>
5:13 pm - Sunday April 19, 2640

ኢህአዴጋችንና ኢህአዴጋቸው?! (ደረጄ ደስታ)

ህወሃት በየመግለጫው እሚላትና አሁንም የሰነቀራት “የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ሕወሓት” እሚላት አባባል ትገርመኛለች። ያቺኑ የአነጋገር ስሌት ይዘን ብንሄድ ለኢትዮጵያ ህዝብስ መሪ ድርጅቱ ማነው? “የኢትዮጵያ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ኢህአዴግ” እንላለን ወይስ….
ለመሆኑ ህወሓት ለትግራይ ህዝብ መሪ ድርጅቱ ከሆነ ኢህአዴግስ ለትግራይ ህዝብ ምኑ ሊሆን ነው? መቸም ድርጅት ሰው አይደለምና የልጅ ልጁ፣ አጎቱ አያቱ ወይም ከሌላው የተወለደ ምናምን እያልን አንተነትንም። ኦህዴድ እና ብአዴን የኦሮሞውና የአማራው መሪ ድርጅት ነን እያሉ ቀብጠውም ከሆነ አባባሉ እነሱንም ይጨምራል። ነገሩማ እንዲያውም አይናገረው እንጂ ኦህዴድ የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ ድርጅት ነኝ ማለት ሳይቃጣው የቀረ አይመስለኝም። አንዳንድ ኢትዮጵያውያንም ኦህዴዶችን “ኢትዮጵያን እሚያክል ትልቅ አገር ይዛችሁ እንደሌሎቹ አንድ ብሄር ውስጥ ብቻ ምን ያንደፋድፋችኋል? እስኪ ሰፋ በሉና ሁላችንም እንቀበላችሁ..” ሳይሏቸው የቀሩ አልመሰለኝም። ተፌዎቹ ወጣቶችም ይህ ሳይገባቸው አልቀረም። ታዲያ ባይሆንማ ኖሮ ለማ መገርሣ ሱስ ነው። አብይ አህመድ ህይወትና መቃብር ነው እያሉ ስለ ኢትዮጵያዊነት በየሄዱበት ምን ያስለፈልፋቸዋል። እንደ ህወሃቶቹ እዚያቹ መንደራቸው ውስጥ አይርመጠመጡም ነበር?
ያው መቸም ቂል የለምና ነገሩ ፖለቲካ መሆኑ ይገባናል። ፖለቲካን ደግሞ ብልህ ሲጫተው እንጂ ገልቱ ሲያንጎላጀው አይጥመንም። ምንም እንኳ “ህወሃትን ያየ ኦህዴድን ያመሰግናል” እንዳይሆንብን እየሰጋን መሆኑ ቢታወቅም፣ “ኢህአዴጋችንና ኢህአዴጋቸው” ከሚል ጨዋታ ሸርተት ብለን እየገባን መሆኑን አንስተውም፡፡
ይህ መሆኑን ወደን ሳይሆን ተገደን የገባንበት ነው። ምክንያቱም እምንደግፈው ተቃዋሚ ድርጅት ፈጥኖ አልደረሰልንም። ሊደርስ የበቀለውም ከስር ከስር በመቀንጠሱ፣ ፋፍቶ የወጣውም በየሤራው በመገንደሱ ተቃዋሚ አልወጣልንም። ስብርባሪያቸውን ገና ከየእስር ቤቱና ስደቱ ለቃቅመን ለመጠጋገን እየሞከርን ነው። ሲሰራብን በኖረው ብርቱ ሥራ እምንደግፈው እንዳይጠናከር፣ ራሳችንን ምን የረባ ተቃዋሚ አለ እያልን እንድንቅና እነሱን ብቻ እንድናደንቅ ሆን ተብሎ የግፍ ተንኮል ሲሰራብን መኖሩን አንስተውም። አሁን ግን ረፍዶም ቢሆን ነቃን። ፖለቲካ በጅምላና በችርቻሮ ምን እንደሆነ ገባን። ሲከፋፍሉን የኖሩትን እነሱን እየከፈልን ነጥለንና ነጣጥለን ማውጣቱን አወቅንበት። እኛ እንኳ ባንከፍላቸው ራሳቸውን ወደኛ ከፍለው የወጡትን ከድርጅት ህዝብ ይቅደም ያሉትን ተቀበልናቸው። እንኳን አገር ከህዝብም ህዝብ ይበልጣል