>
5:13 pm - Thursday April 19, 6068

የነፃነት አርበኛ: ታላቁ እስክንድር ነጋ! (መስከረም አበራ)

የነፃነት አርበኛ: ታላቁ እስክንድር ነጋ!

መስከረም አበራ

ሰው እንዳደገበት የህይወት ዘውግ ማንነቱ ይቃኛል፡፡ በልስላሴ ያደጉ የባለጠጋ ልጆች በአብዛኛው ለስላሳውን መንገድ እንጅ ሌላውን አይመርጡም፡፡ በተቃራኒው ደሃ አደጎቹም ቢሆኑ ለፍተው ጥረው የህይወትን መንገድ ለማለሳለስ መድከማቸው ሰዋዊ ደምብ ነው፡፡ መነሻው ምንም ሆነ ምን መድረሻውን ለስጋዊ ህይወቱ ምቹ ለማድረግ መትጋቱ የአዳም ዘር አንዱ ተመሳስሎሽ ነው፡፡ ሆኖም የስብዕናቸው ውቅር እንዲህ በቀላሉ ለመረዳት የሚያስቸግር ሰዎችም አሉ፡፡ እንዴት ቢያድጉ፣እንዴት ያለ ንባብ ቢያነቡ፣እንደ ምን ጠልቀው ቢያስቡ እንዲህ ያለውን ረቂቅ ማንነት ታደሉ የሚያሰኙኝ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡ እስክንድር ነጋ ከነዚህ ጥቂት አስገራሚዎቼ አንዱ ነው! እስክንድር ህይወትን ለስላሳ አድርጎ የአዘቦት ኑሮ ለመኖር ቢፈልግ ኖሮ ከደህና በመወለዱ ለዚሁ ቀድሞ መንገድ የተጠረገለት ሰው ነበር፡፡ ሆኖም እስክንድር ህይወትን በአዘቦት እይታ የማያይ በመሆኑ ብዙዎቻችን የምናይበትን የድሎት መነፀር አሽቀንጠሮ ጣለ፡፡የብቻውን ድሎት ሳይሆን የብዙሃኑን ፍዳ ለመቋደስ ትልቅ ነፍሱ የነገረችውን ሰንቆ አስቸጋሪውን ብቻ ሳይሆን አስፈሪውን ፅዋ መረጠ፡፡

የእስክንድር ነጋ ነፍስ በብዙ ጌጦች የተዋበች ነች፡፡ ትህትናው ሲባል እውቀቱ፤ እውቀቱ ሲባል ቆራጥነቱ፤ ይህ ሲባል ብሶት እየቆጠረ ጥርስ የማያፋጭ የይቅርታ ሰው መሆኑ ይገርመኛል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ብዙዎቻችን ትልቅ ቦታ የምንሰጠውን ስጋዊ ምቾት ችላ ማለቱ ድንቅ ነው፡፡ ሳር ቅጠሉ ስደት በሚያልምበት ዘመን የሰው ወርቅ እንደማያደምቅ አውቆ ለስደት ያለንን አመለካከት የቀየረ ሰው ነው እስክንድር፡፡ በነገራችን ላይ ለእስክንድር መሰደድ የመኖር አለመኖር ጥያቄም ነበር፡፡ እዚሁ ሃገሩ ላይ ሆኖ የሚሆነውን ለመቀበል ሲቆርጥ ከማንም በላይ ህይወቱ አደጋ ላይ የነበረች ሰው ነው፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ አለመሰደድን ከብረት የጠነከረ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ እስከመጨረሻው መፅናት እስክንድርነትን ይጠይቃል፡፡ በዋነኝነት የሚገርመኝ የእስክንድር ልዩነት ይህ ነው፡፡ ላመኑበት መኖር ሁልጊዜም የማይገኝ ቢሆንም እንደ እስክንድር ላመኑበት እስከ መሞት ድረስ መጨከን ግን ሌልኛ ነው! ረቂቅ ነው! ዛሬ ላየነው የለውጥ ጭላንጭል እስክንድር ነጋ የከፈለው ዋጋ ውድ፣ረቂቅ እና ብዙ ገፅ ያለው ነው፡፡

