀበል ሰው በደንብ ተገልጦ ያልታየ ችግር ስላለበት ለምንም አይበቃምና ሊገለል ሊወገድ እንደሚገባ እንግባባ!!
አስቀድሜ አንድ ጥያቄ ላንሣላቹህና መልሳቹህን ለራሳቹህ እየመለሳቹህ ጽሑፉን አንብቡ፡፡ ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውጭ ያለን እምነት ተከታይ አማራ የአማራ ትግል ሊያካትተው ይገባል ወይስ አይገባም??? ነው ጥያቄው፡፡
መልሱን አስቀድሜ ልስጣቹህና ለምን? እንዴት? በሚል ተጠየቅ ወደ ትንታኔው እንሻገር፡፡ መልሱ አዎ ይገባል እንጅ! በሚገባ ነዋ! የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳ አማራነት የራሱ እምነት፣ ወግ፣ ባሕል፣ መለያ፣ ማንነት፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ትውፊት… ቢኖረውም አንድ ሰው አማራም ይሁን ሌላ በሰውነቱ የመሰለውን የፈለገውን እምነት የመከተል ከፈጣሪ የተሰጠው ተፈጥሯዊ መብትና ሙሉ ነጻነት ያለው በመሆኑ እና የነገዳችንን ነገዳዊ አንድነት ለመጠበቅ ሲባል መብቱን ማክበሩ የግድ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
“ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ውጭ የሆነውን አማራ የአማራ ትግል አያቅፍም! አይቀበልም!” ብንል ማንነትን ለማስጠበቅ ለሚደረግ ትግል ይህ አቋም ትክክል ቢሆንም ፖለቲካንም (እምነተ አሥተዳደርንም) ጨምሮ ለሚደረግ ትግል ግን ያልበሰለና አጥቂ አቋም (politically unwise and violent stand) ነው፡፡ በመሆኑም ልንከተለው አይገባም፡፡
ይሁን እንጅ ለኢትዮጵያ የለየለት የጠላትነት ስሜት ያላቸውን የዓረብን የቱርክን ተዋጊዎች አሰልፎ መላ ኢትዮጵያን ለ15 ዓመታት ወሮ በመያዝ እንዳለ በሀገሪቱ ያሉ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በሙሉ፣ ደኖችን አንድ የቆመ ዛፍ ለምልክት ቆሞ እንዳይቀር ባደረገ መልኩ ያቃጠለውን ያወደመውን የዘረፈውን የመዘበረውንና የዘረፈንህ ልክ የለሽ ሀብትና ቅርሷን ለዓረቦችና ቱርኮች ሰጥቶ ሀገሪቷን ላጣ ለነጣና ስር ለሰደደ ድህነት የዳረገውን ሕዝቧን ጨፍጭፎ የፈጀውን ዲያብሎስ ግራኝ አሕመድን ጀግናው አድርጎ የሚያስብ የእስልምና ተከታይና ዓረቦች በእምነት ስም እስልምና ውስጥ ያጨቁትን ለዓረብ ፖለቲካዊ ጥቅምና ለባሕል ወረራ ለሚዳርጉ መርሖዎች ተገዥ የሆነ የእስልምና ተከታይ አማራ እና፦
በሃይማኖት ሰባኪነት ሽፋን ወደ ሀገራችን ገብተው ለሽዎች ዓመታት ነጻነቷን ክብሯን ሉዓላዊነቷን ተብቃና አስከብራ የኖረችዋን ሀገራችንን በቅኝ ግዛት ለማስያዝና ሕዝቧንም በባርነት ቀንበር ለማስጠግረር፣ ማንነቷን፣ ወጓን ሥርዓቷን ባሕሏን እምነቷን፣ በሙሉ እሴቶቿን አስጥለውና አጥፍተው የራሳቸውን እንድንሸከም ለማድረግ ተግተው ሲሠሩ የነበሩትን፣ የሕዝባችንን አንድነት እና ጥንካሬ ለማዳከም ሸፍጥና ሴራ እየሸረቡ በዘር በሃይማኖት እየከፋፈሉ እርስበርሱ ያባሉ የነበሩ የአጋንንት ደቀመዛሙርት ሚስዮናውያንን የቅኝ ግዛት ሰላዮችን ጀግናው አድርጎ የሚያስብ የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንት ተከታይ እና በእምነት ስም የምዕራባውያኑ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ ጥቅሞችና የባሕል ወረራ ለታጨቀበት የካቶሊክና የፕሮቴስታንት እምነት ባሕል ሥርዓትና አስተሳሰብ ተገዥ የሆነ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ተከታይ አማራ የአማራ ጠላት እንጅ ወገን ሊሆን ፈጽሞ አይችልምና እንዲህ ዓይነት ሰዎችን የአማራ ትግል ፈጽሞ ሊያካትትም ሊቀበልም አይችልም አይገባምም!!! የአማራ ብሔርተኝነት ትግል እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ካካተተ የአማራ ማንነት ትግሉ የጨነገፈና ዓላማና ግቡ በውል የማይለይ ደመነፍሳዊ ትግል ነው የሚሆነው፡፡
የአማራ የማንነት ትግል በተዛባና ትክክለኛ ባልሆነ ግንዛቤ በተንኮል የተበረዘን እስልምናን ካቶሊክነትን ፕሮቴስታንትነትን ተቀብለው ግራኝ አሕመድንና ሚስዮናውያንን ጀግኖቻቸው አድርገው እያሰቡ የሚኖሩ አማሮችን ሊያካትት ሊቀበል አይገባም ብቻ ሳይሆን በአማራ ብሔርተኝነት ትግል ስም እንዲህ ዓይነት ወገኖችን አካቶ የሚንቀሳቀስ ደመነፍሳዊ ቡድን ካለ የአማራነት ህልውና ማንነት ጠላት ነውና ጦራችንን ሰብቀን ወገባችንን ታጥቀን እነኝህን ከአማራ ማንነት የጨነገፉ ጭንጋፎችን አጥብቀን የምንዋጋቸው ይሆናል!!!