እያሉ ሲነጣጥሉን የኖሩት ተንገዋለው ወጡ። እንደተባለው ድርጅት ቀምተናቸው ከሆነ፣ ነገ ደግሞ መርዘውና አስከፍተው የቀሙንንም ህዝብ በፍቅር ነጥቀን ከራሳችን ቀላቅለንና ተቀላቅለን የሞላች አገር እንሆናለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ተስፋች ይሳካ ዘንድ ግን “ኢህአዴጋችንና ኢህአዴጋቸውን” ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። ኢህአዴግን የህዝብ በማድረግና ህዝብን የኢህአዴግ ሎሌ በማድረግ መካከል ያለውን ግብግብ እንደ ዓለም ዋንጫው የብራዚል እና ጀርመን ጨዋታ ዳር ሆነን እምናየው መሆን አይገባውም። እኛ የሌላ ሳንሆን “የህዝብ ኢህአዴግ” ነን እሚሉ፣ ከድርጅት ህዝብን ያስቀደሙ አባላትም ካሉ፣ ማንነታቸውን ቀርበውና ገልጸው ሊያሳውቁን ይገባል። ካሁን በኋላ ኢህአዴግ ዝግ ስብሰባ እያደረገ ከመጋረጃው በስተጀርባ እሚሰራው ሥራ መኖር አይገባውም። ሲሆን ሲሆን እንደተባለው ስብሰባውን አንዳንዴም በቀጥታ ብናደምጠው። ካልሆነ ግን ህዝባዊ ኢህዴጎቻችን እንድንረዳችሁ ከፈለጋችሁ መረጃ ስጡን። ማን በምን ጉዳይ ላይ ምን አቋም እንዳለው በግልጽ አሳውቁን። አዲስ አበባ ላይ ተቀብሎ መቀሌ ላይ እንደሚሽረው፣ ወይም ራሱ ገርፎ ራሱ እንደሚጮኸው፣ ህዝብን ከህዝብ ራሱ እያጋጨ ያልተጻፈ እንደሚያነበው ህወሓት፣ ቫይረስ ያልሆኑትን ለይታችሁ ንገሩን። አንዱን ህዝብ በሌላው ላይ በማስነሳት፣ በስውር እጅ አመጽ ለኩሶ መሪ ለማሳጣት እሚደርገውን ሴራ ተባብረን እንድናከሽፍ ከፈለጋችሁ ሁሉንም ነገር አፍረጥርጣችሁ ንገሩን።
በድርጅት ሽፋን፣ በኢህአዴግነት ከለላ በፌደራሊዝምነት ጥላ፣ የሌብነት ዓላማቸውን ማስፈጸም እሚፈልጉትን አሳልፋችሁ ስጡን። በየመንገዱ እንደወጠረ ሽንት አስር ጊዜ አስቸኳይ ስብሰባ እሚጠሩትን እየሰማችሁ ከምትሰናከሉ የድርጅታችሁን ስብሰባ አጠራር ደንብና መመሪያ ምን እንደሚል ግለጹልን። መቸም ለስሙ ፓርላማ ይባላል እንጂ ቁልፍ ቁልፍ አገራዊ ጉዳዩን እምታዩት እናንተ በመሆናችሁ ፓርላማ ሁናችኋልና የፓርቲ ምስጢር ምናምን እያላችሁ አትጃጃሉ። ቀድሞውንም ቢሆን እፍኝና ጎተራ የመሰረቱት ህብረት እሚመስለው ድርጅታችሁ በአስተሳሰብም በቁጥርም ትንሽ ከሆኑ ሰዎች ጋር ያለሚዛን ተደምሮ የተቋቋመ መሆኑ ግልጽ ሆኗል። ለነገሩማ እንኳን አገር ተጨምሮላችሁ እዚያም ድርጅታችሁ ውስጥ ቢሆን ብዙ ነበራችሁ። በሉ ወደፊት የራሳችንን ሰዎች ስለመምረጥ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ስለማስፋት፣ ህገመንግስቱን ስለማሻሻል ጠንካራ ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን ስለመገንባት በወቅቱ እንነጋራለን። አሁን ግን ተበልታችሁ እንዳታስበሉን፣ ያለፈው አልፏልና ለነሱም ኢህአዴጋቸውን ለኛም ኢህአዴጋችንን ስጡን!!!
Filed in: Amharic