>

ምነዉ ጃኪን የበላዉ ጅብ አልጮህ አለ? (ሃራ አብዲ)

ምነዉ ጃኪን የበላዉ ጅብ አልጮህ አለ?

«ልቤ ይኖራል እንጂ እንደ ተከፋ፤ ፈጽሞ እኔ አልቆርጥም ባንቺ ተስፋ» 

ምን ጃኪ ብቻ! ወንዲ ማክ የት ነዉ?

ሃራ አብዲ

ስዩም ተሾመ እንዴት በኦሮምኛ ችሎታዉ ብቻ ተመዘነ? እረ እንዴት ነዉ ጎበዝ??

 ማንን አንስቼ ማንን ልተዉ??

ፈረንጆች the rat on a treadmills የምትል አባባል አለቻቸዉ። እንግዲህ ትሬድ ሚሉ (ኤክሰርሳይስ መስሪያ ማሽኑ) ላይ የወጣች አይጥ ትንፋሽ እስኪያጥራት ከመሮጥ በቀር ለመዉረድ ብልሃቱ የላትም። ይህ የጊዜን መፍጠንና የሰዎችን ከወቅቱ ሁኔታ ጋርም ሆነ ከግል ህይወት ጥድፊያ ጋር የሚያደርጉትን ግብግብ ለማሳየት የሚጠቀሙባት አባባል ነች።

በሀገራችንም ያለዉ የለዉጥ ሁኔታ እንዲሁ catch up ለማድረግ እያቃተን ይመስላል። በአንዱ ሁኔታ ላይ የተዘገበዉን ሳናጣጥም ሌላ ትኩስ መረጃ ይደርሰናል። ስለዚህ ዛሬ እንደ እድር ወጥ የተለያዩ ነገሮችን ባንድ ማእድ ማቅረብ ግድ ብሎኛል።

 ጃኪ ጎሲ

ትግሪኛ ባደባባይ መናገር የፋራና የ ወያኔነት መገለጫ በነበረባቸዉ በእነዚያ የኢትዮጵያ የጭለማ ዘመናት፤ ጥቂት ባለራእዮች ያንጎራጉሩበት ነበር። ከእነዚህ ባለ ራእይ የሙዚቃ ባለሙያዎች መካከል ጃኪ ጎሲ አንዱና ከዋነኞቹም መካከል ነዉ።

«ፊያሜታ ፤ ባይኔ እስከማይሽ፣ ሰላም ያቆይሽ»

ባለፈዉ ሳምንት እሁድ ከሜሊኒየም አዳራሽ የተላለፈዉን የቀጥታ ስርጭት ስከታተል የተሰማኝ ደስታ  ወደር -አልባ ነዉ ብል አላጋነንኩም።ሙዚቀኞቻችን በቀደመዉ የወጣትነት ስራዎቻቸዉ በትዝታ ወደሁዋላ ሲመልሱን (እነ አረጋኸኝ) የቅርብ ጊዜዎቹ ደግሞ ( እነ ሃጫሉ) ለህሊና መገዛት፣ ሰዉ የመሆን አኩሪ ገድል መሆኑን ደጋግመዉ ያሰመሩበት ቀን ነበር።

«ሀቲ  ኬኛ ቶኮ ማልቱ  አዳን ኑባሴ »ብሎ አሊ ቢራ ሲያስገመግም,,, የፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አይኖች ዉሃማ ሆነዉ ታይተዉኛል። ተሳስቼ ይሆን? ይህ ብቻም ሳይሆን »ኢሱ» በእዉነት አማርኛና ኦሮምኛ ሙዚቃ እንደናፈቀዉ ፊቱ ላይ ይነበብ ነበር። ለምን አይናፍቀዉ? የኤርትራ መሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ እኮ ነዉ!!