እንዴት? ለምን? ምንማለት ነው? የሚለውን በዝርዝር እናያለን፡፡ ወገኖቸ በአማራ ትግል ላይ ብዙ መጥራት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የማየው ነገር ሁሉ ድብልቅልቅ ያለ በእጅጉ ማስተዋል የሚባል ነገር የተለየው፣ ስሜት ብቻ የሚጋልበው፣ የበሰለ ምሁራዊ ተዋስኦ የራቀው፣ ከአማራ ማንነት ጋር የተጣጣመ የጠራ ዓላማና ግብ የሌለውና በታሪካችን በጠላቶቻችን ለተደረጉ ፀረ አማራ ትግሎች እጅ የሰጠ፣ የተንበረከከ፣ ባዶ የምርኮኞችንና የባንዶችን ኳኳታና ጋጋታ ነው እያየሁ ያለሁት፡፡
ከዚህ ቀደም በአማራ ትግል ዓላማና ግብ ዙሪያ በተነተንኩባቸው ጽሑፎች ሌሎቹ ጠባብ ብሔርተኛ ቡድኖች ፀረ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መብቶች እንደሆኑት ሁሉ የአማራ ብሔርተኝነት ትግል እንደነሱ ሊታሰብ የማይገባበትንና የማይሆንበትን አቅጣጫ በመቀየስ፣ የአማራን የላቀ የሠለጠነ አስተሳሰብ ክብርና ማንነት በጠበቀ መልኩ ዘመናዊና የሠለጠነ ገዢ ዓለምአቀፍ መርሖዎችን የጠበቀ፣ ዘመኑን የዋጀ፣ ከሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መርሖዎች ጋር የተጣጣመ መሆን በሚችልበትና ብሔርተኛ አስተሳሰብ በተፈጥሮው ካለበት ፀረ ሰብአዊነትና እና ፀረ ዲሞክራሲያዊነት (መስፍነ ሕዝብነት) በሽታ ነጻ ሆኖ መሔድ የሚችልበትን መንገድ ያለ መሆኑን በመግለጽና መንገዱንም አበጅቸ ወይም ቀይሸ እነሆ ማለቴ በአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴና በኢትዮጵያ ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ንቁ ተሳታፊ የሆነ ሁሉ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡
አሁን ደግሞ ከወዲሁ አንድ መጥራት ያለበት አንገብጋቢ ጉዳይ በመግጠሙና የእኔን እጅ የሚጠብቅ መስሎ ስለተሰማኝ እንደፈረደብኝ ልገላልጠው በማሰብ ይሄንን ጽሑፍ ጽፌያለሁ፡፡ መገላለጡና ፍርጥርጥ አድርጎ ጉዳዩን ማየቱ ግድ ነውና፡፡ ትግላችን የአማራነት የሞት ሽረት ትግል በመሆኑ በዚህ ምክንያት ለጊዜው ይሉኝታን ቆልፌበታለሁ፡፡
ይህ ጉዳይ ጠርቶ መግባባት ላይ ካልተደረሰና ተሸፋፍኖ እንዲዘልቅ የምናደርግ የምንፈቅድ ከሆነ ለጠላት ስስ ብልት ሆኖ በማገልገል የሆነ ጊዜላይ ድንገት እንደፈንጅ ፈንድቶ ከባድ አደጋ ሊያደርስብን ይችላልና ነው የግድ የሆነው፡፡ አስቀድሜ ግን ላስቀይማቸው የምችላቸው ወገኖች ሊኖሩ ስለሚችሉ ተገቢ ባይሆንም እንኳ እነሱን ይቅርታ መጠየቅ እወዳለሁ! ይቅርታ የምጠይቀው ስለማጠፋ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይቅርታ የምጠይቃቸው ወገኖች እውነታውን መረዳት ካለመቻልና የምነግራቸውን እውነት በተለያየ ምክንያት መቀበል ካለመፈለግ ሊቀየሙኝ እንደሚችሉ ስለማውቅ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት አማራ በእነ ወያኔ እና ኦነግ ፀረ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሆነ ርዕዮተዓለም አስተሳሰብ ዓይነት ተደራጅቶ መታገል ለአማራ የማያስፈልበት ምክንያቱ ጠባብ ብሔርተኝነት ክብሩን ስለሚነካ፣ ከጥንት ጀምሮ የያዘውን ጠባብነትን የናቀና የተጸየፈ የሠለጠነ አስተሳሰብ ስለሚቃረንና ጠባብ ብሔርተኝነት በተፈጥሮው ፀረ ሰብአዊ መብትና ፀረ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለሆነ ነው፡፡
አማራ በማንነቱ ተደራጅቶ ለመታገል የሚገደድበት ምክንያት ማንነቱና ዘሩ ወንጀል ተደርጎበት የዘር ማጥፋትና ማጽዳት አዋጅ ታውጆበት በመላ ሀገሪቱ እየተመነጠረ የቆየና አሁንም ያለ በመሆኑ እና በሀገሪቱ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች ይሄንን ግፍ በጥቃቱ ዓይነትነት ወይም በዘር ማጥፋት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን በመግለጽ ማውገዝ መቃወም ባለመቻላቸው፡፡ እንኳን ሊያወግዙትና ሊቃወሙት ይቅርና ኮሽታ እንኳ እንዳልተፈጠረ ቆጥረው ጉዳየ ብለው ሊያዩ ባለመቻላቸው ባለመፍቀዳቸው በዚህ ምክንያት የራሱን ጉዳይ ራሱ ይዞ ህልውናውንና ማንነቱን ከጥፋት መታደግ ግድ ስላለው ነው፡፡
የአማራን ትግል ከሌሎቹ ብሔርተኛ ቡድኖች የሚለይባቸው ሦስት ዐበይት ነጥቦች አሉት፡፡ የሌሎቹ የትግል ምክንያቶችና ፍላጎቶች በራስ ቋንቋ የመጠቀም፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን (self determination) መብት እስከ መገንጠል ድረስ ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር (self administration) መብት  የማረጋገጥ ሲሆን አማራ ግን ምንም እንኳ አማራ አማሮች ባሉባቸው የትኛውም የሀገራችን ክፍል ራሱን በራሱ የማስተዳደርና በቋንቋቸው የመማር የመዳኘት የመጠቀም መብታቸው እንዲከበር የሚፈልግና ለዚህም የሚታገል ቢሆንም ከሌሎቹ የሚለይበት ምክንያቶች፦
1ኛ. የአማራ ብሔርተኝነት የየትኛውንም ብሔረሰብ አባላት በብሔረሰብ ወይም በነገድ ወይም በጎሳ ማንነታቸው ብቻ በጠላትነት ፈርጆ የማያጠቃ በመሆኑ፡፡
2ኛ. ለሀገር ህልውና አደጋ የሆነውን የ “…እስከ መገንጠል!” ፀረ ኢትዮጵያ የጠላትን አስተሳሰብና ዓላማን ያልተሸከመ በመሆኑና ባለማቀንቀኑ፡፡
