>
9:23 pm - Thursday February 2, 2023

ልጆቼ፣ ጉዳዩ ከባንዲራም በላይ ነው!

ልጆቼ፣ ጉዳዩ ከባንዲራም በላይ ነው!
– የዩኒየኒስት እና የፌደራሊስት ሙግት ጥንስስ ነው!!!
ማስታወሻ – Memoir
ልጆቼ «በአንድነት ስም ተጨፍልቄ እንድገዛ አታድርገኝ» እና «በብሔር መብት ስም አትከፋፍለኝ» የሚሉት ትርክቶች (narratives) እስካልታረቁ ድረስ ንትርካችን የሚያቆም አይመስልም!
በአንድ ወቅት የቀድሞ-ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ «ባንዲ ጨርቅ ነው» በማለት፣ አመክንዮ የሰነቀ ንግግር አድረገው ነበር፡፡ ንግግራቸው ያስቆጣው አያሌ ሕዝብ ቢኖርም አመክንዮአቸው ያሳመነው ሰው እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡
ውድ ናኦሚ እና ኒኪታ፣
አቶ መለስ በወቅቱ የዘነጉት ወይም ሆነ-ብለው የካዱት ነገር፣ ከሌላው ጨርቅ ለይቶ ባንዲራን ያገዘፈው ‘ማንነት’ የተባለው የሰውነት ንጥረ-ነገር፣ ‘ስሜት’ የተባለው የባህርይ መገለጫ፣ እንዲሁም ‘ታሪክ’ የተባለው የሰው ልጅ የኋሊት ክስተት በደማቁ የተፃፉበት የነፃነት ክታብ መሆኑን ነበር፡፡
በአሁን ሰዓት ከሕጋዊነት አኳያ ካየነው፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሆኖ መሃሉ ላይ የፌዴራል አርማ ይኖረዋል ተብሎ የተደነገገለት ነው፡፡ አርማው በሰማያዊ መደብ ላይ ያረፈ ቢጫ ኮከብ ነው፡፡ የፌዴራሉን አርማ፣
* አንድም ያለውን አገዛዝ በጭፍን በመጥላት፣
* አንድም የብሔር እኩልነትን ለማንፀባረቅ ብሎ ያስቀመጠው ሥርዓት የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ በመሆኑና ከፋፍሎ የመግዛት አዝማሚያ ስላለው፣
* አንድም አርማው የሌለው ባንዲራ ታሪካዊነት ስላለው፣
* አንድም ሃይማኖታዊ ትርክት ስለያዘ፣
* በመጨረሻ ደግሞ ባንዲራው ላይ አርማው ሲለጠፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ አልተጠየቀም፣ አልተመከረም በሚል ብዙዎቹ የ’አንድነት’ ፖለቲካ አራማጅ እና ደጋፊዎች ክፉኛ ያወግዙታል፡፡
ለ27 ዓመታት በሥልጣን የቆየው ሥርዓት ደግሞ በባሕርይው ‘ከሕዝብ እልህ የተጋባ’ ስለሆነ፣ ይባስ ብሎ ባንዲራውን ያለ አርማው ያውለበለበ ወንጀለኛ ነው ሲል በሕግ ደንግጎ አረፈው፡፡ ማስተዳደሩን ትቶ ስለምን አጉል እንዳደገ ሕፃን ከሕዝብ ጋር እልህ እንደሚጋባ ተረድቼው አላውቅም፡፡
ልጆቼ፣ በአሁን ሰዓት ግን የመንግስት እልኸኝነት አክትሟል፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት ወጣቱ ሥርዓቱን እምቢኝ በማለቱ ሁነኛ ሀገራዊ ለውጥ እየታዘብን ነው፡፡ ይህንን ማስታወሻ ለእናንተ ለልጆቼ የማስቀረቴ ዓላማም በዚህ ወቅት በአካል እየታዘብኩት ያለውን ሀገራዊ ሁናቴ ከእኔ ከአባታችሁ ምልከታ አንፃር ታጤኑት ዘንድ ነው፤ ምናልባትም እነዚህ በየዕለቱ የምታዘባቸው ክስተቶች ከሃያ ዓመት በኋላ በተለያየ ትርክት ቀርበውላችሁ እውነታውን ያስታችኋል ከሚል ፍራቻ፡፡
