>
12:02 pm - Tuesday October 26, 2021

ሴናተር ጆን ማኬይን - በሴናተር ባራክ ኦባማ በተሸነፉባት ዕለት - ያሰሙዋት ዘለዓለማዊ ንግግር!! (አሰፋ ሀይሉ)

ሴናተር ጆን ማኬይን – በሴናተር ባራክ ኦባማ በተሸነፉባት ዕለት – ያሰሙዋት ዘለዓለማዊ ንግግር!!
አሰፋ ሀይሉ
ይህ በጥቅምት 29 ቀን 2001 ዓ.ም.፣ በባራክ ኦባማ የተሸነፉት የሪፐብሊካኑ ሴናተር ጆን ማኬይን፣ ሽንፈታቸውን ከሰሙ በኋላ ያሰሙት የስንብት ንግግር፡፡ አሁን – እርሳቸው በ81 ዓመት ዕድሜያቸው – ሞተው – በትናንትናው ዕለት ቀብራቸው – በሚወዷት ሀገራቸው አሜሪካ – በአናፖለስ፣ ሜሪላንድ – በክብር ተፈጽሞላቸዋል፡፡ እርሳቸው ቢያልፉም ግን – ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር – እና ሥራቸው – በዲሞክራሲ በሚያምኑ እና ዲሞክራሲን በሚወዱ ሁሉ ዘንድ – ዘወትር ሲጠቀስላቸው ይኖራል፡፡ ንግግራቸውን የሰማ – ንግግራቸውን ያነበበ ሁሉ በሕይወቱ ብዙ ያተርፋል፡፡ የእርሳቸውን – አምላክ – ነፍሳቸውን በሠላም ያሣርፍ፡፡ መልካም ንባብ – መልካም ጊዜ – ለእኛ ለቋሚዎቹ – እና ለነገ አላፊዎቹ – ለሁላችን ጋብዤ ተለየሁ፡፡ የህይወታቸው መታሰቢያቸው ሊባል የበቃው አስደማሚ ንግግራቸው እነሆኝ፡-
«ወዳጆቼ ለሆናችሁት – አሁን – የታላቁ ጉዞአችን ፍጻሜ ላይ ደረስን፡፡ የአሜሪካ ሕዝቦች የሚፈልጉትን ተናግረዋል – ደሞ ግልጽ አድርገው ነው የተናገሩት፡፡ ከአፍታ ቀደም ብዬ – ለሴናተር ባራክ ኦባማ ስልክ የመደወል ክብር ደርሶኝ ነበር – እኔም እሱም – ሁለታችንም የምንወዳትን ይህቺን ሀገር – ቀጣይ ፕሬዚደንቷ በመሆን እንዲመራት ስለተመረጠ – እንኳን ደስ ያለህ ለማለት፡፡
«እንዲህ ባለው – ረዥም ጊዜ በፈጀ እና ፈተናው ከባድ በሆነበት የምርጫ ዘመቻ ተወዳድረን – እርሱ በአሸናፊነት መወጣቱ – ይህ ራሱ – የእርሱን የላቀ ችሎታ እና ያን ተቋቁሞ የማለፍ ፅናቱን – በግድ እንዳምን ያደረገኝ እውነታ ነው፡፡ ደግሞ – እርሱ ይህን ድል ሊቀዳጅ የቻለበት መንገድ – ብዙዎችን – ከዚህ በፊት – በአሜሪካ ፕሬዚደንት ምርጫ ድምፃቸውን ሰጡ አልሰጡ ልዩነት አናመጣም በሚል ዕምነት ራሳቸውን ወደዳር ያወጡ – በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያንን አነሳስቶ – ለውጥ እናመጣለን በሚል ተስፋ እንዲነሡ በማድረጉ መሆኑ – ያን ሊያደርግ የቻለበት መንገድ – እጅግ ጥልቅ የሆነ አድናቆቴን እንድሰጠውና – ለስኬቱም እርግጠኛ እንድሆንበት ያደረገኝ ነገር ነው፡፡
«ይሄ የምርጫ ድል – በተለይ ደግሞ – ለአፍሪካ-አሜሪካውያን ሁሉ – በህይወታቸው ልዩ ትርጉምን የሚያመጣላቸው –  ልዩና ታሪካዊ ምርጫ እንደሚሆንላቸው – ደግሞ እንዲያም በመሆኑም – በዛሬዋ ዕለት – ያ ልዩ የድል ኩራት ሊሠማቸው እንደሚገባ – ከልብ አምናለሁ፡፡