3ኛ. አማራ በሌሎች ላይ ያልተፈጸመ ያልታወጀ ጥቃት ማለትም እንደሰው እንደዜጋ በሀገሩ የመኖር መብቱ ተነፍጎት ከሀገሪቱ እንዲጠፋ ሲደረግ የቆየ እና አሁንም እንዲጠፋ እየተደረገ ያለ ስለሆነ ይሄንን አረመኔያዊ ጥቃት ለመቀልበስ ትግሉ በወያኔና በሌሎች የጥፋት ኃይሎች የታወጀበትንና በሰፊው እየተፈጸመበት ያለውን የዘር ማጽዳትና ማጥፋት ጥቃትን ቀልብሶ እንደሰው በምድር ላይ እንደዜጋ በሀገሩ ላይ ለመኖር የሚያደርገው ህልውናን የመታደግና የማስቀጠል የህልውና ትግል በመሆኑ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ሁለተኛው ምክንያት የአማራ ብሔርተኝነትን ትግል እንደሌሎች ጠባብ ብሔርተኛ እንቅስቃሴዎች በጠባብነት እንዳይፈረጅ ያደርገዋል፡፡ አማራ ሀገሩ ያልሆነ የኢትዮጵያ ክፍል የለምና ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ ሊገነጥል አይችልምና የመገንጠል ጥያቄ የለበትም፡፡ ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ለእንግዳ ሊጠሰው የሚችለው መሬትም የለም፡፡ በመሆኑም እስከ መገንጠል እንደሚሉና እንደጠበቡ ብሔርተኛ እንቅስቃሴዎች ዓይነት አይደለም፡፡
ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ማለትም የታወጀበትን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ጥቃትን ለመከላከልና ለመቀልበስ የሚለው ምክንያት የፖለቲካዊ መብትን የማስጠበቅ ጉዳይ ባለመሆኑና ከዚያ በላይ ሰብአዊ ወይም የህልውና መሆኑ በማንነቱ የመደራጀቱን አግባብነትና የተደራጀውም እንደሌሎቹ አግባብ ላልሆነ ለጠባብ ብሔርተኝነት ጥቅም አለመሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ይህ ሦስተኛው ምክንያት ባይኖር አማራ በማንነቱ መደራጀትን ፈጽሞ አያስብ እንደነበረ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ይህ ምክንያት ባይኖር ቀሪዎቹ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ስለሆኑ አማራ በማንነቱ ለመደራጀት ባልተገደደና በማንነቱ መደራጀቱም አግባብ ያልሆነና ጠባብነት ሆኖ በተቆጠረበት ነበር፡፡ ነገር ግን ሦስተኛው ምክንያት አማራ በማንነቱ ተደራጅቶ የራሱን ጉዳይ እራሱ እንዲይዘው አስገድዷል፡፡ እራሱ ካልያዘው በስተቀር ሌሎችን በመወከል በውክልና ሊደረግ የሚችል ትግል ባለመሆኑ ነው፡፡
ስለሆነም የአማራ ትግል የሌሎቹ ብሔርተኛ ቡድኖች ትግል ለእሱ ቅንጦት የሆነበት ዓይነት ትግል ሳይሆን ትግሉ የህልውና ወይም ህልውናን የማቆየትን የማስቀጠልን የሚያህል አስገዳጅና የመጨረሻው አሳሳቢ አንገብጋቢ ሰብአዊነት የሚሰማው የሰው ፍጡር ሁሉ ሊያግዘው ሊደግፈው የሚገባ ትግል ነው፡፡ ስለሆነም ሌላ የተደበቀ ዓላማ ከሌለው በስተቀር ማሰብና ማገናዘብ የሚችል ጭንቅላት ያለው ሁሉ አማራ በማንነቱ የመደራጀቱን አግባብነት ያላንዳች ማቅማማት ይረዳል ይቀበላልም፡፡
መልካም! አሁን ከውጭ ወደውስጥ እንግባ፡፡ መሰንበቻውን አንድ ሲገርመኝ የቆየና አሁንም እንደገና አዲስ በተመሠረተው አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) አቋም አስተሳሰብ ምክንያት እየገረመኝ ያለ ጉዳይ አለ፡፡ እዚህም እዛም በአማራ ብሔርተኝነት ትግል ውስጥ እንንቀሳቀሳለን የሚሉ ወገኖች እራሳቸው እንደሚሉት ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ቢሆንም ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የአማራን ትግል ምንነት ጨርሰው ሳያውቁና ምኑም ሳይገባቸው እንደነበረ በተረዳሁ ጊዜ በእጅጉ ነው የተገረምኩ፡፡
ከስድስት ዓመታት በፊት ጀምሮ በጻፍኳቸውና ብዙ ሰው በሚያውቃቸው ቀስቃሽ ጽሑፎች የአማራ ብሔርተኝነት ትግል ግብና ዓላማ ምን እንደሆነ በተቻለኝ መጠን አሳማኝ በሆኑ አመክንዮዎች እያስደገፍኩ ለማስረዳት ጥረት ሳደርግ መቆየቴ ይታወቃል፡፡
እኔ ምክንያቱ ከመረዳት የአቅም ውስንነት ይሁን ወይም ደግሞ ከቁርጠኝነት ማነስና ፍላጎት ማጣት ይሁን ወይም ደግሞ የነጮችን ጥቅም በሚያስጠብቀው ርዕዮተዓለም በመማረክ ይሁን ወይም ደግሞ እንደ ያ ትውልድ በተሳሳተና በተዛባ ግንዛቤ ለራስ ማንነት ዝቅተኛ ግምት በመስጠት ይሁን በትክክል በየትኛው ምክንያት እንደሆነ አላውቅም በስንት ድካም መከራና ትግል በብዙ ቅስቀሳ የተቀሰቀሰው እያየሁት ያለው የአማራ ብሔርተኝነት ትግል ከተዘራው፣ ከተሰበከው፣ ከተቀሰቀሰው ጋር የማይጣጣም እንዲያውም የሚቃረን ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በዚህም በእጅጉ ማዘኔን ሳልገልጽ አላልፍም፡፡
ለመሆኑ የአማራ ብሔርተኝነት ትግል ማለት ምን ማለት ነው??? የሚለውን ጥያቄ ብንመልስ ነገሩን ግልጥ ያደርገዋልና ወደዚያው እንግባ፦
የአማራ ብሔርተኝነት ትግል ስንል አማራ የሚታገለው ህልውናውንና ማንነቱን ከጥፋት ለመታደግ ለማዳን የሚደረግ ትግል ነው የሚለው አጭሩ መልስ ነው፡፡ ለዚህ ዓላማ የሚታገልበት ምክንያት ህልውናውም ማንነቱም እንዲጠፋ እየተደረገ ስለሆነ ነው ብለናል፡፡
ብዙዎቹ “ህልውናን ከጥፋት የማዳን ትግል!” ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ሳይገባቸው የቀረ አይመስለኝም፡፡ “ማንነትን ከጥፋት የማዳን ትግል!” የሚለው ግን ምን ማለት እንደሆነ የገባው ሰው ስለመኖሩ በእጅጉ እጠራጠራለሁ፡፡ ስላልገባቸውም ነው እየተደነባበሩ የሚገኙት፡፡
የአማራ ማንነት ማለት አማራ እንደማኅበረሰብ ከጥንት ጀምሮ ያፈራቸው፣ የፈጠራቸው፣ ያበለጸጋቸው፣ ያጎለበታቸው፣ የደከመባቸው፣ የወጣ የወረደባቸው፣ ዋጋ መሥዋዕትነት የከፈለባቸው ባሕሉ፣ ወጉ፣ ትውፊቱ፣ ሥርዓቱ፣ ቋንቋው፣ አስተሳሰቡ፣ ሥነ ልቡናው፣ ታሪኩ፣ ቅርሱ፣ ሥልጣኔው፣ ሃይማኖቱ አጠቃላይ የማንነት እሴቶቹ ማለት ነው የአማራ ማንነት ማለት፡፡ ኬኔ ጋር ናቹህ???