እናም ዛሬ ማንም የፈለገውን፣ ማንነቴን እና ስሜቴን፣ ታሪኬን እና የታገልኩለትን ነፃነቴን ይገልፅልኛል ያለውን ባንዲራ አንግቦ ማውለብለብ ይችል ዘንድ ተፈቅዶለታል፡፡ ያሳለፍናቸው ሳምንታት አያሌ በውጭ ሀገር ሥርዓቱን ሲታገሉ የነበሩ ቡድኖች ወደ ሀገር የገቡበት፣ ከፍተኛ ሕዝባዊ አቀባበል የሚደረግበት ወቅት ነው፡፡ ያላየነው የባንዲራ ዓይነት የለም፤ ሁሉም የነፃነት ታጋይ የራሱ ባንዲራ አለው፡፡ (በነገራችን ላይ፣ የፌዴራል ሥርዓቱ አባል የሆኑት ዘጠኝ ክልሎችም የየራሳቸው ባንዲራ አላቸው፤ በተጨማሪም እያንዳንዱን ክልሎች የሚያስተዳድሩት የፖለቲካ ፓርቲዎችም የየራሳቸው ባንዲራ አላቸው፡፡ ገዢዎቹም፣ እነሱን ለመጣል የታገሉትም ለየቅል ባንዲራ ማንገባቸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባንዲራ ያለውን ቁርኝት አስቀድመው የተረዱ ይመስላሉ፡፡)
የሆነ ሆነና፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት የተባለው የፖለቲካ ቡድን ጳጉሜ 4 ቀን 2010 ወደ ሀገር ሲገባ፣ ያ ከላይ የነገርኳቹ የፌዴራል አርማ እንደዚያን ቀን ደብዛው ጠፍቶ አያቅም፤ ከተማዋ አዲሳባ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ተጥለቀለቀች፡፡ ሳር ቅጠሉ፣ ዛፍ እና ማማው፣ ሕንፃ እና አደባባዩ አርማ-የለሽ በሆነው የኢትዮጵያ ባንዲራ አሸበረቀ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ይሁን ብሎ ዝም ይበል እንጂ ቅር ያለው አልነበረም ማለት አይደለም፡፡
ተለይቶ በሚታወቅ መልኩ፣ በግልፅ በታየና በተሰማ መልኩ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን በይፋ የሚቃወም እና የሚኮንን ሕዝብ ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ሆኖም የሕዝብ ስሜትን በደፈና መመዘን ከባድ በመሆኑ፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አኳያ መግለፁ ይበጃል፡፡ ስለሆነም ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የተባለው እድሜ-ጠገብ የፖለቲካ ፓርቲ ይህን ባንዲራ ይነቅፈዋል፤ የምኒልክ ባንዲራ ነው ይላል፤ ምኒልክ ደግሞ የኦሮሞን ሕዝብ ጨፍጭፏል፣ ግዞት ጠይቋል ብሎ ያምናል፡፡ ሌሎች ባንዲራውን ሲያዩ የደስታ እና የነፃነት ስሜት ሲሰማቸው፣ ኦነግ እና ደጋፊዎቹ፣ እንዲሁም ብዙ ኦሮሞዎች ባንዲራውን ሲመለከቱ የሀዘን ስሜት እና የጭቆና ትውስታ ይስማቸዋል፡፡ «ይሰማቸዋል» ብዬ አስረግጬ የምናገረ በአካል በወዳጆቼ ላይ በመታዘቤ ነው፤ እልህ ይዞአቸው «እህ!» የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በቃ ተሰማቸው፤ ለምን እንዲህ ተሰማችሁ ብሎ በደፈናው የኢትዮጵያ ጠላት አድርጎ መፈረጅ አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን በቁስላቸው ላይ እንጨት መስደድ ነው፡፡