«እኔ ሁልጊዜም ቢሆን – አሜሪካ – በርትተው ለሚሠሩት እና አጋጣሚውን ለሚጠቀሙበት ሰዎች ሁሉ – የዕድል በሯን ትከፍታለች የሚል ፅኑ ዕምነት አለኝ፡፡ ሴናተር ባራክ ኦባማም – ያን በፅኑ እንደሚያምን አውቃለሁ፡፡ እና ደግሞ – እኔም ሆንኩ ባራክ ኦባማ – እንደሀገር በተጓዝንበት ረዥሙ ታሪካችን – በእኛ ዘንድ ሠፍነው በቆዩት – እና በሀገራችን መልካም ስምና ዝና ላይ የራሳቸውን ጥቁር አሻራ አሳርፈው ባለፉት – በእነዚያ ያረጁ ኢፍትሃዊ አካሄዶቻችን የተነሣ – ሀገራችን የተወሰኑ ዜጎቿን – ነፃነት ሊያስገኝላቸው ይችል የነበረውን ታላቅ በረከት ነፍጋ መቆየቷ ሣያንስ – የእነዚያ ትውስታ ራሱ – አሁን ድረስ ባስታወሱት ቁጥር የሚያም ያልሻረ ቁስልን በህዝባችን ላይ ተክሎባቸው እንዳለፈ – እና – እዚህች የዛሬዋ ዕለት ላይ ለመድረስ – ብዙ ብዙ መጓዝን እንደጠየቀን – ሁለታችንም እናውቃለን፡፡
«ከአንድ ክፍለዘመን በፊት – ፕሬዚደንት ቲዎዶር ሩዝቬልት – ጥቁር አሜሪካዊውን ቡከር ቲ. ዋሺንግተን – ዋይት ሀውስ ተገኝቶ ራት እንዲመገብ መጋበዙ ሲሰማ – ከብዙ ማዕዘኖች – ምን ያህል የነደደ ቁጣ ቀስቅሰው እንደነበር እናውቃለን፡፡ የአሁኗ አሜሪካችን ግን – ከዚያ መሠሉ ግፍ – እና ከዚያ ዘመኑ ትምክህትን ከተሞላ ዘረኝነት – ዓለማትን የሚያስከነዳ ርቀት የተሻገረች ሀገር ሆናለች፡፡ ለዚህ ደግሞ – አንድ አፍሪካ-አሜሪካዊ ሰው – የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ሆኖ ከመመረጥ በላይ – ዓይነተኛ ማስረጃ ሊሆነን የሚችል ነገር የለም፡፡ ከአሁን በኋላ – በዚህች የምድራችን ኃያል ሀገር ምድር ላይ – አሜሪካዊ ዜጋ የሆነ ማናቸውም ሰው ቢሆን – በዜግነት ማግኘት ያለበትን ክብር እና ሙሉ መብት – ሳያገኝ የሚቀርበት – አንዳችም ምክንያት አይኑር፡፡
«ሴናተር ኦባማ – ለራሱ በግሉ እና – ለዚህች ሀገር – ታላቅን ነገር ዛሬ ተቀዳጅቷል፡፡ ለዚህ ድሉ በአድናቆት አጨበጭብለታለሁ፡፡ እና – ያች ንፁህ ልብ የነበራት አያቱ – በሕይወት ኖራ – ይህችን ቀን አብራው ቆማ ልታይ ባለመቻሏ – በውስጤ ያሳደረብኝን የጋራ ስሜት በዚህ አጋጣሚ ልገልጥለት እፈልጋለሁ፡፡  ይህን የምለው ግን – በእርግጥ አሁን በህይወት ይህን ልታይ ባትታደልም – ያች ፅኑ ሴት – በፈጣሪዋ ዘንድ ነፍሷ በሠላም እንደምታርፍላትና – ይህ በልጅነቱ እንዲያድግላት ሳትታክት የታተረችለት መልካም ሰው እዚህ ላይ በመገኘቱ – እጅግ ታላቅ ክብር እንደሚሰማት – እምነታችን – ይህንን – ከልብ በእርግጠኞች እንድንቀበል እንደሚያደርገን – ስቼው አይደለም፡፡