እነኝህ ማንነቶቹም በወያኔ ብቻ ሳይሆን በምዕራቡ ዓለም ፍልስፍናና ርዕዮተ ዓለም እራሱን አደንቁሮ ሀገሪቱን ከስሯ ነቅሎ ከባሕሏ ከሥልጣኔዋ ከማንነቷ ወዘተረፈ ጋር አቆራርጦ ነቅሎ የትም ሳይተክላት ነቅሎ ብቻ በተዋት ባጠቃላዩ የያ ትውልድ ጭፍራ (ደርግ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ሸአቢያ፣ ኦነግ) የሀገሪቱን እሴቶች በሙሉ “የፊውዳል ነው!” እያሉ እንዲጠፋ ስላደረጉና አሁን ደግሞ ወያኔ ከአጋሮቹ ጋር ሆኖ እያጠፋ ያለ በመሆኑ እነኝህ እሴቶቻችንን መጠበቅ መታደግ የጠፉትን መመለስ ስላለብን ነው፡፡
ዛሬም የምዕራባውያኑ ሸፍጥ ሰለባ የሆነው የያ ትውልድ የጥፋት አስተሳሰብ ሰለባ ወይም ተከታይ የሆነው ይህ ትውልድ ምዕራባውያኑ የተሟላ ማንነት ባለው ጥንታዊ ማኅበረሰብ ስለሚቀኑ የቀኑበትን ጥንታዊ ማኅበረሰብ ማንነት ሰረገው ገብተው ማንነቱን ለማጥፋትና የራሳቸውን ለመጫን እንዲመቻቸው የሸረቡትን የሴኩላር (የዓለማዊ) የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓት በማንሣት “የአማራ ትግል መከተል ያለበት ሴኩላር (ዓለማዊ) የሆነ የአሥተዳደር ዘይቤን ነው!” በማለት እያወኩና የአማራን ሕዝብ በተሳሳተ አቅጣጫ ለመንዳት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይሄንን ስል ግን እንደ ዘውዳዊው ሥርዓት ሃይማኖታዊ የመንግሥት ሥርዓት መመለስ አለበት እያልኩ እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡
ከቅጥረኝነታቸው የተነሣ ይሄንን ዕኩይ አቅጣጫ የሚከተሉት አይደሉም የሚገርሙኝ ሸፍጡና የአማራ ብሔርተኝነት ትግል ምንነት ሳይገባቸው የሚያጫፍሩት እንጅ፡፡ ስለሴኩላር የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓትና ይህ የአሥተዳደር ሥርዓት አራምዳለሁ ስለሚለው የሃይማኖት እኩልነት የሚያጠያይቁ ኢፍትሐዊ ጉዳዮች ከዓመታት በፊት “ማተብ እናስወልቃለን? ሴኩላሪዝምስ ምንድን ነው?” በሚለው በዚህ ይዙን (ሊንኩን) ባስቀመጥኩላቹህ ጽሑፌ፦
እና “የሃይማኖት እኩልነት በዲሞክራሲ ሥርዓት እንዴትነት የፈጠረው ተቃርኖ በዚህ “መንግሥት”  ” በሚለው ጽሑፌ፦
በሰፊውና በጥልቀት ከአራትና አምስት ዓመታት በፊት የዳሰስኩት ጉዳይ ስለሆነ ጊዜ ለመቆጠብ ስል እዚህ ላይ አልደግመውም፡፡ ጽሑፎቹን እንድታነቧቸው ጋብዣቹህ ብቻ ልለፍ፡፡
እንግዲህ አማራ ህልውናውንና ማንነቱን ከጥፋት ለማዳን የሚታገል ከሆነ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ሃይማኖቱም ከማንነቱ መገለጫዎች አንዱና ዋነኛውም ነውና ሃይማኖቱን ከማንነቱ ነጥሎ ሊጥል አይገባም አይታሰብምም፡፡ እርግጥ ነው በዚህ ዘመን ያለው አማራ እንደጥንቱ ዘመን አማራ አንድ ሃይማኖትን አይደለም የሚከተለው፡፡ በየዘመኑ ተሰርቆ የተወሰደ በርካታ ወገን አለ፡፡ ግማሹ በግራኝ አሕመድ ሰይፍ ተገዶ የተወሰደ ነው፡፡ ግማሹ ደግሞ በሚሲዮናውያን የቅኝ ግዛት ሰላዮች ተሰብኮና ተደልሎ የተወሰደ ነው፡፡ ዛሬ ያለው የእስልምና፣ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ተከታዮች ቅድመ አያቶች በዚህ መንገድ ከራሳቸው ሃይማኖት ተማርከው የተወሰዱ ናቸው፡፡
እርግጥ ነው አሁን በዘመናችንም በተለያየ ምክንያት እየተወሰዱ ያሉም አሉ፡፡ ይሆነናል ካሉ የግልና ተፈጥሯዊ መብታቸው ነውና የመሰላቸውን መከተል ይችላሉ፡፡ መግቢያየ ላይ የጠቀስኩት ግዴታ ግን አለባቸው ለአማራ ማንነት እንታገላለን፣ አማራ ነንና አማራነት ይገደናል ካሉ እንደ አማራ ተወላጅነታቸው የቅድመ አያቶቻቸውን ወይም የአማራን ሃይማኖትንና ተያያዥ እሴቶችን የመጠበቅ የመንከባከብ ግዴታ እንዳለባቸው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ግለሰቦች የመሰላቸውን እምነት የመከተል መብት ያላቸው ቢሆንም አማራ ግን እንደ አንድ ማኅበረሰብ ቀደም ሲል የኦሪት እምነትን ከዚያም ኦሪት ወይም ብሉይ ኪዳን በተስፋ ትጠብቀው የነበረው መሲሕ (ክርስቶስ) ሲገለጥና ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ የብሉይ ኪዳንን ወይም የአይሁድነትን ዘመን ቋጭቶ አዲስ ኪዳንን ወይም ክርስትናን ሲመሠርት ክርስትናን ተቀብሎ ከዚህ ሃይማኖት ጋር የተዋሐደ የተሳሰረ ማንነት
ሊኖረው ችሏል፡፡