እነ ንዋይም እንደ ደርግ ጊዜ የእናቶች ኪነት ከመድረክ ላይ የወረዱት በጠቅላይ ሚኒስትራችን የ« ደህና ሁኑ» እጅ ማዉለብለብ ተጠርገዉ ነበር። በዚህ አላማቸዉም። ማን ከእንደዚያ ያለ የሰላም፤ የፍቅርና የናፍቆት መድረክ ላይ በቀላሉ መዉረድ ይፈልጋል?

«ናይ ዘላለም እዩ ፍቕርና፤ ሎሚም ካብ ቀደምና» ሲል በአይቆረቁረዉ ድምጹ ልባችንን የማረከዉ ጃኪ ባለዉለታችን ነዉ።የትግራይ ነጻ አውጭዎች ወሽመጣችንን በቆረጡበትና «ኢትዮጵያ እንዴት እነዚህን እርጉማን ፈጠረች በማለት ቁዋንቁዋዉን ጭምር እንድንጠየፍ በተገደድንበት ጊዜ እንኩዋን ለጃኪ ጎሲ «ፊያሜታ» ጆሮ ነበረኝ።

መቼም የሀገራችን ነገር እንደ ጉዋያ ለቃሚ የፊት የፊቱን ነዉና፤ ጃኪን የበላዉ ጅብ ምነዉ አልጮህ አለ አስብሎኛል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለእርቅ ሲበቁ ጃኪ ጎሲ (የመድረክ ስሙ ወይም ቁልምጫዉ ሊሆን ይችላል)ወፍራም ቡልኮ የሚያሸልም ስራዉ መወደስ መቻል ነበረበት።

የድል አጥቢያ አርበኞች ጥንት እንደሞሉት ሁሉ ፤ዛሬም ሞልተዉ እየፈሰሱ ነዉ። እግረ-መንገዴን ሃጫሉ ላይ አፋቸዉን ለማላቀቅ ትንሽም ያልከበዳቸዉ ስም-አልቦዎችን ነገር ሳላነሳ ማለፍ አልሆነልኝም። ለመሆኑ እነዚህ ሃሳብ እንደገንዘብ የሚቸግራቸዉ simpletons; ሓጫሉ አርቲስታዊና አክትቪስታዊ ተልእኮዉን በብቃት ለመወጣት የነሱን እርዳታ የሚፈልግ ይመስላቸዋል? ያን ጊዜ የኦሮሞ ወጣት አራት ኪሎ ግባ ብሎ የዘፈነዉ እንዴት በናሺናል ቲቪ ይተላለፋል ብሎ ዘርአይ አስገዶም አጥን እንደያዛት በግ የአግድም ሲንቀጠቀጥ፤ በፍርሀት ሲርድ የነበረ ሁሉ ይሆናል አሁን ከየጎሬዉ ወጥቶ ሃጫሉን የሚተቸዉ። የቴዲም ነገር~~~ብዙ ተብሎበታልና ልለፈዉ።

ስዩም ተሾመ ስራዉቹ ና የኦሮምኛዉ  መመዘኛ፤ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ!

ለዚህ ለዉጥ መምጣት እስራትና ድብደባን ጨምሮ ብዙ ዋጋ የከፈሉ አክቲቪስቶችና የሰብአዊ መብት ተሙዋጋቾች እንደ አሮጌ ቁና ወደጎን እየተገፉ ከወያኔ ጋር ተለጥፈዉ ህዝባችንን መከራ ሲያበሉ የነበሩ ሰዎች የለዉጡ አስተናባሪ (Ushers) ሆነዉ መታየት ልብ ያጥወለዉላል። ለዚህ ትልቅ ምሳሌ አድርጌ የማቀርበዉ ስዩም ተሾመን ነዉ። ስዩም ኦሮምኛ በደንብ አትችልም ተብሎ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሊደርጉት በታሰበዉ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንዳልተጋበዘ ያስነበበዉን አይቼ በአግራሞት ተሞልቻለሁ። ጎበዝ እንዴት ነዉ ነገሩ??

