>

ለመላው የ"ፊንፊኔ"  የ"በርበራ" እንዲሁም  ያዲስ አበባ ነዋሪዎች!!!! (በእውቀቱ ስዩም)

ለመላው የ”ፊንፊኔ”  የ”በርበራ” እንዲሁም  ያዲስ አበባ ነዋሪዎች!!!!
በእውቀቱ ስዩም
*  ከሃያ ሺህ በላይ ህዝብ ባቀባበሉ ስነ- ስርአቱ ላይ የሚገኝ ከሆነ “አገር አለኝ ወገን አለኝ” የሚለው ዘፈን የሚመረጥ ሲሆን ፤የህዝቡ ቁጥር ከመቶ ያነሰ ከሆነ “ንፋስ ነው ዘመዴ” የሚለው ዘፈን ይመረጣል
 
በውቄ ስዩም  የተባለ ድህረ- ወጣት ተጋዳላይ ፤ ከተወለደባት እና ከተገረዘባት እናት አገሩ ተሰድዶ፤በዱር በገደሉ፤ በፓርኩ በሆቴሉ፤ በተራራው በስዊሚንግ ፑሉ ፤ሶስት ወር ሙሉ  ለናት አገሩ ሲንከራተት ቆይቶ ፤በመጭው መስከረም ሰላሳ በድል ይመለሳል፤ በዚህ ታሪካዊ ቀን  የጀግና አቀባበል ይደረግለታል፤ ያቀባበሉ ትንቢታዊ መርሀ ግብር ይህን ይመስላል፤
1 ከቦሌ አየር ማረፍያ; እስከ ረከቦት ጎዳና መታጠፍያ ድረስ፤ ያለው አውራጎዳና ከእግረኛ፤ከመኪና እና ከውፍጮ ቤት ከሚመለሱ የጋማ ከብቶች ዝውውር ነፃ ሆኖ ይቆያል፤
ካውሮፕላኑ እንደወረደ ፤ ክብሩን የሚመጥን ፍተሻ ይደረግለታል፤ የጉምሩክ ፈታሾች  ጀግናው በሻንጣው  ውስጥ  አስራ ሰባት ሞባይሎች፤ ዘጠኝ  ላፕቶፖች   እና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሶላር ባውዛዎች ደብቆ መያዙን ይደርሱበታል፤ ይሁን እንጂ ጊዜው የይቅርታና የመደመር መሆኑን ከግምት በማስገባት ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ ያሳልፉለታል፤
2  የቀድሞው ፕሪዚዳንት ክቡር መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ያየር ማረፊያው በር ድረስ መጥተው ይቀበሉታል፤ ‘ገና ለገና  በቅናሽ ዋጋ ተገኘ ብለህ፤ ይሄን በርገር ስትነፋ ኖረህ ፤ በሶስት ወር እኔን ቦንሰኸኝ መጣህ አይደል?   ብለው ወደ ተራማጅ ሆዱ (ቦርጩ)በከዘራቸው እየጠቆሙ ሙድ ይይዙበታል፤ በማስቀጠልም ደከም ያለ ነጭ ፈረስ እና ጋሻ ያበረክቱለታል፤ “ መቸም ኮርቻው  ላይ ጊዚያዊ ሊፍት ካልተገጠመለት  በቀር ይህንን ኮረሪማ ቁመት ይዘህ ፤በዚህ ቾፕስቲክ እግር ተመርኩዘህ ፤እዚህ ፈረስ ላይ ትወጣለህ ብየ ለማሰብ ይከብደኛል ‘ብለው ስጋታቸውን ይገልፁለታል፤ በመጨረሻም ‘በፈረሱ ዝዋይ ወርደህ ጋሪ ንዳበት፤ በጋሻው የደንበኞችን ሂሳብ ሰብስብበት ‘ብለው ይመርቁታል፤
3 የፖሊስ ኦርኬስትራ በማርሽ የታጀበ  ሙዚቃ ይጫወትለታል፤ የሙዚቃው አይነት ላቀባበል እንደመጣው ህዝብ መጠን ይወሰናል፤ከሃያ ሺህ በላይ ህዝብ ባቀባበሉ ስነስራት ላይ የሚገኝ ከሆነ “አገር አለኝ ወገን አለኝ” የሚለው ዘፈን የሚመረጥ ሲሆን ፤የህዝቡ ቁጥር ከመቶ ያነሰ ከሆነ “ንፋስ ነው ዘመዴ” የሚለው ዘፈን ይመረጣል፤
3 በምሊኒየም አዳራሽ አጠገብ በሚገኘው ሬስቶራንት   እኔ ነኝ ያለ የራት ግብዣ ይደረግለታል፤ ከራት በሁዋላ ያዲሳባ መስተዳደር  የምክትል ከንቲባ ተኬ ኡማ  የጀግናውን አጣዳፊ ችግር ተገንዝበው ፤ቁልፍ  ያበረክቱለታል-የመፀዳጃ ቤት::
4   በመጨረሻን ም፤ ምክትል ከንቲባው፤ በውቄ ያለበትን የመኖርያ ቤት  ችግር ከግምት አስገብተው፤ በቅርቡ ከተገኙት ባለቤት የሌላቸው ህንፃዎች   አንዱን መርጦ ከበሩ ላይ ቆሞ፤ወይም ተኝቶ  ፎቶ እንዲነሳ ይፈቅዱለታል፤
Filed in: Amharic