እስክንድር የሚዲያ ነፃነት ፅኑ አርበኛ ነው፡፡ራሱን መሃለኛ አድርጎ ማውራት የማይወድ አዋቂ፣እዩኝ እዩኝ የማይል፣ራሱን ተራ ማድረግ የሚወድ የሃሳብ ሰው፣ ትዕቢት የማይነካካው ትሁት ስለሆነ እንጂ ቢተረክ ብዙ ገድል የሰራ ሰው ነው፡፡ አጥንቱ እስኪሰበር ተቀጥቅጧል፡፡ “አጥንቴን ተሰብሬላችሁ” ብሎ ግን ውለታ አያስቆጥርም፡፡ ይህን ግፍ በሰው ጎትጓችነት ቢያወራ እንኳን ይቅርታውን አስቀድሞ፣ ሌሎች ደግሞ ከዚህ የበለጠ የህይወት ዋጋ እንደከፈሉ አጥብቆ ተናግሮ፣ የእሱ እና የሙያ አጋሮቹ መስዕዋትነት የተከፈለው ዲሞክራሲ ለሚባል ውድ ነገር ስለሆነ ወደዛው እስኪደረስ ሁሉም መታገል እንዳለበት ለማስመር እንጅ የራሱን ገድል ለማውራት አይደለም፡፡

እስክንድር በጣም ብዙ ከሚገርሙኝ ማንነቶቹ አንዱ ይህ በነፃው ፕሬስ ብዙ ያልተለመደ ለሙያ አጋሮች እውቅና የመስጠት ቅንነቱ ነው፡፡ የእስክንድር መልካምነት እውቅና ከመስጠት አልፎ ሽልማቶቹን ለማጋራትም ይሞክረዋል፡፡ እስርቤት በነበረበት ጊዜ አንድ ቀን ሞልቶልኝ ልጠይቀው ሄጄ ይህንኑ አስተውያለሁ፡፡ እንዲህ ያለ ማንነት በነፃው ፕሬስ ባህል አጋጥሞኝ ስለማያውቅ ገርሞኝ ነው ያየሁት፡፡ የሄድኩት እሱ በደምብ ከሚያውቃቸው ሁለት ሰዎች ጋር ነበር፡፡ ስሙ ተጠርቶ ሲመጣ ፀሃያማ ፈገግታው የእስረኛ አይመስልም፡፡

እኛ የሄድንበት ሰሞን ባለቤቱ እና ልጁ ባህርማዶ የሄዱ ሰሞን ነበር፡፡ ይህ ለእሱ ቀላል ፈተና እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ “እስኬ ለምን ሰርኬን እንድትሄድ አደረክ? አንተ እዚህ ማን አለህ? ልክ አላደረክም!” አለ አብሮኝ የነበረው ጠያቂ፡፡ “አይ አይ ለእኔ የሚሻለኝ ይሄ ነው፡፡ ናፍቆት እዚህ ሲመጣ የሚሰማው ስሜት ጥሩ አይደለም፣በማንም ላይ ቂም እንዲያዝ አልፈልግም እና መሄዱ ይሻላል” አለውና የእሱ የግል ወሬ ላይ ያተኮረ መስሎት አጀንዳ ቀየረ፡፡ ስለጤናችን አጥብቆ ጠየቀ፡፡ እኔን ስለማያውቀኝ ፊቱ ላይ ትንሽ ግርታ ያየው ወዳጄ “እሷ ካልጠየኩት ብላ ነው የመጣችው:: አንተ ባታውቃትም እሷ ታውቅሃለች” ብሎ ስሜን እና ከእሱ ጋር የሚያገናኘኝ የመሰለውን አንዳንድ ማንነቶቸን ሊያስተዋውቅ ሞከረ፡፡ “ጥሩ ነው! እኛ ምናልባት ስራ ሰራን ከተባለ እንደ እሷ ያሉ ተተኪዎችን “Inspire” አድርገን ስለሃገራቸው እንዲያነቡ እንዲፀፉ ማድረግ ከቻልን ነው” አለ፡፡ “አይ እስኬ አንተማ በከተማዋ አራት ማዕዘን ሃውልት ሊሰራልህ የሚገባ ሰው ነህኮ!” ሲለው “አይ እኔኮ የተለየ ነገር አላደረኩም፤ ከሃገር ውጭም ሃገር ውስጥም ብዙ ጓደኞች ስላሉኝ ነው ሽልማት የበዛው፤ እንደው የተወሰነ ደግሞ ለሌሎች ታሳሪዎች ቢሰጥ ጥሩ ነበር፤ እነሱም ብዙ ዋጋ ከፍለዋል…. “ይላል፡፡