ስዩም ትህትና ገዝቶት፣ አስር መምህራን ቢጋበዙ እሱ ላይጋበዝ ቢችል ተገቢ እንደሆነ ሃሳቡን በግልጽ አስቀምጦአል።

በእኔ እምነት ግን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አምስት ምሁራን እንኩዋን ቢሰበስቡ ስዩም ተሾመ አንዱ መሆን አለበት። አለቀ።

ስዩም በተደጋጋሚ በወያኔዎች የታሰረዉ፤ የተገረፈዉና የበዛ ስቃይ የተቀበለዉ ከቁዋንቁዋ  ጋር ቀጥታ ግንኙነት አልነበረዉም። ቢሆን ኖሮ ኦሮምኛ በደንብ ባለመቻሉ ለወያኔ ስጋት መሆኑ ይቀንስ ነበር፤ ድብደባና እንግልቱም በዚያዉ መጠን። በመላእክትም ልሳን ሆነ በወፍ ቁዋንቁዋ ቢናገር የወያኔን የዘር መድልኦ እስከተቃወመ ድረስ ዋጋ ከመክፈል አይድንም ነበር። እንዴት ነዉ ነዉ ታዲያ፤ ያሁኑ መስፈርት? ለመሆኑ ስብሰባዉ የኢትዮጵያን ህገ-መንግስት በቁቤ ለመጻፍ ነዉ እንዴ?

ያ ሁሉ ወደ አራት ሺህ የሚጠጋ ምሁር ኦሮምኛ አይችል ምን ሊበጀዉ ነዉ??

ይህ መቼም የጠቅላይ ሚኒስትራችንን ስራ ጥላሸት ለመቀባት የወያኔ አሽከሮች የሚያደርጉት ነገር ነዉ እንጂ ከአብይ ጋር ምንም ንክኪ እንደሌለዉ አምናለሁ። ይህ ለዉጥ ስር እንዲሰድ ከተፈለገ፤ ሙያና ሞያተኛዉ፤ ትግሉና ታጋዩ ይገናኙ።

በ«እንደመር» ሰበብ እባቦቹ እየተደመሩ እንዳይነድፉን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያሻል, ይህን እያየን አይደለም።

በስዩም ላይ የደረሰዉ መገፋት በሌሎችም ላይ በአስፈሪ ሁኔታ እየደረሰ ነዉና በቅርቡ እመለስበታለሁ። ይህ ለብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ሞራል ከማሰብም ያለፈ ነዉ። የመጣዉን ለዉጥ ዋጋ የከፈሉበት ጀግኖች ተጠንቅቀዉ እንዲገፉበት እድል ካልተሰጣቸዉ ምድረ እበላ-ባይ ገብቶ ሲፈተፍት ድሉ ባፍጢሙ እንዳይቆም ለመከላከልም ጭምር ነዉ ።

ሥዩሜ!! ጅግንነትህ በእዉቀትና በምክንያታዊነት የተማገረ ስለሆነ ጽና!! ብዙዎች ብእርህንና ደህንነትህን ይፈልጉታል። እናት ኢትዮጵያም አብዝታ ትፈልግሃለች!!

ወደ አርቲስቶቻችን  ስመለስ ፤ ጃኪስ ታዲያ፤ ስራዎቹን እንዲያቀርብ ፤ፊያሜታን እንዲጫወት ተጋብዞ ነበር?

ወንዲ ማክ «ወይ ነይልኝ»ን እንዲያንቆረቁር ጥሪ ደርሶታል? (ስለአማራና ኦሮሞ ግንኙነት ነዉ የተጫወተዉ የሚሉ አሉ።

ወንዲ ስለማንም ይጫወት ለህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማሻሻል አስደናቂ አስተዋጽኦ አድርጎአል።

እስቲ የምታዉቁትን አቀብሉን። ቸር ይግጠመን። እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ህዝብዋን ይባርክ።

Filed in: Amharic