>
5:13 pm - Monday April 18, 5414

ለውሸት ታሪክ የእውነት ህይወት አትክፈሉ!!! (አብረሃም ወልዴ)

ለውሸት ታሪክ የእውነት ህይወት አትክፈሉ!!!
አብረሃም ወልዴ
* እውነትም እንኳ ሲቆይ ተረት ነው የሚሆነው:: ታዲያ እንዴት ሰው በተረት ይጣላል? ከተረት መልካም መልካሙን ወስደን ወደፊት እንይ:: ሁላችንም ለሃገራችን አብይ እንሁን::
ተወልጄ ያደኩት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ውስጥ ነው:: እኔ የተሰራሁት በደገኞቹ ደግ ኦሮሞዎች በቆለኞቹ ብልህ አማሮችና በወይናደጋው ስብጥር የፍቅር ማህበረሰብ ጥበብ ነው:: እኔን የሰሩ እነሱ ናቸው:: ኦሮሞ ሲነካ ያመኛል:: ኦሮሞ ሲታማ ይሰማኛል:: የትኛውም የፍቼ ልጅ የኔን ሃሳብ ይጋራል:: ምክንያቱም እኛ እንደ አንድ ቤት ልጆች ነው ያደግነው:: ኦሮሞ ፍቅር ነው:: ኦሮሞ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ነው:: በእርግጥ እንደ ኦሮሞ የተበደለ ህዝብ ያለ አይመስለኝም:: የማይገባውንም መከራ ያልዘራውንም ያጨደ ህዝብ ነው:: ስርዓቶች በድለውታል:: አየለ በቀለ አበበ ከበደ እሸቱ ተሰማ ግርማ ስሜ ታደሰ…. እነዚህ የስም ስያሜዎች በይበልጥ የኦሮሞ የሆኑበትን ታሪክ ብቻ ማወቅ በቂ ነው:: ነገር ግን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አገዛዞቹን ሁሉ ሲታገል የኖረው ከዚህ አይነቱ የጭቆና ደዌ ኦሮሞንም ለማላቀቅ መሆኑን የኦሮሞው ማህበረሰብ ያውቃል ብዬ አምናለሁ:: ከዚህ ወዲያ የኦሮሞን ችግርንም በደልንም ማየት አንፈልግም:: ምንም እንኩዋን በጥቂቶች ጥፋት ሁሉም በመወቀስ ላይ ያለ ቢሆንም በአንፃሩ ህብረተሰቡ ኦሮሞን ሲያመሰግን የኦሮሞን ጨዋነት ሲሰብክ ባህልና ቁዋንቁዋውን ሲያጠናና ለጋብቻ ዝምድና ደጅ ሲጠናው እንጂ እንደ ሃገር አፍራሽ እያየው ስጋት ሲሆነው ከማይ ብሞት ይሻለኛል::
ዛሬ በርካሽ ጥቅም የተደለሉ ግለሰቦች በድረ- ገፅ ፅሁፎቻቸው ተቆርቆሪ መስለው የኦሮሞን ወጣት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሚሆን ቃላት እየወረወሩ ለቁጣ የሚያነሳሱት ሰይጣን ስለሆኑና ደም ስለሚጠማቸው ብቻ ነው:: የኦሮሞ ወጣት ስማኝ… እኔ በጣም ከሚወዳችሁ ስታነቡ ከሚያነቡት ውስጥ አንዱ ነኝ:: ከዚህ በህዋላ ግጭት ከዚህ በህዋላ ጥል ለእናንተ አይገባም:: እናንተ ከዚህ በህዋላ እየተመሰገናችሁ እየተመረቃችሁ ባህላችሁን ፍቅራችሁን ጥበባችሁን ቁዋንቁዋችሁን የምታሳዩበትና የምታስተምሩበት ግዜያችሁ ነው:: በትንሽ ነገር እልህ አትያያዙ:: አነካኪዎችን ብለጥዋቸው:: ዘመኑን ሊቀምዋችሁ ከሚልከሰከሱ ውሾች ተጠበቁ:: ከፍ በሉ እንጂ ዝቅ እንዳትሉ:: ስለ አማራና ስለ ኦሮሞ ፍቅር ፍቼ ከተማ ምስክር እንደሚሆን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ገልጬዋለሁ:: ለመውደድ ተሸነፉ:: ለፍቅር ብቻ ኑሩ::
ከፍፁም ፍቅርና ከፍፁም ተቆርቁዋሪነት የመነጨ ምክሬን ስሙ:: የምትወዱትን ባንዲራ ከፍ አርጉት እንጂ ዝቅ አታድርጉት:: ባንዲራን ከፍ የሚያረግም ዝቅ የሚያደርግም ስራ ነው::ለውሸት ታሪክ የእውነት ህይወት አትክፈሉ:: እውነትም እንክዋን ሲቆይ ተረት ነው የሚሆነው:: ታዲያ እንዴት ሰው በተረት ይጣላል?:: ከተረት መልካም መልካሙን ወስደን ወደፊት እንይ:: ሁላችንም ለሃገራችን አብይ እንሁን:: የኦሮሞና የአማራ ወጣቶች ማህበር ከሲዳማና ከወላይታ ወጣቶች ማህበር ጋር የሃረሪና የኦሮምያ ወጣቶች ማህበር ከሶማሌና ከአፋር ወጣቶች ማህበር ጋር በመተባበር ስለተሰራ የበጎ ስራ ዜና መስማት እንጂ መርዶማ የሰለቸን ነገር አይደለም እንዴ?
እኔ የማውቀውን ውድ ማንነታችሁን ሌላውም እንዲያውቀው እመኛለሁ:: የውስጣችሁን አውጡት:: ስለማውቃችሁ እናገራለሁ:: እናንተ ውስጥ ደግነትና ፍቅር ሞልትዋል:: አውጡት!!!
Filed in: Amharic