እንደታዘብኩት እሱን ማዕከል አድርጎ የሚወራ የጎበዝነህ ገድል ብዙ ምቾት አይሰጠውም፤ወሬውን ቶሎ ያስቀይርና ስለሌሎች ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች ተመሳሳይ አበርክቶ ያወራል፤ ለእሱ የሆነው በዝቶ ይሰማዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ለሌሎች ባልደረቦች እውቅና እና ምስጋና መስጠት በግሉ ፕሬስ በኩል አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ እስክንድር ሰውነቱም ጋዜጠኝነቱም ለየት ይላል! የማወቅ እና የአስተዳደገ መልካምነት መለያ የሆነውን ትህትና ተሸክሟል፡፡ እንደ ህፃን ልጅ ያለ ቅንነቱን ለማየት ከአስር ደቂቃ በላይ አይፈጅም፡፡ በአንፃሩ በራሱ እስከ መጨከን ድረስ ላመነበት ይፀናል፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያው ከማውቃቸው ሁሉ ገዝፎ ይታየኛል፡፡በማንኛውም ደረጃ ቢያቀርቡት የሚያኮራ መረዳት አለው፡፡ እውቀቱ የወለደው ትንታኔው እንደ ትንቢት ይቃጣዋል፡፡

እስክንድር ዛፍ ሲጠፋ አድባር የሆነ እምባጮ አይደለም፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ እኔ ነኝ ካለ ተንታኝ ጋር ቢሰለፍ የሚያኮራ መረዳት ያለው ሰው ነው፡፡ ለውይይት ይሁን ለመፃፍ ሲቀመጥ ቁንፅል ነገር ይዞ አይደለም፡፡ ይልቅስ ስለሚጽፍ የሚናገረው ነገር በደንብ ያውቃል፡፡ ክርክሩን በዓለም ጠርዝ የትኛውም ቦታ ላይ ከተከናወነ ፖለቲካዊም ሆነ ታሪካዊ ሁነት ጋር እያሰናሰለ ያስረዳል፡፡ የንባቡን ስፋት በፅሁፎቹ ውስጥ ማየት ይቻላል፡፡ አንብቦ የሚፅፍ እየጠፋ ባለበት ሃገር እስክንድር ለምልክት የቆመ ይመስላል፡፡ሆኖም እኔነት በእርሱ ዘንድ የለም፡፡ ሃሳቡን ሲያስረዳ በአውቃለሁ ባይነት ትዕቢት አይደለም፤በማራኪ ትህትና እንጅ!

እስክንድር ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ መብት መከበር ቃላት የማይወክሉት መስዕዋትነት የከፈለ ሰው ነው፡፡ሰውነቱ ደቆ ፣ቤተሰቡን በትኖ ፣ወልዶ ዕለቱኑ መሳም አለመቻልን ያህል ህመም ጥርሱን ነክሶ ችሏል፡፡ ለእስክንድር ጋዜጠኝነት ሰንደል ማስቲካ እንደመሸጥ ያለ ኪስ የማድለቢያ የችርቻሮ ስራ አይደለም፡፡ በኪሳራ ሳይቀር ጋዜጣ ሲያሳትም እንደኖረ የሚያውቁት ሁሉ የሚናገሩት ነው፡፡ እስክንድር በታሰረ ሰዓት በሆነ አጋጣሚ ያገኘሁት ጋዜጣ አዟሪ ለእስክንድር ገንዘብ ምንም እንዳልሆነ፣ ለጋዜጣ አዟሪዎች የነበረው ክብር እና ያልሰሩበትን እስከ መስጠት እና ለእርሱ የሚገባውን ሁሉ ለእነሱ እስከመተው በደረሰ ደግነት እንደሚያውቁት አጫውቶኛል፡፡ እስክንድር የሚያወራውን ሆኖ የሚያሳይ እንጅ በአደባባይ ሌላ በጓዳ ሌላ የሆነ ግብዝ አይደለም፡፡የሰላማዊ ትግል ሃዋርያ ነው፡፡ እሱኑ በየደረሰበት ይሰብካል፡፡ እየሞተ መታገልን የሚመርጥ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እስክንድር ይገርማል -ነግረውት የማያልቅ ግዙፍ!