በዛሬ ማስታወሻዬ ስለባንዲራ ማውራቴ ከሰሞኑ ክስተት ጋር በመያያዙ ነው፡፡ እናም አርበኞች ግንቦት ሰባትን ለመቀበል ከተማውን ሙሉ የተሰቀለው ባንዲራ፣ ከቀናት በኋላም በብዙ ቦታዎች አልወረደም፡፡ ትናንት እና ዛሬ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ልማት ተቋም፣ የኢጋድ ስብሰባ በመኖሩ ምክንያት፣ መንግስት በቦሌ መንገድ እና በሌሎች ጥቂት አካባቢዎች አርማ የሌለውን አውርዶ ‘ሕጋዊውን’ ባለአርማ ባንዲራ ሰቅሏል፡፡ (ይህ ሲደረግ ማንም አልተቃወመም፡፡)
ሆኖም ከነገ በስቲያ፣ መስከረም 5 ቀን 2011 ኦነግ የተባለው ፓርቲ ወደ ሀገር ይገባል፡፡ ከጊዜ ብዛት እና ሀገራቀፍም ዓለማቀፍም በሆኑ ክስተቶች ምክንያት ኦነግ ቢያንስ አምስት ቦታ የተከፋፈለ ፓርቲ ነው፡፡ ተከፍለው የወጡት (ዋና መስራቹን ሌንጮ ለታን ጨምሮ) የቀድሞ ኦነጎች እምብዛም አቀባበል ሳይደረግላቸው ወደ ሀገር ገብተዋል፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ተቀብሮ የኖረው ኦነጋዊ ስሜት ሃያል እንደሆነ አውቃለሁ፤ በገዢው ፓርቲ ኦሕዴድ አባላት ጭምር ኦነግ ተውዳሽ እንደሆነ፣ በመግቢያዬ ያነሳኋቸው አቶ መለስ ‘ስትፋቁ ኦነግ ናችሁ’ ያሉ ጊዜ ገልፀውታል፡፡ እናም መጪው ቅዳሜ አቀባበል የሚደረግለት ኦነግ ስሙንም፣ አርማውንም፣ ከጥንት ጀምሮ የተጠነሰሰውንም የነፃነት ትግል መርሆ እንደያዘ የቆየው ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ሽብርተኛ ያስብል ስለነበር፣ ሁሉም በልቡ ብቻ ታቅፎት የቆየ የራሱ ባንዲራም አለው፡፡ ይህን ባንዲራ ሲያዩ ሲቃ የሚይዛቸው፣ ለነፃነት ሲባል የተሰዉት ወንድም እህቶቻቸው የሚታወሷቸው አያሌ ኦሮሞዎች አሉ፤ ይህንንም በአካል ታዝቤዋለሁ፡፡
ልጆቼ፣ ዛሬ ላይ በለውጡ ምክንያት እልኸኛ መንግስት የለም፡፡ ነገር ግን እልኸኛ ሕዝብ ገና እንዳለ ነው፡፡ እንዲሁ በሀቀኝነት ለኦነግ የደመቀ አቀባበል ለማድረግም ይሁን ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ከተደረገው በላይ ለማድረግ፣ የኦሮሞ ወጣቶች ቁጥር የለሽ የኦነግ ባንዲራ አዘጋጅተዋል፡፡ ከቀናት በፊት የተሰቀለው፣ ኦነግ እና ደጋፊዎቹ የማይወዱት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ አሁንም አልወረደም፡፡ ታዲያ የኦሮሞ ወጣቶች የኦነግን ባንዲራ የት ይስቀሉ? በነገራችን ላይ፣ ይህ የኦነግ ባንዲራ ከኦነግ በፊትም የነበረ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ባንዲራ እንደሆነም በብዙ ኦሮሞዎች ዘንድ ይታመናል፡፡