«ሴናተር ኦባማ እና እኔ የሀሳብ ልዩነቶች ነበሩን – እና ተከራክረንባቸውም ነበረ – እናም እርሱ በክርክሩ በደንብ ረትቶኛል፡፡ በእርግጥ ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ነገር ቢኖር – ከእነዚያ እኔንና እርሱን ከማያስማሙን ነገሮች ውስጥ – ብዙዎቹ – ልዩነታችን መሆናቸው ታውቆ አብረውን እንደሚቀጥሉ ነው – ለዚያ አንዳች ጥርጥር አይግባችሁ፡፡ ሀገራችንን  – እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ወቅቶች ይገጥሟታል – በዚያ ሁሉ ውስጥ ግን – ዛሬ – በሙሉ ልብ ቃል ልገባለት የምፈልገው ነገር ቢኖር – እርሱ ሀገራችንን በፈተናዎቿ ውስጥ እንዲመራት በማናቸውም ጊዜ ላይ የሚያስፈልገው  – ማንኛውም በእኔ አቅምና ኃይል ሁሉ ተጠቅሜ ማድረግ የምችለውን ማናቸውንም ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ – ከጎኑ እንደምገኝለት – እና ያገራችንን የበዙ ችግሮች – የቱንም ያህል ቢሆኑ – በጋራ ሆነን መሻገር እንደማያቅተን ነው፡፡
«እኔን ስትደግፉ የነበራችሁ አሜሪካውያን ሁሉ – አሁን እናንተን የምጠይቃችሁ – እርሱን ከእኔ ጋር አብራችሁ እንኳን ደስ ያለህ እንድትሉት ብቻ ሣይሆን – ለቀጣዩ ፕሬዚደንታችን – ሁላችንንም ወደ አብሮነት ሊያመጣን የሚያስችለንን – አስፈላጊ ወደሆኑት ይቅር-ለግዜር መባባሎች የሚያደርሱንን መንገዶች የምንቀይስበትን – ልዩነቶቻችንን እንድንሻገር እና ታላቁን ብልጽግናችንን ዳግም እንድናረጋግጥ የሚያስችለንን – በዚህ አደገኛ በሆነ ዓለም ውስጥ ደህንነታችንን ለማስጠበቅ የሚያስችለንን – እና ልጆቻችንን እና የልጅ ልጆቻችንን እኛ ከወረስናት የበለጠ ጠንካራ፣ የተሸለች ሀገር እንድንተውላቸው የሚያስችለንን – ቀና አስተሳሰባችሁን ከልብ በመነጨ ፈቃደኝነት ልባችሁን ገልጣችሁ እንድትሰጡት – እና ያልተቆጠበ ጥረታችሁ እንዳይለየው ጭምር ነው – በአደራ ጭምር የምጠይቃችሁ፡፡
«ልዩነቶቻችን የቱንም ያህል ቢሆኑም – እኛ ሁላችን አንዳችን የሌላኛችን ወገን የሆንን አሜሪካውያን ነን፡፡ እና ያን አሜሪካዊነት ሊገዳደር ወይ ሊያፈርሰው የሚችል – አንዳችም ሌላ ሰዎች ተሰባስበው የሚፈጥሩት ማህበር ሊኖር እንደማይችል – እኔ ስነግራችሁ – እርግጠኛ ሆናችሁ እንድታምኑኝ እጠይቃችኋለሁ፡፡
«በዚህች በዛሬዋ ዕለት [የሽንፈት ስሜት የሚያጠላብን] የተወሰነ ግራ የመጋባት ስሜት በላያችን ሊንግስብን እንደሚችል የታወቀ ነው – ነገር ግን – ነገ – ይህን የዛሬውን ስሜታችንን ተራምደነው እንሂድ – እና ሀገራችንን ዳግመኛ ወደፊት እንድትራመድ ለማድረግ – ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን – አብረን በጋራ ለሥራ እንነሣ፡፡ ብዙ ውጊያዎችን እንደወገን አብረን ቆመን ተዋግተናል – ስንዋጋ ደግሞ – ያን የሚጠብቀንን ጦርነት – ከልብ ቆርጠን ደማችንን አምርረን በኅብረት እንዋጋው!
