ይድረስ ለቢሾፍቱው ቆሪጥ
ከአንተንሳይ መስፍን
ደራሲ የሚለው ስም እንዳንተ የሚገባው ያለ አይመስለኝም ።
ትዕግስቴ እና ጊዜዬ የፈቀዱልኝን ያህል መፅሀፍት አንብቤያለሁ እንዳንተ ‘ምሉዕ’ የሆነ ደራሲ አልገጠመኝም ።
በቃ ደራሲ ነሃ…ድርስ-ፍጥር ስታደርግ የሚያህልህ የለማ ።
የገሃዱ አለም ነፀብራቅ…ከእውነተኛው አለም የተቀዳ…ገለመሌ ….,ይሉት ጣጣ አይጨንቅህማ…
ከደራሲ ይልቅ ለፈጣሪ ሳትጠጋ ትቀራለህ?
የቡርቃ ዝምታን አነበብንልህ
ከጥላቻ ይሁን ከታዛዥነት ጭቃ አብኩተህ የአበጀሃት ታሪክ ልብወለድ ናት እያልክ እንኳ ባነበበውም ባላነበበውም በአግድም ተረክ እና በጆሮ ጠገብ እውቀት እየተዋዛች እኛ እንደ ውሾቹ ስንጮህ እሷ እንደ ግመሉ ለንቃን እያዘገመች ፤
አይናችን እያየ በየዋኻት ልብ ጎልብታ ከስሯ ሃቁን ቀብራ ድንጋይ ለብሳ ቆመች።
እኛ እግዜር ይይልህ ብለን አለፍን ።
ለነፃነታችን ደርግ ሣይመሰረት ገና የደርግን የግፍ አገዛዝ ተቃውመው ትግል ከጀመሩት ጋር እንዳንተ በጭማሪ ሠዓትም ቢሆን ፋኖ ያልተሠማራን ፈሪዎች ከእግዜር ይይልህ ሌላ ምን ለበቅ አለን?
እግዜር ግን አየልህ ፤
ይኼውልህ ዛሬ ….እንኳን አንተ ና የመሳሰሉህ ከምንም አንስታችሁ ያቋጠራችሁንን የጥንት ቂም ይቅርና ትናንት በፍፃሜ ‘ሀይል አገዛዝ’ ኃ/ማርያም ደሣለኝ ዘመን የተበዳደልነውን አክ እንትፍ ብለን ፤ ያንተና ኩባንያዎችህንም ጉዳይ የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን ብለን በፍቅር ተገምደን ያስረሳችሁንን ህብረት እንደገና ለመስተማር ድክ ድክ እያልን ነው ።
የጋዜጠኛው ፣ የደራሲው እና የስደተኛው ማስተዋሻ እያልክ የፃፍካቸውን ፤(‘የተስፋዬ በቀል’ ልትላቸው ትችል የነበሩ) ፅሁፎችንም አነበብናቸው ።
እኛ ሌላ ርዕስ ሰጥተንልሃል ።
ያጣ ለማኝ ተሣድቦ ይሄዳል
ሌላ ቁም ነገር የላቸውም ።
የቡርቃ ዝምታን ኤርትራዊ version የኑረልነቢ ማህደርንም አነበብንልህ ።
ወይ ያንተ ነገር!? የእኛ አልበቃህ ብሎ በኤርትራ ብሔረሰቦችም ውስጥ ያቺን የባልትና ውጤትህ የሆነች ፀረ-ዕምዬ መርዝ በኑረልነቢ ማህደር በኩል ትረጭ ጀመርክ ።
(ዕምዬ ስማቸውን ያልጠቀስኩት ላንተም ስለሚያምህ ፤ ለኔም ያንተ ሥም በተጠቀሰበት ገፅ የሣቸውን መጥቀስ ስለሚያመኝ ነው ። ጎበዝ ደራሲ ስለሆንክ ትረዳኛለህ ።)
በቡርቃ ና በኑረልነቢ መካከል ያለው ልዩነት የአንተ ቴክኒክና የገፀባህሪያት ስም ብቻ መሆኑን ለመለየት ጎበዝ አንባቢ መሆን አይጠይቅም ። ማንበብ መቻል ብቻ ይበቃል ።
ዋናው ጭብጥ በአንድ የምትቆረቆርለት በምታስመስልለት
ብሔር ላይ አንድ ጥላቻህን ልትደብቅለት እንኳ የማያስችልህ ንጉስ ፈፀማቸው የምትላቸው ልብወልድ ግፎች ናቸው ።
በብዙ ማዋዣ ተረኮች እና በተካንክበት የቃላት ጨዋታ ብታጅቦነቡናቸውም ሁለቱም መፅሀፍት ጭብጣቸው ንጉሡ ጭራቅ ነበር ነው ።
የዚህ ምንዝሩ ደግሞ ግልፅ ነው ። ዕልቂት ።
እግዜር ይይልህ አልን ።
አሁን ግን ወዲያው አየልህ
ከእናንተ ጀምሮ እስከ ኃያላን መንግስታት በተደረገ ረዥም ና እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ተለያይቶ የነበረው ህዝብ ያለገላጋይ ያለ ሽማግሌ በአንድ የስልክ ጥሪ ብቻ ተገናኘ።
‘ሁነኛ’ ሠው እስኪያገኝ ለረዥም አመታት ተደብቆ የኖረው የኑረልነቢ ማህደርም እንደታተመ ዘመን አለፈበት።
ይማሯል እንደ አካልዬ
ይዋጓል እንደ ገብርዬ
ይከሽፏል እንደተስፍዬ
የግርጌ ማስታወሻ
የልብወለድህ ፍሬ የሆነውን የአኖሌ ጡት እንዳለ አስቀምጠንልሃል ። አልፎ አልፎ ብቅ እያልክ መጥባት ትችላለህ ።