ይህ ሲባል ግን ሃይማኖትን ከእስራኤል ተቀብለናል ማለት እንዳልሆነ ልብ ይባል፡፡ ይልቁንም እኛ ሰጥተናቸዋል እንጅ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የምናነብ ከሆነ ለዚህ ሃይማኖት ከብሉይ ኪዳን ጀምረን ብዙ አበርክተናል፣ ብዙ ዋጋም ከፍለናል፡፡ ሁለት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አባቶችን ብቻ እናንሣ፡፡ መልከጼዴቅን አስቡ፡፡ መልከጼዴቅ ሕዝበ እስራኤልን ከእግዚአብሔር ጋራ
ያስተዋወቃቸውን አብርሃምን የባረከው የእግዚአብሔር ካህን ነው፡፡ እነሱ እግዚአብሔርን ሳያውቁት በፊት ገና እኛ ግን እግዚአብሔርን ከማወቅም አልፈን ካህንነት ደረጃ ደርሰን ነበር፡፡ የሊቀነቢያት ሙሴን አማች ዮቶርን ወይም ራጉኤልንም እንውሰድ የእስራኤሎችን ነቢይ መምህርና መስፍን ሙሴን ሕግንና የአሥተዳደር ጥበብን አስተምሮ ምስፍናውን በሚገባ እንዲወጣ ያስቻለ ካህን ነው፡፡
ይሄ ምን ማለት እንደሆነ ይገባናል ግን??? አማራ ማለት ክርስቲያን ማለት የሆነው እንዲሁ በአጋጣሚ አይደለም፡፡ ለዚህ ሃይማኖት ቅድመ ብሉይ ኪዳን ከስር መሠረት ጀምሮ ሲደክምበት የቆየበት ነገር በመሆኑ፣ ብዙ ያበረከተው ዋና ዋና አስተዋጽኦ በመኖሩ ነው አክሱማውያኑ የብሉይ ኪዳን ዘመን መቋጨቱን እንዳወቁና ክርስትናን እንደተቀበሉ ብሉይ ኪዳንን ትተው ሐዲስ ኪያንን ወይም ክርስትናን ብሔራዊ ሃይማኖት አድርገው ማወጃቸውን ተከትሎ ይሄን አዲስ ሃይማኖት ክርስትናን ብሔራዊ ሃይማኖት አድርገው ባወጁት በአክሱማውያኑ ማንነት ወይም በነገዱ መጠሪያ ስም አማራ ተብሎ ሊጠራ የቻለው፡፡ ዛሬ ድረስ በመላ ሀገራችን ከትግሬ እስከ ሞያሌ ከቤንሻንጉል እስከ አፋር በአራቱም ማዕዘን አማራ ማለት ክርስቲያን ማለት ሆኖ ሊገኝ የቻለው ለዚህ ነው፡፡
እና ታዲያ እኮ እንዴትና ለምንስ ተብሎ ነው ነገዳችን ከጥንት ጀምሮ ከሀገር አልፎ ለዓለም ያበረከተውን ይሄንን ዋጋ እንዲያጣ የሚመከረው??? ይሄንን ግዙፍ ማንነቱን፣ ክብሩን፣ ታሪኩን፣ ቅርሱን ጥሎ እርቃኑን እንዲቀር ነው ወይ የሚፈለገው??? ጠላቶቻችንስ ከዚህ የተለየ ምን አደረጉን??? ለሃይማኖታዊ ማንነትን ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ በእኛ የሚጀመርና አዲስ እኮ አይደለም በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ያለ አሠራርና ተሞክሮን ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሁለት ሀገሮችን ተሞክሮ ዕንይ፦
የእንግሊዝንና የእስራኤልን፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) እና ሴኩላር (ዓለማዊ) ነው፡፡ እንዲህ ቢሆንም መንግሥታቸው ሴኩላር መሆኑ የቀድሞው ዘውዳዊው ሥርዓታቸው ለነበረው ባሕል፣ ወግ፣ ሥርዓትና ሃይማኖት ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ እንዳያደርግ አላገደውም፡፡
የእስራኤልን መንግሥት ደግሞ ተመልከቱ፡፡ የእስራኤል መንግሥት ሴኩላር (ዓለማዊ) እና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መንግሥት ነው፡፡ እስራኤል ውስጥ እስራኤላዊ ወይም የአይሁድ ተወላጆች ሆነው በእምነታቸው ግን እስላምና ክርስቲያን የሆኑ አሉ፡፡ መብታቸው ተከብሮላቸው ይኖራሉ፡፡ የሕዝቡ ወይም የአይሁዶች የወል ማንነት
የሆነው እምነታቸው ግን አይሁድነት በመሆኑ የእስራኤላውያን እምነት ተብሎ መንግሥታቸው እውቅና ሰጥቶ የሚያከብረውና ጥበቃ የሚያደርግለት አይሁድነትን ነው፡፡
ከዚህም አልፎ በእስራኤል ሀገር የአይሁድ እምነት ተቋም የትምህርት፣ የባሕል፣ የቱሪዝም (የጉብኝት) የመሳሰሉት የሚኒስቴር (የዋና ሹም) መሥሪያ ቤቶችንም ይመራል ያሥተዳድራልም፡፡ የእስራኤል መንግሥት ይሄንን በማድረጉ ግን “ሴኩላር መንግሥት አይደለም!” አልተባለም፡፡ ሴኩላር አሥተዳደርን ከማንነታቸው ጋር እንዲስማማ አድርገው ነው የተጠቀሙበት፡፡ ማንነታቸው ነውና ይሄንን ለማንነታቸው የሚሰጡትን ዋጋና ክብር መለወጥ አይፈልጉም፡፡ እስላምና ክርስቲያን የሆኑ
እስራኤላውያንም እንኳ ቢሆኑ አይሁድነት የሕዝባቸው የወል ማንነትና ታሪካቸው በመሆኑ ይሄ አተያይ እንዲለወጥ አይፈልጉም፡፡