በጣም የሚገርመው ደግሞ የተሸከመውን መከራ ከምንም የማይቆጥር በሁሉም ስፍራ አንድ አይነት አቋም ያለው ሰው ነው፡፡ እስርቤት ያገኘሁት ጊዜ ለአንድ ሰዓት ያክል ስለ ሰላማዊ ትግል ማስታወሻ ይዘው የሚማሩበት ቁም-ነገር አጫውቶናል፡፡ እያጫወተን እያለ አንድ ስርዓት የሌለው አይነት እስረኛ እላዩላይ የመውጣት ያህል ተጠግቶት የሚነግረንን ሁሉ ያጠነጥናል፡፡ ሰላይ መሆኑ ነው፡፡ ስጋት የገባው ወዳጄ እስክንድር ንግግሩን እንዲገታ በምልክት ያሳየዋል፡፡ እስክንድር እስከዛሬ የሚገርመኝን መልስ ሰጠ “ተወው እኔ ያልኩትን ሳይጨምር ሳይቀንስ ፅፎ ካመጣ እኔ መናገሬን እፈርምለታለሁ”አለ:: ሳላስበው አይኔን አፍጥጨ አየሁት፡፡ ምን አይነት ሰው ነው? ገረመኝ!

ከኢህአዴግ ጋር የማይታረቀው ማንነቱ ይህ ነው፡፡ መከራ የማያስጎነብሰው፤የብረት ጉልበት አንሶ የሚታየው ደፋር! የሆነበት ሁሉ የማይሰብረው ከነፍሱ ታላቅነት፣ ከህልሙ ግዝፈት ፣ከፍላጎቱ ርቀት የተነሳ ይመስለኛል፡፡በማይመጥናቸው ወንበር ላይ ቁጢት ያሉ ገዥዎች ደግሞ ይህ አይገባቸውምና ሰላማዊው፣ጨዋው፣ትሁቱ እስክንድር ለነሱ ሞገደኛ ሽብርተኛ ነው፡፡ ቀንድ እንዳለው አውሬ ይፈሩታል፡፡ ከአእምሯቸው በላይ የሆነው ግንዛቤው የሆነ ተዓምር ፈጥሮ ከስልጣናቸው እንዳይመነግላቸው ይሰጋሉ፡፡

በእርግጥ ዕውቀት ከፅናት ያሟላው ባለ ሙሉ ስብዕናው እስክንድር ከእስርቤት ውጭ ቢሆን፣ብዕሩንም ባይነጥቁት ኖሮ ወንበራቸው ላይ መደላደሉ ቀላል አይሆንላቸውም ነበር፡፡ኢትዮጵያ ያዋለደቻቸው ሃገራት ዲሞክራሲን ሲተገብሩ የሃገሩ ከዲሞክራሲ እድል ፋንታ መጉደሏ ይቆጨዋል፣ ያሳፍረዋል፣የተደራጀ ዘረፋው የሚያስከትለው የሙስና ጣጣ በደንብ ይገባዋል፤በጣም ያሳስበዋል፡፡ የነፃ-ሚዲያ ያለመኖር ሙስናን ለመዋጋት ያለማስቻሉ ጉዳይ አጥብቆ ያስጨንቀዋል፡፡ነገ ምን ይመጣብኛል ሳይል ፣በአውሬዎች መዳፍ እንዳለ ሳያጣው ባገኘው አጋጣሚ በወንዝ ልጆች የሚደረገውን የተደራጀ ዘረፋ እና ገፈፋውን ያጋልጣል፡፡ ሞትን ንቆ፣ወፌ ላላ ግርፋትን ያላየ፣አጥንቱ ተሰብሮ በሸክም ያልወጣ ያልገባ ይመስል፣ያልወለደ፣ የልጅ ናፍቆት ያላዋተተው ያህል ላመነበት ጉዳይ ይተጋል፡፡ይሄ ፅናቱ ከማከብረው እና ከማደንቀው ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ እንደ አቶ አንዳርጋቸው ሁሉ እስክንድር የራሱ ገላ ምቾት አያስጨንቀውም፡፡ ከሰው በላይ ሆኖ ለመታየት የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ አልባሌ ሳይሆን እንደ አልባሌ ይኖራል፡፡ የነፍሱ ረሃብ ስጋውን አክስቶታል፡፡ በቀጭን ስጋው ውስጥ ግን ትልቅ ነፍስ መሽጋለች! በነፃነት ጉዟችንም ሆነ ስኬታቸን ውስጥ ይህችን ነፍስ ልናከብር ይገባል፡፡ እስክንድር ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት አርበኛችን ብቻ ሳይሆን የትም ብናሰልፈው የሚያኮራን ድምጻችን ነው!

መስከረም አበራ

Filed in: Amharic