«ደግሞ የማረጋግጥላችሁ ነገር – ምንም እንኳ እናሸንፋለን ብለን ተነስተን – ያሰብንበት ሳንደርስ – ጉዞአችን በሽንፈት የተቋጨብን ቢሆንም – ነገር ግን ይህን ስሙኝ – ሽንፈቱ የእኔ ነው – የናንተ አይደለም!
«ለሁላችሁም ለእኔ ትልቅ ክብር የሆነውን ድጋፋችሁን ለሰጣችሁኝ – እና ማናቸውንም እገዛ ስታደርጉልኝ ለነበራችሁ ሁሉ – ላደረጋችሁልኝ ለእያንዳንዷነገር ሁሉ – ከልብ – በጣም ከልብ አመሰግናችኋለሁ፡፡ ወዳጆቼ – እናንተ አሁን የሚሰማችሁን ሳስብ – የዛሬዋ ቀን ይዛ የመጣችልን ውጤት ተቀይሮ – ሌላ ቢሆን ኖሮ ብዬ – እንዴት ከልቤ እንደምመኝ – የውስጤን ገልጬ ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ገና ከመነሻው ጀምሮ – መንገዱ አዳጋች ነበረ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን – ከእናንተ መሐል ድጋፉን የነሣኝና የወዳጅነት ፊቱን ያዞረብኝ ሰው ፈጽሞ አላጋጠመኝም፡፡ ለዚህ ለእኔ ላሳያችሁኝና ላደረጋችሁልኝ ነገር ሁሉ – የቱን ያህል የከበደ ውለታ እንደሚሰማኝ የምናገርበት በቂ ቃላት የለኝም፡፡
«በተለይ ባለቤቴን ሲንዲን – ልጆቼን – ውዷን እናቴን – እና ሁሉንም ቤተሰቦቼን እና በዚህ ረዥም መንገድ በፈጀ ውጣ ውረድ የበዛበት የምርጫ ዘመቻ ወቅት ሁሉ ከጎኔ ሆነው አብረው አስቸጋሪውን ጉዞዬን የተወጡትን ብዙ የጥንት ወዳጆቼን እና ውድ ጓደኞቼን ሁሉ ለውለታችሁ ባለዕዳ መሆኔን እወቁት፡፡ ከዚህ ከሰጣችሁኝ ማበረታታት እና ካሳያችሁኝ ፍቅር የበለጠ በህይወቴ ላገኝ የምችለው ዕፁብ-ድንቅ የሆነ ነገር ከቶውኑም ሊኖር እንደማይችል ዛሬ ላረጋግጥላችሁ እና ከልብ ላመሰግናችሁ እፈልጋለሁ፡፡
«ያው እንደምታውቁት መቼም – ምርጫዎች ሲባሉ ባጠቃላይ – በተለይ – በእጩ ተወዳዳሪው ቤተሰብ ላይ የሚያሳድረው ጫና – ከሁሉም የባሰ ነው፡፡ በዚህም የምረጡኝ ዘመቻዬ የሆነው ያ ነበር፡፡ አሁን ለውድ ቤተሰቤ ማለት የምፈልገው – በቃ እናንተ ያለፋችሁበትን ሁሉ ሊያካክስ የሚችል አንዳች ነገር በእኔ አቅም ላደርግላችሁ የምችለው ነገር ቢኖር – ከልብ የመነጨ ፍቅሬን ነው – ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን ነው – እና ደግሞ ካሣለፍነው የተሻለ ሠላም የሰፈነባቸውን የወደፊቶቹን ዓመታት ነው ቃል የምገባላችሁ፡፡