ሞኝና ወረቀት ያስያዙትን አይለቅም እንዲሉ የኞቹ ጅሎች ግን ሴኩላሪዝምን ከማንነታችን ጋር እንዲጣጣም አድርገን እንጠቀምበት ሳይሉ ሀገሪቱን ማንነት እንደሌላት ሀገር ቆጥረው እንደወረደ ተቀብለው ተግባራዊ ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ይሄ ፈጽሞ ሊሆን አይገባም፡፡ ማንነታችንን እንጠብቃለን፣ ለማንነታችን ዋጋ እንሰጣለን ካልን “አስላም ሆኛለሁና፣ ካቶሊክ ሆኛለሁና፣ ፕሮቴስታንት ሆኛለሁና፣ ምንትስ ሆኛለሁና አይመለከተኝም!” ሳንል በአማራነታችን የግድ የእንግሊዝንና የእስራኤላውያንን ዓይነት አኪያሔድ መከተልና ለነገድ የወል የማንነት መገለጫችን ለሆነችው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የተለየ ክብርና ዋጋ መስጠት ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ ይጠበቅብናል! ነው እያልኩ ያለሁት ግልጽ ነው??? ሀገሪቱ ካሏት የሥልጣኔ ፍሬዎች ከዘመን አቆጣጠር እስከ ሥነፈለክ (የሕዋ ምርምር)፣ ከከርሰ ምድርና ገጸምድር ሀብት ምርምር እስከ መድኃኒት ቅመማ፣ ከፊደል እስከ ምሕንድስና፣ ከዜማ እስከ ቅኔና ሥነጽሑፍ፣ ከፍልስፍና እስከ የሞራል (የቅስም) ሕግና የሠለጠነ ባሕል ወዘተረፈ. ተቆርሮ የማያልቀው የሀገሪቱ የሥልጣኔ ሀብት የተገኘው ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ነው፡፡ ይህች ቤተክርስቲያን ለዚህች ሀገር ምን ያልሆነችው አለ???
አውቃለሁ የእስልምና የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ተከታዮች ይሄ አመለካከት ሊመቻቸው እንደማይችል፡፡ ምክንያቱም ሲሰብኳቸው የራሳቸውን ማንነት ጠልተው እስላሞቹ የዓረብን፣ ካቶሊክና ፕሮቴስታንቶቹ የምዕራባውያንን ማንነት እንዲቀበሉ እንዲከተሉ አድርገው ነውና የሰበኳቸው ወይም የቀረጿቸው፡፡ ምን ማለቴ እንደሆነ ከዚህ በፊት “ኢትዮጵያዊያን እስላሞችና እጅግ አሳሳቢው የኢትዮጵያዊነት ስሜታቸው!” በሚል ርእስ በሰፊ ትንታኔ የጻፍኩትን ጽሑፍ ይሄንን ይዝ (ሊንክ) ከፍተው ያንብቡ፦
የእስልምና የካቶሊክና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ማወቅ ያለባቸው ነገር “ለአማራነታችን እንታገላለን ማንነታችንን እናስጠብቃለን!” የሚሉ ከሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ፊት መንሳት ወይም እንደባለጋራ መመልከት ፈጽሞ የማይችሉና የማይገባም መሆኑን ማወቅና ማመን ይኖርባቸዋል፡፡ ትግላችን ፖለቲካዊ ብቻ ቢሆንና ማንነትን ከጥፋት መታደግን የማይጨምር ቢሆን እንደተባለው የሴኩላሪዝምን ዘይቤ መከተሉ የግድ ይሆን በነበር፡፡
ይህ እንዳይሆን ግን ማንነት ብለን የማንነት ትግልንም ጨምረናል፡፡ ማንነት ካልን የትግሉ ማዕከል ማንነት ነው ማለት ነው፡፡ አለቀ ይሄው ነው፡፡ በመሆኑም በአማራ ብሔርተኝነት ትግል ስም የተደራጀ ሁሉ ይሄንን የእንግሊዝና የእስራኤልን አሠራር ወይም አስተሳሰብ የግድ መቀበል ይኖርበታል፡፡ አይ! የሚል ካለ ማንነታችንን በማጥፋት ላይ ላሉት ቅጥረኛና ባንዳ መሆኑ ይታወቅ!!! አዲስ የተመሠረተው አብን ይሄንን አሠራር መከተል ነበረበት፡፡
አንዳንድ ሰዎች አዲስ የተመሠረተውን አብንን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን) የመሠረቱ ሰዎች ድርጅቱን ሲመሠርቱ እኔን አለማካተታቸውን ሲያውቁ ተገርመው “እንዴት? እነኝህ አብን ነን ብለው ፊትለፊት የምናያቸው ሁሉም በአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ የምናውቃቸው አይደሉም! ካሉም አማራነትን አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው ማቀንቀን የጀመሩት፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም በግልጽ አማራ የሚባል ብሔረሰብ የለም! ይሉ የነበሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም የብአዴን ካድሬ የነበሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ለአማራ እንቆረቆራለን ብለው እንዲህ ዓይነት የአማራ ብሔርተኝነት ድርጅት ከመሠረቱ ለአማራ ብሔርተኝነት ትግል ስትቀሰቅስ የኖርከውና ርዕዮተዓለሙን በመቅረጽ መንገዱን ስትጠርግና ስታመቻች የኖርከውን አንተን ጥሎ የሚመሠረት የአማራ ብሔርተኝነት ድርጅት ምን ዓይነት ድርጅት ነው? የማን ብልጣብልጥ ጮሌዎች ናቸው እነሱ ለመሆኑ…….?” ሲሉ የጠየቁኝ ወገኖች አሉ፡፡