ከትናንት ጀምሮ ባንዲራ አውርድ-አታውርድ፣ ልስቀል-አትስቀል እሰጥ-አገባ በከተማዋ እየተንሰራፋ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን መግለጫ እስከመስጠት ያደረሰ የወጣቶች ግብግብ ተስተውሏል፡፡ እነዚህን ወጣቶች «ባንዲራ እኮ ጨርቅ ነው፤ ቁምነገሩ ሕዝብ ነው፣ ወንድማማችነት ነው» በሚል አመክንዮ ማሳመን አይቻልም፡፡ የተሰቀለውን አውርዶ ሌላ መስቀል ሰቃዩን ያስከፋል፤ ያንን ሳታወርድ አብረህ ስቀል ማለት ደግሞ ቅድም እንዳልኩት በቁስል ላይ እንጨት መስደድ ነው፡፡
ልጆቼ ናኦሚ እና ኒኪታ፣ ምናልባት በናንተ ጊዜ ሕዝቡ በአንድ ባንዲራ ተማምኖ ይሆንና ይህ የገለፅኩት ተቃርኖ ሊያስቃችሁ ይችላል፤ ነገር ግን አሁን ላይ የባንዲራ ነገር ከልብ የመነጨ ግጭት ለማስነሳት አቅም አለው፡፡ ምናልባትም በናንተ ዘመን ተነጋግሮ የመግባባት ባህል ዳብሮ ይሆናልና፣ የእኛ ዘመን ሰው ለምን ይህ እንደተሳነው ያስደንቃችሁ ይሆናል፤ ነገር ግን ዛሬ ማውራት እንጂ መስማት የማንችል ሕዝቦች በኢትዮጵያ እየኖርን ነው፡፡ ለዚህም ነው ነገሩ ከባንዲራ በላይ ነው የምላችሁ፡፡
ውድ ናኦሚ እና ኒኪታ፣ የዛሬ የባንዲራ ጉዳይ በቀጣይ ወራት ገና በሰፊው የሚያከራክር ጉዳይን የሚያስከትል ነው፡፡ ይህም የፖለቲካውን ጎራ ‘ዩኒየኒስት’ እና ‘ፌደራሊስት’ በሚል የሚያቧድን ነው፡፡ ኦነግና ደጋፊዎቹ፣ እንዲሁም ከኦነግም በላይ ለለውጡ ምክንያት የሆኑት የኦሮሞ ነፃነት ታጋዮች ፌደራሊዝሙ እንዲነካባቸው አይፈልጉም፡፡ በሌላ በኩል የጥንቱን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ የሚያውለበልቡት፣ በኢትዮጵያ አንድነት አንደራደርም የሚሉና ፌደራሊዝሙ በብሔር ከፋፍሎናል ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ በመሆኑም፣ የሁለቱ ጎራ ሙግት ገና አልተጀመረም፤ የዛሬው የባንዲራ ንትርክ ጥንስሱ ነው፡፡
ልጆቼ፣ «በአንድነት ስም ተጨፍልቄ እንድገዛ አታድርገኝ» እና «በብሔር መብት ስም አትከፋፍለኝ» የሚሉት ትርክቶች (narratives) እስካልታረቁ ድረስ ንትርካችን የሚያቆም አይመስልም!
ሁለቱን ሀሳቦች በዲሞክራሲ ካላስታረቅናቸው በምን ሊታረቁ ይችላሉ? እዚያ እና እዚህ ሲዘላለፉ የነበሩ አቋሞች አሁን በኢትዮጵያ እውነተኛ ዲሞክራሲ መተግበር ሊጀመር ነው ሲባል፣ መሣሪያ እስከመጣል የደረሰ እርምጃ ወስደው የቀደመ የትግል ስልታቸውን ቀይረው ሀገር ቤት ይገኛሉ፡፡ ይህ በራሱ መልካም ጅምር ነው – ሁለቱን ሀሳቦች ለማስታረቅ፡፡
ታዲያ በቀጣይነት የሰከነ ውይይት ቢያደርጉ፣ ማለትም «ስጋትህ ምንድን ነው?» ተባብለው ቢጠያየቁ የማይግባቡበት የወደፊት እርምጃ ይኖር ይሆን? ‘በብሔር ማንነቴ ስበደል ኖሪያለሁኝ’ ሲል ‘አልተበደልክም’ ለምን ይባላል? በደሉን የሚያውቅ እራሱ! ይልቁንስ ‘ከዚህ በኋላ በደልህ እንዳይደገም ምን ይደረግ?’ ተብሎ በወንድምነት ቢጠየቅ ምላሹ ምን ይሆን? መቼም ‘እገነጠላለሁ’ ይላል ተብሎ ስጋት ውስጥ አይገባ፤ የቱንም ያህል ስጋቱ ቢገዝፍ ሕዝብን በስጋት ብቻ ተነሳስቶ ከመገንጠሉ አናድነውም፡፡ እስከሚገባኝ ድረስ የመገንጠል ሀሳብ ያላቸው ልሂቃኑም ቢሆኑ አዲሱ ዲሞክራሲ የእውነት ከሰፈን እንገንጠል ቢሉም ሰሚ ሕዝብ አይኖራቸውም፡፡