«… በዚህ ምርጫ ለማሸነፍ የሚያስችለንን በእኛ አቅምና ኃይል ውስጥ ሁሉ ማድረግ የሚቻለንን ሁሉ አደርገናል፡፡ ከዚህ በላይ ሌላ ልናደርገው የምንችለው ነገር ይኖር እንደሆን በበኩሌ አላውቅም፡፡ ያን ለሌሎች ያን ሂደት አጥንተው ያን መናገር ለሚችሉ እተወዋለሁ፡፡ በተረፈ ግን – ማንኛውም እጩ ተወዳዳሪ ስህተት ያጋጥመዋል – ስህተት የማይሰራ እጩ የለም – እና እኔም እርግጠኛ ነኝ – ከእነዚያ መሠሎቹ ስህተቶች – ዳጎስ ያሉትን ያበረከትኩት እኔ ራሴው ነኝ፡፡ ነገር ግን – የማረጋግጥላችሁ ነገር – እነዚያ እንዲህ ሊሆኑ ይችሉ ነበር – እንዲያ ቢሆኑስ ኖሮ ብዬ – በወደፊት ሕይወቴ – የአንዲትን [የሰከንድን ሽራፊ ያህል] ቅጽበት እንኳ ጊዜ ለፀፀት እንደማላጠፋ ነው፡፡
«ይህ የምርጫ ዘመቻ – በሕይወቴ ሁሉ ካደረግኳቸው ነገሮች – ትልቅ ክብር እንዲሰማኝ ያደረገ ተግባር ነበር – እና ለወደፊትም ጭምር – በእኔ ዘንድ ያለው ክብር እንደዚያው ነው፡፡ እና ልቤ የተሞላው በሌላ ነገር ሣይሆን – በተሞክሮዬ ላገኘሁት ልምድ ያለኝ ከፍ ያለ ምስጋና – እና ደግሞ – የአሜሪካ ህዝብ – ሴናተር ባራክ ኦባማን እና የድሮ ጓደኛዬን ሴናተር ጆ ባይደንን – [ፕሬዚደንት እና ምክትል ፕሬዚደንት ሆነው] – ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በመሪነት ይወስዱን ዘንድ ክብር አጎናፅፈናቸዋል – ብሎ ከመወሰኑ በፊት – እኔንም ከምንም ዓይነት አድልዎ ነጻ ሆኖ – በእኩል ሊመዝነኝ ዝግጁ ሆኖ – የምለውን ሊያደምጠኝ ሙሉ ጆሮውን ስለሰጠኝ – ከፍ ያለ የምስጋና ስሜት ልቤን እንደሞላው ይኖራል፡፡
«ዛሬ – አሁን በዚህች ምሽት – ከሌሎች ምሽቶች ሁሉ በላቀ መልኩ – ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ይህችን የምወዳት ሀገሬን እያገለገልኩ የኖርኩበትን ዕድሜዬን የምፀፀትና የማማርር ሰው ዓይነት ብሆን ኖሮ – እውነት እውነት እላችኋለሁ – አሜሪካዊ ተብዬ የመጠራት ክብሩ የማይገባኝ ሰው እሆን እንደነበር አልጠራጠርም፡፡ ዛሬ – በዚህች እጅግ በምወዳት ሀገሬ ላለው የመጨረሻው ከፍተኛው የመሪነት ሥልጣን እጩ ተወዳዳሪ ነበርኩ፡፡ አሁን በዚህች ምሽት ደግሞ – እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ – ሀገሬን ወደማገልገሌ ተመለስኩ፡፡ ይሄ ለማንኛውም [ክብር ለሚሰማው ሰው ሁሉ] የተቀደሰ ሥጦታ ነው – እና ለዚያ የአሪዞናን ህዝብ አመሰግነዋለሁ፡፡