ስለእውነት ለመናገር መልሱን እኔም አላውቀውም፡፡ ስለማያውቁኝ ነው እንዳልል ሊቀመንበሩን ጨምሮ ብዙዎቹ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የፌስቡክ (የመጽሐፈ ገጽ) ጓደኞቸ ናቸው፡፡ ራሳቸው ናቸው ጓደኝነት ጠይቀውኝ የመጡት እንጅ እኔ ጠይቄ አይደለም ጓደኞች የሆነው፡፡ የምጠረጥረው ነገር ግን አለኝ፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ከእስር እንደተፈታሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተበረዘ ያልተከለሰ ብሔረሰብ እንደሌለ በሚተነትነው “ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከጥፋት የሚታደገው ብቸኛው መንገድ!” በሚል ርእስ በጻፍኩት ጽሑፌ ላይ ማዕከላዊ ከመርማሪዎች ጋር “ብሔርህን ተናገር? አልናገርም!” በሚል ውዝግብ “አንድ ብሔር የለኝም ከሁለት ብሔረሰብ የተገኘሁ ነኝ አንዱን ብቻ ነኝ ብየ ብል ሌላኛው በደሜ ውስጥ ያለ ማንነት ሆኖ እያለ እንደሌለ ማድረግ ስለሚሆንና ይሄም ስሕተት በመሆኑ አንዱን ብቻ ነኝ ማለት አልችልም……!” በሚል ከመርማሪዎቹ ጋር የተከራከርነውን ጽፌው ስለነበረና ለጓደኞቸም የጉራጌ ደም እንዳለብኝ ስለነገርኳቸውና አብንን ከመሠረቱት ውስጥም ይሄንን ስለሚያውቁ “አምሳሉ ንጹሕ አማራ አይደለም!” ብለው ትተውኝ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡
ነገር ግን እነሱስ እራሳቸው ማን ሆኑና??? እነዚህ የአብን መሥራቾች ብቻ ሳይሆኑ በአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ለምሳሌ ሙሉቀን ተስፋው፣ ምስጋናው አንዷለም በአንድ ጎናቸው ቅማንት እንደሆኑ እራሳቸው የተናገሩት ጉዳይ ነው፡፡ የአብን መሥራቾች ማንነትም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ከአገው፣ ከቅማንት፣ ከወይጦ ደም የሌለውና “በእናትም በአባትም እስከ ቅምቅማት ምንጅላቴ ምንም ያልተቀላቀለብኝ ንጹሕ አማራ ነኝ!” ማለት የሚችል ማን አለ??? ምናልባት ዘሩን አጣርቶ የማያውቅ ካልሆነ በስተቀር፡፡
እንዲያውም አማራ ነኝ ብሎ ከሚያስበው ምንም የአማራ ደም የሌለበት እንዳለም ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ሥፍራዎችን መጥቀስ አልፈልግም ነገር ግን በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ውስጥ በደማቸው ኦሮሞ ሆነው የዘመን እርዝማኔ ኦሮሞነታቸውን አስረስቷቸው አሁን ላይ እራሳቸውን አማራ አድርገው የሚቆጥሩ ወይም የሚያስቡ በርካታ ወገኖች አሉ፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው አንጋፋው የታሪክ ምሁር ተክለጻድቅ መኩሪያ እንደጻፉት ዐፄ ሱስኒዮስ ዐፄ ያዕቆብን ወግቶ በመግደል ሥልጣን ሲይዝ ዐፄ ያዕቆብን የወጋበት ሠራዊት ከወለጋ ያመጣው ፈረሰኛ የኦሮሞ ሠራዊት ነበር፡፡ ዐፄ ሱስኒዮስ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ይሄንን ሠራዊት ወደ ወለጋ አልመለሰውም፡፡ የተለያዩ የሰሜንና የደቡብ ጎንደር አብያተክርስቲያናትን ርስት እየወረሰ እንዲሠፍሩበት እንዳደረጋቸው ጽፈዋል፡
እነዚህ የኦሮሞ ተወላጆች በጊዜ ሒደት ኦሮሞነታቸው ተረሳቸው፡፡  በጎንደር አማርኛ ላይ አንዳንድ የኦሮምኛ ቃላት ሊኖሩ የቻሉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ዛሬ ላይ የእነኛ ተዋጊዎች ልጆች ኦሮሞነታቸውን አያውቁም፡፡ ይሄኔ እራሳቸውን እንደ ንጥር (ኦሪጅናል) ጎንደሬ ይቆጥሩም ይሆናል፡፡ እነሱ የሚያውቁት አማራነታቸውን ነውና፡፡ ምናልባት ከታሪክ አዋቂ ቤተሰብ የተወለዱቱ ይሄንን ያውቁ ይሆናል፡፡ ጎጃም ወሎ ሸዋ ከኦሮሞ ጋር ተጎራብተው እንደመኖራቸውና በታሪካዊ ኩነቶች ምክንያት ያለው ነገር ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ሌሎች ብሔረሰቦችም እንደዚያው፡፡ ለዝርዝሩ፦
በመሆኑም እንዲያው ጥርጣሬየን ለመናገር ያህል ነው እንጅ እራሳቸው ከቅማንት፣ ከአገው፣ ከወይጦና ከኦሮሞ የተወለዱ ሆነው እያለ “አምሳሉ በእናቱ ንጥር ጎንደሬና የባላባት የባለርስት ልጅ ቢሆንም በአባቱ የጉራጌ ደም አለበትና ንጹሕ አማራ አይደለም!” በሚል ምክንያት እኔን የተውኝ አይመስለኝም፡፡ ለነገሩ አብረን እንሥራ ብለው ጠይቀውኝ ቢሆን ኖሮም ከላይ በገለጽኩላቹህ የአማራ ብሔርተኝነት አቋሜ ምክንያት ከነሱ ጋር ለመሥራት አልፈልግም ነበረ፡፡ ምክንያቱም እነሱ ከአማራ ማንነት የራቁ፣ የአማራን ማንነት መጠበቅ፣ ማስቀጠል የማይፈልጉ ከአማራነት የጨነገፉ ናቸውና፡፡ እነሱም ይሄንን አቋሜን አውቀው ይመስለኛል ከዓረብና ከምዕራባውያን ቅጥረኛና ባሪያ ጋር ልሠራ እንደማልችል ተረድተው ጥያቄውን ያላቀረቡልኝ፡፡
በዚህ አጋጣሚ አማራ ህልውናው ብቻ ሳይሆን የተሟላ ማንነቱም የጠፋው ተመልሶ ያለው ተጠብቆ እንዲቀጥል ለትክክለኛው የአማራ ብሔርተኝነትና ማንነት መታገል የምትፈልጉ፣ የምትቀኑ፣ የምታስቡ ቆራጥ፣ ቆፍጣና፣ ጀግና፣ ባለአደራነት የሚሰማቹህ ወገኖች ጊዜ ሳናጠፋ እንገናኝ፣ እንምከር፣ እንደራጅ አደጋ ላይ ላለው ወገናችንና ማንነታችን እንድረስለት???