ውድ ልጆቼ፣ በሌላ በኩል ደግሞ «ኢትዮጵያ…ኢትዮጵያ… አንድነት… አንድነት…» መባሉ ሲደጋገም የሚያስደነግጠው ወይም የሚያስቆጣው ካለ ላይፈረድበት ይችላል፤ ግን ደግሞ ሊብራራለት ይገባል፡፡ እሱም ‘ኢትዮጵያ… አንድነት ስትሉ፣ የብሔር ማንነትህን ወዲያ ጣል ማለታችሁ ነው ወይ?’ ብሎ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ አሁንም እስከሚገባኝ ድረስ የብሔር ማንነትን የማስወገድ አላማ ያለው የአንድነት ፖለቲካ ልሂቅ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ ግን ደግሞ በአንድነት ውስጥ የብሔር ማንነት እንዴት ሊከበር እንደሚችል የትኛውም የአንድነት አቀንቃኝ ሲያብራራ አንሰማውም፡፡ ለማብራራት ከሞከረ፣ ኢሕአዴግ በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ በሕገመንግስቱ ያሰፈረውን መድገም ይሆንብኛል ብሎ ይሰጋ ይሆናል፡፡
ሆኖም ኢሕአዴግ በሕገመንግስቱ ያስፍረው እንጂ፣ አስፍሮም ለእኩይ ተግባር ይጠቀምበት እንጂ የብሔር ማንነትን ለማስከበር በሃቅ አልሰራበትም፡፡ «የራስን እድል በራስ መወሰን» የተባለው የብሔሮች መብት በሕገመንግስቱ መስፈሩ ኦሕዴድን ‘የህወሓት ሎሌ’ ከመባል አላዳነውም፡፡ ስለዚህም የአንድነት ፖለቲካ አቀንቃኝ ልሂቃኑ በልዩነት ያበበች አንድ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ካለመ፣ የብሔር መብት ተሟጋች ልሂቃን ስጋት ለመቅረፍ ይትጋ፡፡ የብሔር መብት ተሟጋቹ ፌደራሊስትም፣ የእርሱ መንገድ ለኢትዮጵያ አንድነት ስጋት አለመሆኑን በሰከነ አመክንዮ ያስረዳ፡፡ ግን ደግሞ ሁለቱም ወገኖች ቀና ልብ እና ጆሮ ይኑራቸው፡፡ እኛም ተመልካች ሕዝቦች፣ እንኳን ጳጉሜ ብቻ «የይቅርታ ቀን፤ የአንድነት ቀን» እይተባለች ተከፋፍላ፣ ጠቅላላ የዓመቱ ቀናት «የመደማመጥ ቀን» እየተባሉ ቢሰየሙ የሚደማመጥ አይኖርም ብለን ተስፋ አንቁረጥባቸው፡፡
እንግዲህ ውድ ልጆቼ፣ ናኦሚ እና ኒኪታ፣ ይህ በስተመጨረሻ ያልኩት ምኞቴ ነው፤ በቅርቡ በሳል ውይይቶች እና መደማመጦች እንደሚጀምሩም ተስፋ አለኝ፤ በቅርብ የማውቃቸውን አክቲቪስቶች እና ጋዜጠኞች ስለጉዳዩ እንዲወተውቱና የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ እመክራለሁ፡፡
ዛሬ በእናታችሁ ማህፀን 22 ሳምንታችሁ ነው፡፡ ተወልዳችሁ እስካያችሁ እጓጓለሁ፤ አድጋችሁ ስለሀገር ጉዳይ እስካወያያችሁ እናፍቃለሁ፡፡ በእናንተ ዘመን የኢትዮጵያ ባንዲራ ምን አይነት ሊሆን እንደሚችል ግን ለመገመት ያዳግተኛል፡፡
Filed in: Amharic