«እና – ዛሬ – አሁን በዚህች ምሽት – ከሌሎች ምሽቶች ሁሉ በበለጠ መልኩ – እኔንም የደገፉኝንም ይሁን ወይም ሴናተር ኦባማን የደገፋችሁት ብትሆኑ – ለሁላችሁም አሜሪካውያን ወገኖቼ – ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው – በልቤ ውስጥ – ምንጊዜም ቢሆን የምታገኙት – ለእናንተ ለዚህች ሀገር ዜጎች ያለኝን – እና ለዚህች ሀገር ያለኝን ጥልቅ ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ምንም የለም፡፡ ቀደም ብሎ የምርጫ ተቀናቃኜ ሆኖ ለቆየው – ከዚህ በኋላ ደግሞ የወደፊቱ ፕሬዚደንቴ ለሚሆነው – ለሴናተር ኦባማ – አምላክ በነገሩ ሁሉ ፈጥኖ እንዲደርስለት – ከልቤ እመኝለታለሁ፡፡
«እና ደሞ – በዚህ ዘመቻዬ ደጋግሜ እንዳደረግኩት ሁሉ – አሁንም – ያንኑ መልዕክቴን በዚህች ቅፅበት ለማስተላለፍ እፈልጋለሁ – ወድ ለአሜሪካውያን ወገኖቼ ሁሉ – ለሁላችሁም ነው መልዕክቴ – አሁን ላይ በምትኖሩት ኑሮ የተነሣ – በምትገፉት ፈተና የተሞላበት ህይወት የተነሣ – ገና ለገና በችግር ተከበብኩ ብላችሁ – ፈጽሞ ምሬት እውስጣችሁ ዘልቆ እንዲሰማችሁ አትፍቀዱለት – ፈጽሞ ተስፋ መቁረጥ በውስጣችሁ አይግባ – ይልቁን – ሁልጊዜም ቢሆን – ሁሌም – በአሜሪካ ታላቅነት እና ልታመጣላችሁ በምትችለው የነገ ተስፋ ከልባችሁ እመኑ – ምክንያቱም – በዚህች ሀገር – እዚህች ምድራችን ላይ – የማይቻል ምንም ነገር የለምና!»
«አሜሪካኖች – ተስፋ ቆርጠን አናውቅም፡፡ እኛ – እጅ ሰጥተን አናውቅም፡፡ እኛ – በታሪክ ፊት ተደብቀን አናውቅም፡፡ እኛ – ታሪክ ሠሪዎች ነን፡፡ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ – እና ..አምላክ እናንተን ይባርክ – እና አምላክ አሜሪካንን ይባርክ፡፡»
— Transcript of John McCain’s Concession Speech, ELECTION 2008, November 5, 2008.
እኛንም ደግሞ – ሕዝባችንን፣ ሀገራችንን – አምላክ አብዝቶ ይባርክልን፡፡ እንደ ማኬን ያሉትን – በአስደናቂ ንግግራቸው – እና አርአያነት ያለው ምግባራቸው – ከመቃብራቸው በላይ ሲዘከሩ – ከትውልድ ትውልድ ውለታን ሠርተው የሚያልፉን – የተቀደሰ አርቆ አስተዋይ ልብ ያላቸውን – ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን – አምላካችን – በዚህች ምድራችን ላይ ያምጣልን፡፡
እምዬ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡
Filed in: Amharic