ጥሪያችን ግን የብአዴን ካድሬ (ወስዋሽ) የሆነን ወይም የነበረን ሰው ፈጽሞ አይመለከትም፡፡ አውቃለሁ አሁን አሁን በታችኛው ደረጃ ካሉ የብአዴን አባላት ለወገናቸው የመቆርቆር ዝንባሌ እያሳዩ ነው፡፡ እነኝህ ወገኖች መረጃ በማቀበልና በመሳሰሉት ነገሮች ባሉበት ሆነው ትግላችንን ሊረዱ ሊያግዙ ይችላሉ፡፡ ወገናዊ ግዴታም አለባቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ለትግሉ ደኅንነትና ተአማኒነት ሲባል ከይቅርታ ጋራ “እንቀላቀላቹህ?” የሚል ጥያቄ እንዳታነሡብን በአንክሮ ትጠየቃላቹህ፡፡
እናም የግድ መደራጀት ይኖርብናል ወገኖቸ፡፡ የአማራ ማንነትን በቅጡ የማያውቅ፣ የማይረዳ፣ ድግ የማይሰጠው፣ የማይከነክነው፣ የማይቆጨው፣ የማያንገበግበው፣ የትኛውም በአማራ ስም የተደራጀ ቡድን አማራን አይወክልም!!! የሚወክለውን ይፈልግ፡፡ “አማራነት! ማንነት!” እያሉም ጨርሶ የማያውቁትን ያልገባቸውንና ዋጋ ሊከፍሉለት፣ ሊጠብቁት የማይፈልጉትን ጉዳይ “አማራነት! ማንነት!” እያሉ በአንደበታቸው ባይጠቅሱ ደስ ይለኛል፡፡
በነገራችን ላይ አማራን አማራ የሚያሰኘው ማንነቱ ማለትም አስቀድሜ ከላይ የገለጽኳቸው እሴቶቹ እንደሆነ አበክሬ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ለጥቃት ያጋለጠውም ይሄ ማንነቱ ነው ሌላ አይደለም፡፡ አማራ ያለማንነቱ እንደማንኛውም የሰው ልጅ ሰው ነው፡፡ አማራ እንደማንኛውም የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ አይደለም እየተጠቃ ያለው፡፡ አማራ የአማራ ማንነት ባለቤት በመሆኑ ነው ቅናት ባንጨረጨራቸው ባዕዳንና የበታችነት ስሜት መድረሻ ባሳጣቸው ዜጎቻችን ለጥቃት ያጋለጠው፣ እንዲጠፋ እንዲፈልጉና እንዲዘምቱበትም ያደረጋቸው፡፡
እንጅ አማራ በሌላ እግዚአብሔር የተፈጠረ ሌላ የተለየ ፍጥረት ስለሆነ አይደለም፡፡ ስለሆነም ማንነታችን ነው አማራነታችን፡፡ ለዚህ ማንነታችን ፊታችንን አዙረን ለአማራ ማንነት ወይም ለአማራነት እንታገላለን ልንል አንችልም! ለአማራ ማንነት እንታገላለን ካልን ደግሞ ከቶውንም ከአማራ የማንነት እሴቶች አንዱን ጥለን አንዱን አንጠልጥለን ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም ምንነቱ ሳይገባቹህና ለአማራ የማንነት እሴቶች መከበርና መጠበቅ የጸና አቋም ሳትይዙ ወይም መያዝ ሳትፈልጉ ስንል ሰምታቹህ ብቻ “ለአማራ ህልውናና ማንነት እንታገላለን!” የምትሉ ሁሉ ለዚህ ቆራጥ ትግል ብቁና ዝግጁ አይደላቹህምና ቦታ ለቃቹህ ዞር ትሉልን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን!!!
በተለሳለሰ አቋም የአማራን ጥቅም አስጠብቃለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ ሲሠራ የቆየው የጥፋት ኃይሎች የጥፋት ሥራ የአማራን ጥቅም በተለሳለሰ አቋም ማስጠበቅ እንዳይቻል አድርጎ አወሳስቦታል፡፡ ስለሆነም የአማራ ብሔርተኝነት ትግል ቆፍጣና እና የቆረጠ ወይም ቀኝ አክራሪ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱም ምክንያታዊ ጽንፈኛ አቋም ሊይዝ ግድ ነው፡፡
ሕዝባችንን በዚህ መንፈስ ቃኝተን ካልተነሣን በስተቀር አንዷንም የአማራን ጥቅም ማስጠበቅ አንችልም! ይሄንን ያልተረዳና በተለሳለሰ አቋም የአማራን ጥቅም ማስጠበቅ የሚችል የሚመስለው የአማራ ብሔርተኝነት ትግል ነባራዊ እውነታዎችን ጨርሶ አልተገነዘበም፡፡ ሕዝባችንንም ለውድ የጊዜ የገንዘብ የጉልበት…. ኪሳራና ብክነት ይዳርጋልና አያስፈልግም!
ወያኔ ተጨባጭ ለውጥ ያደርጋል ተብሎ ሲጠበቅ በጥቃቅን ነገሮች እየደለለና እያዘናጋ ተጨማሪ ጊዜ የሚያገኝበትን ሁኔታ አመቻችቶ ተሻግሯል፡፡ የለውጥ ጥያቄውን ጫና ለማስተንፈስም “ቀጣዩን ምርጫ ነጻና ፍትሐዊ አደርጋለሁ! ሒደቱንም ከወዲሁ ጀምሬአለሁ!” እያለ ለተቃዋሚዎችና ለምዕራባውያኑ እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ ይህ የወያኔ ቃል እውነትም ይሁን ሐሰት ክፍተቱን በመጠቀም የወገናችንን ፖለቲካዊ ማኅበራዊና ሰብአዊ መብትና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ለማስከበር አጋጣሚውን ልንጠቀምበት ይገባል!!!
ምርጫው እንኳ ቢቀር ወገናችንን ለማታገል መደራጀቱ የግድ መሆን ያለበት ጉዳይ ነውና እባካቹህ እንደራጅ??? የእንደራጅ ጥያቄ በየጊዜው ሳቀርብ ቆይቻለሁ ይሄኛው ለስንተኛ ጊዜ መሆኑን ይሆን??? ተቀምጦ በታዛቢነት መመልከት ምንም የሚለውጠው ነገር የለም! እንዲያውም እየደረሰ ላለው ጥፋት ተባባሪነት ነው፡፡ በታሪክም ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ በመሆኑም እባካቹህ? እባካቹህ? እባካቹህ???…
ድል ለአማራ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic